ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!

ሁለት ቴዲዎች ባለፉት ሳምንታት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ሰንብተዋል። በእርግጥ ሁለቱም በየፊናቸው ስኬታማ ለመሆን በቅተዋል። ከዚያ በስተጀርባ ግን በሁለቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል የነበረው ውዝግብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብዙ ነገር ይጠቁማል።

በመጀመሪያ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሁለቱም ቴዲዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሁለቱም ወገኖች ለድጋፍና ተቃውሟቸው የራሳቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል። ነገር ግን፣ ከሁለቱ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሲነሱ የነበሩት ሃሳቦች በዋናነት “ኢትዮጲያ” በሚለው ጭብጥ ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ።

እንደ ማንኛውም እውቅ ሙዚቀኛ በተለይ “ኢትዮጲያ” በሚለው ነጠላ ዜማ እንደወጣ ሌላው ቴድሮስ (ፀጋዬ) የሰነዘረው ሂስና ትችት ከዘፈኑና ዘፋኙ አልፎ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን አሳዝኗል፥ አስቆጥቷል። ከዚያ በተረፈ፣ ዘፋኙ የለቀቀው አልበም ተደማጭነት እንዳያገኝ ወይም ለአድማጭ ተደራሽ እንዳይሆን “በገበያ ላይ መቅረብ የለበትም” የሚል ተቃውሞ አልገጠመውም። ከዚያ ይልቅ፣ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ትኩረታቸው “አርቲስቱ ከብዙሃንነት ይልቅ የአህዳዊ አንድነት አቀንቃኝ ነው” የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ከአርቲስቱ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ በኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት – ኢብኮ (EBC) እንዳይቀርብ ታገደ። ስለ “ኢትዮጲያ” በመዝፈኑ አርቲስቱን “የአንድነት አቀንቃኝ ነው” በሚል ቃለ-ምልልሱ የሕዝብ ንብረት በሆነው ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይቀርብ ሲከለከል የፖለቲካችን ሕመም አገረሸ። በውሳኔው የቴዲ አፍሮ ደጋፊዎች ክፉኛ ሲቆጡ፣ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ በጣም ተደሰቱ። 

የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ በኢብኮ እንዳይተላለፍ በታገደበት ሳምንት ሌላኛው ቴድሮስ (ዶ/ር) “ኢትዮጲያን” ወክሎ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ሆኖ ለመመረጥ የመጨረሻውን ጥረት እያደረገ ነበር። በአንድ በኩል የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ዶ/ር ቴድሮስን በመደገፍ የዓለም-አቀፉ ድርጅት መሪ ሆኖ እንዲመረጥ ድጋፍና ቅስቀሳቸውን አጠናከረው ቀጠሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ተቃዉሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ከሁለቱም ወገኖች ምርጫው በሚካሄድበት ቦታ በአካል ተገኝተው ያሳዩት ድጋፍና ተቃውሞን እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ደጋፊዎች ለራሳቸው የብዙሃንነት አቀንቃኝ ሆነው የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን “የአንድነት አቀንቃኞች” እያሉ ሲያብጠለጥሏቸው ነበር። ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተርነት የሚደረገው ውድድር ሊጠናቀቅ ሲቃረብና በዶ/ር ቴድሮስ ላይ የሚካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲሄድ በአብዛኛው “የብዙሃንነት አቀንቃኝ” የነበሩት ደጋፊዎቹ ስለ አንድነት ማቀንቀን ጀመሩ። በዚህም “ዶ/ር ቴድሮስ እየተወዳደረ ያለው እንደ ግለሰብ ወይም መንግስት ሳይሆን ኢትዮጲያ እና አፍሪካን ወክሎ እንደመሆኑ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ኢትዮጲያዊ ድጋፉን ሊቸራቸው ይገባል” የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀረቡ። ቀድሞ የአንድነት አቀንቃኝ የነበሩት አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ደግሞ “ስለ አንድነት ሲባል ዶ/ር ቴድሮስ ከፍተኛ አመራር ከሆኑበት የኢህአዴግ መንግስት ጋር ያለንን ቅራኔና ልዩነት መተው አይቻለንም” በሚል ተቃውሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በዚህም የኢትዮጲያ ፖለቲካ ሕመሙ በጣም እንደፀናበት መገንዘብ ይቻላል።

አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጲያ አንድነት ይልቅ ብዙሃንነትን በማስቀደም የሁላችንም በሆነ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቃለ-ምልልሱ እንዳይተላለፍ አደረጉ። በተመሣሣይ፣ አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ተቃዋሚዎች ከአንድነት ይልቅ የፖለቲካ ልዩነትን በማስቀደም የዓለም-አቀፍ ድርጅት መሪ እንዳይሆን ተቃወሙ። ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም ቴዲዎች በየፊናቸው ስኬታማ ሆነዋል። በሁለቱም አጋጣሚዎች ተነስታ የወደቀችው ኢትዮጲያ ናት። ኢትዮጲያ ውስጥ እየኖረ ስለ ሀገር አንድነት ሲዜም የሚቀፋቸው በአንድ ወገን፣ ስለ ኢትዮጲያ አንድነት እያዜሙ የኢትዮጲያን ተወካይ የሆነ ተወዳዳሪ የሚቃወሙ በሌላ ወገን ሆነው አንዱ ሌላውን ሲጠላና ሲያጥላላ በመሃል ግራ ተጋብታ መሄጃ የጠፋት ኢትዮጲያ ናት።

“ኢትዮጲያ” በሚለው አልበም ዙሪያ ከትችትና ተቃውሞ ባለፈ ቃለ-ምልልሱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ ቢታገድም ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በሥራው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። ስለዚህ፣ ቴድሮስ አሸንፏል! ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ለመሆን ያደረገው ውድድር ምንም ያህል ተቃውሞ ቢገጥመው በምርጫው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። አሁንም ቴድሮስ አሸንፏል። በሁለቱም አጋጣሚዎች የታየው በቂምና ጥላቻ የታጨቀ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ “አንድነት” የሚለውን ቃል ትርጉምና ፋይዳ አሳጥቶታል። በአጠቃላይ፣ ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!!!

ዶ/ር ቴድሮስ ያሸነፈባቸው 4 ምክንያቶች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዳሬክተር ሆኖ የተመረጠበት ምክንያት በዋናነት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከግለሰብ ይልቅ በሀገራት ዲፕሎማሳዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ፋይዳ አንፃር ስለሆነ ነው። በዚህ መሰረት፣ ዶ/ር ቴድሮስ አሸናፊ የሆነው በሚከተሉት ከአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡-

1ኛ – አፍሪካ፡- ዶ/ር ቴድሮስ በኢትዮጲያ መንግስት ሙሉ ድጋፍ የተሰጠው እንደመሆኑ ከሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሳዊ ግንኙነትና በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና በመጠቀም ዶ/ሩ ሙሉ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። 

2ኛ – አውሮፓ፡- ሁለተኛው ተወዳዳሪ “Dr. Nabaro” እንግሊዛዊ መሆናቸውና ሀገራቸው እንግሊዝ ደግሞ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣቷ ይታወሳል። በዚህ ምክንያት፣ የእንግሊዙ ተወዳዳሪ ልክ እንደ ዶ/ር ቴድሮስ ከአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ሙሉ ድጋፍ የማግኘት እድል አልነበራቸውም።

3ኛ – ኢሲያ፡-  ሦስተኛዋ ተወዳዳሪ ፓኪስታናዊቷ “Nishtar” ከኢሲያ ክፍለ ሀጉር የመጡ ናቸው። ነገር ግን፣ ላለፉት አስር አመታት የዓለም የጤና ድርጅትን የመሩት ዳይሬክተር የዚሁ ክፍለ ሀጉር ተወካይ እንደመሆናቸው እኚህ ተወዳዳሪ ከኢሲያ ሀገራት ሳይቀር ሙሉ ድጋፍ የማግኘት እድል አልነበራቸውም።

4ኛ፡- ላቲን አሜሪካ – “Dr. Nabaro” ከእንግሊዝ ይልቅ ስፔናዊ ወይም ፖርቹጋላዊ ቢሆኑ ኖሮ የላቲን አሜሩካ ሀገራትን ድጋፍ የማግኘት እድሉ ከፍተኛ ይሆን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሦስተኛ ተራ ቁጥር ላይ በተጠቀሰው ምክንያት፣ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ሌላ የኢሲያ ተወካይ በድጋሜ እንዲመረጥ ድምፃቸውን ለፓኪስታናዊቷ “Nishtar” አይሰጡም። ስለዚህ፣ በላቲን አሜሪካ ሀገራት ዘንድም ቢሆን ዶ/ር ቴድሮስ የመመረጥ እድላቸው ከሁለቱም ተወዳዳሪዎች የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ዶ/ር ቴድሮስ ከሦስቱም ተወዳዳሪዎች የላቀ የማሸነፍ እድል እንደነበራቸው እሙን ነው። ስለዚህ፣ ለዶ/ሩ ፈታኝ የነበረው የሌሎች ሀገራትን ድጋፍ ማግኘቱ አልነበረም። ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የውድድር ስልት በላይ ለዶ/ር ቴድሮስ ትልቅ ፈተና የነበረው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የጋጠማቸው ተቃውሞ ነው።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የድምፅ አሰጣጡ ከግለሰብ ይልቅ በሀገራት ዲፐሎማሳዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ፋይዳ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ዶ/ር ቴድሮስ በማህበራዊ ሚዲያዊች አማካኝነት የገጠማቸው ተቃውሞ በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ውስን ነው። ነገር ግን፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ምን ያህል ጉልህ እየሆነ እንደመጣ በግልፅ ያሳያል። በአጠቃላይ፣ የምርጫ ሂደቱ ማህበራዊ ሚዲያዎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማህብረሰቡን በንቃት በማሳተፍና ንቅናቄ መፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በግልፅ አሳይቶናል።

ያልተዘጋ እሰር ቤት ውስጥ ነፃነት ያስፈራል!

ከእስር ቤት የወጣሁ ሰሞን ወደ አንድ ባለሱቅ ደበኛዬ ጋር ስሄድ “እንኳን ለቤትህ አበቃህ….” እያለ አገላብጦ ከሳመኝ በኋላ “እኛ እኮ ‘እንትን’ ትመስለን ነበር” አለኝ። “‘እንትን’ ማለት ምን?” አልኩት። ፈራ-ተባ እያለ “እኛ እኮ የመንግስት ጆሮ-ጠቢ፥ ሰላይ ትመስለን ነበር” ሲለኝ ክት ብዬ ሳቅኩ። እንዲህ ማሰቡ በራሱ በጣም ገረመኝና “ያምሃል እንዴ? እስኪ አሁን እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” አልኩትና መልሱን ሳልጠብቅ ሄድኩ።

ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ከእኔ ጋር የአብሮነት ቆይታ ካላቸው ጓደኞቼ ጋር እየተጨዋወትን ሳለ ከመሃላቸው አንዱ “አይ ስዬ…እኔ እኮ ከእነሱ ጋር ትመስለኝ ነበር?” አለኝ። የረጅም ግዜ ጓደኛህ እንዲህ በጥርጣሬ ዓይን እያየህ መቆየቱን ስታውቅ የሆነ በቃ ያበሳጫል። “እንዴ… አንተ እንዴት ነው እንዲህ የምታስበው?” አልኩትና ወደ ሌሎቹ ዞሬ “ቆይ አንዴ ሁላችሁም…” ስል የሁሉም ትኩረት እኔ ላይ ሆነ። ከዚያ “ቆይ ከእናንተ ውስጥ ‘ስዬ ሰላይ ነው’ ብሎ የሚያስብ ነበረ?” እላቸዋለሁ ሁሉም በአንድ ድምፅ “አዎ!” አሉኝ።

ምላሻቸው ከማስገረም አልፎ አስደነገጠኝ። በለሆሳስ “ቆይ እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” ብዬ በውስጤ ማሰላሰል ስጀምር ከጎኔ የነበረው ጓደኛዬ “ቆይ ስዬ…አንተ ራስህ፣ ይህን ያህል ዓመት በነፃነት የፈለከውን እየተናገርክና እየፃፍክ ስትኖር ‘አለመፍራትህ በራሱ ሌላን ሰው አያስፈራም?’ እንደዛ በነፃነት ስትናገርና ስትፅፍ ሁላችንም ‘በቃ… ከኋላው የሆነ ነገር ቢኖር ነው’ ብለን አሰብን። ይሄ’ኮ አንተ የተለየ ነገር ስላደረክ ወይም ከሌሎቻችን በተለየ አንተን አለማመን አይደለም። እንደዛ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ከሁላችንም በተለየ አንተ ብቻ “ነፃ” ስትሆን አያስጠረጥርም ልትለኝ ነው?”

ይህ ከሆነ አምስት ወራት አለፉ። ነገር ግን፣ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስለኝ ነበር” የምትለዋ ጥያቄ ቀጥላለች። ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ቤት እየሄድኩ ሳለ አንድ መስፍን የሚባል ጓደኛዬ አገኘኝና “ስዬ…ድሮ እኮ እንፈራህ ነበር” አለኝ። “ለምን?” እለዋለሁ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስ…” አላስጨረስኩትም! ወደ ቤት እንደገባሁ ይህን ፅሁፍ መፃፍ ጀመርኩ።

በመጀመሪያ ደረጃ ያለኝ ፖለቲካ አቋምና አመለካከት ትክክለኝነቱ የሚረጋገጠው በየእለቱ በማንፀባርቀው ሃሳብና በምሰራው ሥራ ሳይሆን በመታሰሬ መሆኑ በራሱ ያበሳጫል። ነገር ግን፣ ለራሱ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ “ባልተዘጋ እስር ቤት” ውስጥ እየኖረ እንደ እኔ “ታስሮ ለተፈታ” ሰው ከንፈሩን ሲመጥ ማየት በጣም ይገርማል። ኧረ እንደውም ከማስገረም አልፎ አንዳንዴ እንደ እብድ ለብቻ ያስቃል።

“‘እንትን’ ትመስለን ነበር” ሲሉ “ሰላይ ወይም የመንግስት ጆሮ-ጠቢ” ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። ጥያቄው በጓደኞቼ ውስጥ የነበረውን ስጋትና ፍርሃት ያስከተለው ጥርጣሬን ያሳያል። እኔን የጠረጠሩበት ምክንያት ከሌሎች በተለየ መልኩ ሃሳብና አመለካከቴን በነፃነት በመግለፄ ነው። በእርግጥ ሁላችንም የራሳችንን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ እንሻለን። እንዲህ ያለ ነፃነት ለእስርና እንግልት እንደሚዳርግ ደግሞ እናውቃለን። ስለዚህ፣ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት የሚገልጽ ሰው እንደሚታሰር ይጠብቃሉ። ካልታሰረ ደግሞ “‘እንትን’ ቢሆን ነው” ብለው ይጠረጥራሉ።

ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈሩት ሆነ የሌሎችን ነፃነት የሚጠራጠሩት መንግስትን ስለሚፈሩ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Montesquieu” አገላለፅ፣ መንግስት የተፈጠረበት መሰረታዊ ዓላማ ዜጎች እርስ-በእርስ አንዳይፈራሩ ነው፡-

“The political liberty of the subject is a tranquility of mind arising from the opinion each person has of his safety. In order to have this liberty, it is requisite the government be so constituted as one man need not be afraid of another.” Baron de Montesquieu, The Spirit of Laws, trans. Thomas Nugent, 2 vols. (New York: The Colonial Press, 1899), 1:151–162.

የመንግስት ሥራና ተግባር ዜጎች እርስ-በእርስ ሳይፈራሩ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት አንዲገልፁ ማስቻል ነው። ሆኖም ግን፣ በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ዜጎች የራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ ይቅርና የጥቂቶች ነፃነት ብዙሃኑን ለስጋትና ጥርጣሬ እየዳረገው ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የተፈጠረበትን መሰረታዊ ዓላማ ስለሳተ ነው። መንግስታዊ ሥርዓቱ የዜጎችን መብትና ነፃነት ከማስከበር ይልቅ መንግስትን ሕዝቡን የሚፈራና ሕዝቡም እርስ-በእርስ እንዲፈራራ የሚያደርግ ስለሆነ ነው። በመሰረቱ ፍርሃት ለፍፁም አምባገነናዊ መንግስት የተግባር መመሪያና መርህ ነው፡-

“In a tyranny, the moving and guiding principle of action is fear. Fear in a tyranny is not only the subjects’ fear of the tyrant, but the tyrant’s fear of his subjects as well. [It] is not merely a psychological motive, but the very criteria according to which all public life is led and judged.”  On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding

በዚህ መሰረት፣ መንግስትን በመፍራት ሆነ በመጠራጠር፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ከመግለፅ የሚቆጠቡ ሰዎች በሙሉ በፍርሃት መርህና መመሪያ መሰረት ለሚመራው ሥርዓት ተገዢዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስርዓቱን በስልጣን ላይ ለማቆየት የመሚያስፈልገውን ፍርሃት እየለገሱ ስለሆነ እንደ ቀንደኛ ደጋፊ መታየት አለባቸው።

ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ሌሎች በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት የሚዳረጉት በራሳቸው ያጠፉት ጥፋት ወይም የፈፀሙት ወንጀል ስላለ አይደለም። የአምባገነናዊ መንግስት ዓላማም እነሱን በማሰቃየትና በማስፈራራት ወደፊት ለሥርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደ እነሱ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ እንዳይሞክር ለማስፈራራት ነው።

ብዙ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እስር ቤት ውስጥ የተዘጋባቸው ከእስር ቤት ሲወጡ ነፃነታቸውን ስለሚቀዳጁ ነው። በዚህም፣ ከእስር ቤት ውጪ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ስለሚገልፁና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደነሱ ነፃነቱን እንዲቀዳጁ ፈር-ስለሚቀዱ ለእስር ይዳረጋሉ። ምክንያቱም፣ እነዚህ ሰዎች ነፃነታቸውን የሚያጡት እስር ቤት ሲገቡ ብቻ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ከእስር ቤት ውጪ ሀኖ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለን ሰው ማሰርና ማሰቃየት አስፈላጊ አይደለም። በመኖሪያ ቤቱ እና በስራ ቦታ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ የሚፈራ ሰው ባልተዘጋ እስር ቤት ውስጥ ራሱን ያሰረ ስለሆነ ድጋሜ ማሰር አያስፈልግም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ፍርሃትን ማስፈን ለሚሻ ስርዓት ፈሪዎች ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በተደጋጋሚ የሚታሰሩት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ሃሳብና አመለካከቱን ለመግለፅ፣ መብትና ነፃነቱን በይፋ ለመጠየቅ ስለሚፈራ ነው። ስለዚህ፣ እነሱ የሚታሰሩት ሌሎችን ካልተዘጋው እስር ቤት ነፃ ለማውጣት ሲሞክሩ ነው። 

የብሔር ፖለቲካ ጡዘት ከሰውነት እስከ አውሬነት ያደርሳል!

የሌላ ሀገር ዜጋን እየወደድን የሌላ ብሔር ተወላጅን እንጠላለን!

እስኪ አንድ ኢትዮጲያዊን ዝም ብላችሁ ታዘቡት። ወደ ቤተ-እምነት ሲሄድ “የሰው-ልጅ በአምላክ አምሳል የተፈጠረ ነው። ሰዎች እርስ-በእርስ ተዋደዱ፣ ጠላትህን እንደ ራስህ ውደድ፣…ወዘተ” የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮት “አሜን” ይቀበላል። ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ደግሞ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት ይማራል። በሁሉም የትምህርት ደረጃ የታሪክና የሲቪክ መማሪያ መፅሃፍት ውስጥ በጥቁር-አሜሪካዊያን ላይ ስለደረሰው ባርነትና የጉልበት ብዝበዛ፣ በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት በጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ላይ ስለተፈፀመው የዘር መድሎና ጭቆና፣…ወዘተ በሰፊው ያስተምራሉ። የግል ሆነ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት ዘወትር “ዘር-ቀለም ሳንለይል…” እያሉ ዘወትር ይዘምራሉ።

አብዛኛው ኢትዮጲያዊ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የቀድሞ ታሪክ ወይም ወቅታዊ ፖለቲካ በሰዎች ላይ ስለሚፈፀም የዘረኝነት መድልዎና መገለል፣ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና፣ ፖለቲካዊ እስራትና ግድያ፣…ወዘተ በየሚዲያው ይሰማል፣ በየትምህርት ቤቱ ይማራል፣ እርስ-በእርሱ ይወያያል፣ በጋራ ያወግዛል። በጦርነቶች ወይም በሽብር ጥቃቶች በሰዎች ላይ የሞትና አካል ጉዳቶች ሲደርሱ ሰብዓዊ ርህራሄ ይሰማዋል። ከማንም ቀድሞ ለተጎዱ ወገኖች የተሰማውን “ጥልቅ ሃዘን” በይፋ ይገልፃል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ በሀገሪቱ የቀድሞ ታሪክ ወይም በወቅታዊ ፖለቲካ አማካኝነት በዜጎች ላይ ስለተፈፀሙ በደሎች፣ ጭቆናዎች፣ አድልዎች፣ ግድያና እስራቶች ከቤተሰብ ወይም ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር በግልፅ ይነጋገራል፥ ይወያያል፣ ይግባባል። በሌሎች ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ታሪካዊና ፖለቲካዊ በደሎችና ጭቆናዎች በቤተሰቡ አባላት ወይም በወዳጆቹ ላይ እንዲፈፀም አይሻም።

እስካሁን ድረስ እንደተመለከትነው፣ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ለእሱ ቅርብ ከሆኑት የቤተሰብ አባላት ወይም ወዳጆች እና ሩቅ ካሉት የሌላ ሀገር ዜጎች ጋር ያለው ግንኙነትና አመለካከት በዋናነት በበጎ አመለካከትና በሰብዓዊነት የታነፀ ነው። ነገር ግን፣ ስለ ራሱ ሀገር የቀድሞ ታሪክና ወቅታዊ ፖለቲካ ውይይት ሲጀምር በአንድ ግዜ አቅሉን ይስታል። ስለኢትዮጲያ የቀድሞ ታሪክ ሆነ አሁን ስላለው ፖለቲካዊ ስርዓት የሚደረገው ውይይት ወዲያው “አማራ፣ ኦሮሞ፣ “ትግሬ”፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ሱማሌ፣….” እየተባባሉ መደናቆር ይጀመራል።

ታሪካዊ በደልና ጭቆና ወይም ፖለቲካዊ እስራትና ሞት በሌላ ሀገር ዜጋ ወይም በቤተሰባችን አባል ላይ ሲደርስ የነበረን ሰብዓዊነት እዚሁ ለሌላ ብሔር ተወላጅ የሀገራችን ዜጎች ሲሆን ከውስጣችን እንደ ጉም በኖ ይጠፋል። ለውጪ ሀገር ዜጋ የነበረን ሰብዓዊ አመለካከት ለሌላ ብሄር ተወላጅ ሲሆን ወደ ፖለቲካ ይቀየራል።

ለምሳሌ፣ ባለፈው አመት አንድ ወዳጄ “በጎንደር የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ከመኖሪያ ቄያቸው ተፈናቀሉ” በሚል አምርሮ ሲቃወም ነበር። በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት መሰረት በአማራ፣ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል ከአራት ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ 669 ሰዎች መገደላቸው ስነግረው “እነዚህ ፋብሪካ ለማቃጠል የወጡ ወንጀለኞች ናቸው” አለኝ። ይሄው ሰው ግን፣ ባለፈው በለንደን ከተማ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት አንዲት የፓርላማ አባል መገደሏን እንደሰማ ጥቃቱን በማውገዝ ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ሲገልፅ ማንም አልቀደመውም። ታዲያ ይህ ወዳጄ ለውጪ ሀገር ዜጋ የነበረውን ሰብዓዊ አመለካከት ለሌላ ብሔር ተወላጅ ሲሆን በአንዴ ወደ ፖለቲካ ለምን ቀየረ?

በተመሣሣይ ስለ ሀገራችን የቀድሞ ታሪክና ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ከውጪ ሀገር ዜጎች ጋር መወያያት እየቻልን የሌላ ብሔር ተወላጅ ከሆነ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ጋር ግን መግባባት ቀርቶ መደማመጥ አንኳን አይቻልም። ለምሳሌ፣ ባለፈው ሳምንት ከአንድ ኢጣሊያናዊትና ኤርትራዊት ጋር ለመወያያት እድሉ ገጥሞኝ ነበር። ከኢጣላናዊቷ ጋር ስለ አደዋ ጦርነትና አፄ ሚኒሊክ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ውይይት አድረገን። በተመሣሣይ፣ ከኤርትራዊቷ ጋር በኤርትራና በኢትዮጲያ ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በግልፅ ተወያየን። ወደ ሀገሬ ስመጣ ግን ስለ ኢትዮጲያ የቀድሞ ታሪክ ሆነ ስለ ወቅታዊ ፖለቲካ በግልፅ መወያያት አይቻልም። ስለ አደዋና አፄ ሚኒሊክ ከኢጣሊያን ዜጋ ጋር መወያያት ከቻልኩ ከአንድ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ጋር መወያያትና መግባባት የሚሳነኝ ለምንድነው? ከኤርትራዊቷ ጋር ያደረኩትን ግልፅ ውይይት ከአንድ የትግራይ ተወላጅ ጋር ማድረግ የሚከብደኝ ለምንድነው? ከሌላ ሀገር ዜጋ የነበረን ግልፅ ውይይት ከሌላ ብሔር ተወላጅ ጋር ሲሆን በጭፍን ጥላቻ መደናቆር የሚሆነው ለምንድነው?

በአጠቃላይ፣ ከሌላ ሀገር ዜጋ ጋር በግልፅ እየተወያየን ከሌላ ብሔር ተወላጅ ጋር እንኮራረፋለን። ለሌላ ሀገር ዜጋ የነበረን ስብዓዊነት ለሌላ ብሔር ተወላጅ ሲሆን ፖለቲካ ይሆናል። የሌላ ሀገር ዜጋን እየወደድን የሌላ ብሔር ተወላጅን እንጠላለን። በቤተሰባችን አባላት ላይ ቀርቶ በሌላ ሀገር ዜጋ ላይ እንኳን እንዲደርስ የማንፈልገውን መጥፎ ነገር በሌላ ብሔር ተወላጅ ላይ ለማድረስ እንዝታለን። ለመሆኑ ለኢትዮጲያዊ ከሌላ ሀገር ዜጋ እና ከሀገሩ ልጅ ማን ይቀርበዋል?

የ“እኛ” እና “እነሱ” ፖለቲካ፡ ከሰብዓዊነት እስከ አውሬነት

የሰው-ልጅ እርስ-በእርሱ የሚያደርገው ማህበራዊ ግንኙነት እና አንቅስቃሴ በዋናነት “እኛ” እና “እነሱ” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በቋንቋ አጠቃቀማችን እና ትምህርት አሰጣጣችን መሰረት እያንዳንዱ ሰው ራሱን “እኛ” በሚል የቡድን እሳቤ ውስጥ ነው የሚመለከተው። ሌሎችን ደግሞ “እነሱ” በሚል የተፃራሪ ቡድን አባል አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ አለ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ እንደ ሁኔታ የሚለያይ ነው። ለምሳሌ፣ “እኛ” ኢትዮጲያዊያን ከሆንን “እነሱ” ኢጣሊያዊያን፣ እንግሊዛዊያን፣ ኤርትራዊያን፣…ወዘተ፤ “እኛ” ኦሮሞ ከሆንን “እነሱ” አማራ፣ “ትግሬ”፣ ጉራጌ፣…ወዘተ፤ “እኛ” የአበበ ቤተሰቦች ከሆንን “እነሱ” የጫላ ቤተሰቦች፣ የሃጎስ ቤተሰቦች፣…ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። በአጠቃላይ፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለውን እሳቤ እንደ ሁኔታው በቤተሰብ፣ ብሔርና ሀገር ደረጃ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።

በሦስቱም ደረጃ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው አመለካከት የሚወሰነው በመካከላችን ካለው ግንኙነት አንፃር ነው። በዚህ መሰረት፣ ለአንድ ኢትዮጲያዊ የኢጣሊያኖችን ሃሳብና እንቅስቃሴ ማወቅና መገመት ከባድ ነው። ነገር ግን፣ የሁለቱ ሀገር ዜጎች በኢትዮጲያዊው ማህበራዊ ሕይወትና የዕለት-ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ውስን ነው። የኦሮሞዎች ሕይወት ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሃሳብና እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ስለ አማራ፣ ትግራይ ወይም ጉራጌ ብሔር ተወላጆች ሃሳብና እንቅስቃሴ ማወቅና መገመት ይፈልጋል። ይሁን እንጂ፣ ሁሉም የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ከማንም በፊት የቤተሰቡንና የቅርብ ወዳጆቹን ሃሳብና እንቅስቃሴ በትክክል ማወቅና መገመት አለበት።

እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ በሕይወቱ ውስጥ ቀጥተኛ ግንኘነትና ተፅዕኖ ስላላቸው ቤተሰቦቹና የቅርብ ወዳጆቹ ሃሳብና እንቅስቃሴ በእርግጠኝነት ማወቅ ይችላል። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ የቤተሰቡ አባላት ወይም የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት “እነሱዎች” ጋር በቃላሉ መነጋገርና መግባባት ይችላል። ማህበራዊ ግንኙነቱም በውይይትና ሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ ይሆናል። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ስለ ሌላ ሀገር ዜጎች ሃሳብና እንቅስቃሴ በእርግጠኝነት ማወቅ አይችልም። ይሁን እንጂ፣ የውጪ ሀገር ዜጎች ከእሱ ጋር ያላቸው ግንኙነትና በዕለት-ከእለት ሕይወቱ ውስጥ ያላቸው ተፅዕኖ ውስን ነው። ስለዚህ፣ ሩቅ ያሉ የሌላ ሀገር ዜጎች “እነሱዎች” ጥሩ ሥራና ምግባር እንዳላቸው ይገምታል።

“Edmund Leach” የተባለው ምሁር፣ ቅርብ ባሉት “እነሱዎች” እና ሩቅ ባሉት “እነሱዎች” መካከል ሌላ ሦስተኛ “እነሱዎች” እንዳሉ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ብዙውን ግዜ ሰዎች ስለ ከሦስተኛው “እነሱዎች” ጋር ያላቸው ግንኙነት በውይይት ላይ ያልተመሰረተና ለሌሎች ያላቸው አመለካከት ሰብዓዊነት የጎደለው ነው፡-

“But lying in between the remote Heavenly other and the close predictable other there is a third category which arouses quite a different kind of emotion. This is the other which is close at hand but unreliable. If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” REITH LECTURES 1967: A Runaway World, Lecture 3: Ourselves and Others: 26 November 1967 – Radio 4

ከውጪ ሀገር ዜጋ ጋር በግልፅ መወያየትና መግባባት እንችላለን። ከእነሱ ጋር መወያየትና መግባባት ባንችል እንኳን የእነሱ ሃሳብና እንቅስቃሴ በእኛ ሕይወት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ዝቅተኛ ስለሆነ ይህን ያህል አሳሳቢ አይደለም። ሆኖም ግን፣ በአንድ ሀገር ውስጥ አብረን እየኖርን እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ከተሳነን፤ የጠበቀ ማህበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እያለን አንዳችን የሌላችንን ሃሳብና እንቅስቃሴ ማወቅና መገመት ከተሳነን፣ እንደ ሰው ያለን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ አመለካከታችን ከውስጣችን ይጠፋል። ከቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን፣ ከጎጥ፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል ነዋሪዎች ጋራ የነበረን በውይይትና ምክንያታዊ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ አመለካከት፣ እንደ ሰው የነበረው ሰብዓዊነት ለሌላ ክልል ነዋሪዎች ወይም ብሔር ተወላጆች ሲሆን ከውስጣችን ተሟጥጦ ይጠፋል።

የሌላ ሀገር ዜጋን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያየ፣ የሌላ ብሔር ተወላጅን ግን እንደ ዱር አውሬ አድኖ መግደል ይሻል። በእርግጥ ለአንዳንዶቻችሁ አገላለፁ በጣም የተጋነነ ሊመስላችሁ ይችላል። ነገር ግን፣ የራሱን ዝርያ እንደ አውሬ ወይም ጠላት አድኖ የሚገድል ፍጡር ቢኖር የሰው ልጅ ብቻ ነው። በጣም ውስን በሆኑ አጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ሌሎች እንስሳት የሚያድኑትና የሚገድሉት ሌላ የእንስሳት ዝርያን ነው። እንደ “Edmund Leach” አገላለፅ፣ የራሱን ዝርያ እንደ አውሬ ማደንና መግደል የሚሻው የሰው-ልጅ ብቻ ሲሆን ይህም በዋናነት በቃላት ላይ የተመሰረተ የመግባቢያ ቋንቋ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡-

“…our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. In the non-human world whole species function as a unity. Wolves do not kill each other because all wolves behave the same language. If one wolf attacks another wolf, the victim automatically responds with a gesture which compels the aggressor to stop. … The complication in our own case is that if a human victim is to be safe, the attacker and the attacked must not only behave the same language, they must speak the same language, and be familiar with the same code of cultural symbols. And even then each individual can make his own decision about what constitutes ‘the same language’.’’ REITH LECTURES 1967: A Runaway World, Lecture 3: Ourselves and Others: 26 November 1967 – Radio 4

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ እንደተገፀው፣ የብሔር ፖለቲካ የአንዱን ወይም የሌላን ብሔር እኩልነት በማረጋገጥ ላይ ብቻ የሚቆም አይደለም። የሰው-ልጅን ምክንያታዊ አስተሳሰብና ሰብዓዊነት ከላዩ ላይ ገፍፎ የሚወስድ፣ የአንዱን ብሔር ሕልውና ለማረጋገጥ በሚል የሌላውን ብሔር ሕልውና እስከማሳጣት የሚደርስ ነው። አጉል ብሔርተኝነት የሰው ልጅን ባህሪ ከሰብዓዊነት ወደ ተራ እንስሳነት ይቀይረዋል። ከሁሉም እንስሳት በተለየ ሰዎችን እንደ የዱር አውሬ እያደነ የሚገድል ጨካኝ ፍጡር ያደርገዋል። በታዝማኒያዎች (Tasmanians) እና በአይሁዶች ላይ የፈፀመው የዘር-ማጥፋት፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የአፓርቲይድ አገዛዝ በጥቁሮች ላይ የተፈፀመው አድሎና በደል፣… ሁሉም የሌላ ብሔር ተወላጆችን እንደ ሌላ ዓይነት ፍጥረት አድርጎ በብዙሃን አዕምሮ ውስጥ በመሳልና፣ ለታሪካዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እነሱን ተጠያቂ በማድረግ የተፈፀሙ ናቸው።

በአንድ ሀገር ውስጥ አብረው እየኖሩ የማይነጋገሩ፣ ከወደፊት የተስፋ ይልቅ የታሪክ ጠባሳዎችን በመዘከር፣ በጋራ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸው ዙሪያ ከመወያየት ይልቅ በመፈራራት፣ በአጠቃላይ እርስ-በእርስ ተነጋግሮ ከመተማመን ይልቅ በጥርጣሬ አይን በመተያየት ላይ የተመሰረተው ብሔራዊ አንድነት መጨረሻው እንጥርጥሮስ ነው።

አምባገነኖች የሚጠሉትና የሚፈሩት እውነትን ነው!

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኒጄር፥ ኒያሜ ከተማ በአፍርካ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የተለያዩ ሰብሰባዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ከ28 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ተሳታፊ ሆነዋል። እኔም በቦታው የተገኘሁት በአፍሪካ ስላለው የኢንተርኔት ነፃነት፡ “Internet Freedom in Africa” በሚል ርዕስ ያለኝን ልምድና ተሞክሮ እንዳካፍል ተጋብዤ ነበር። ዩጋንዳዊው “ፔፔ” እና ኬኒያዊቷ “ሳሎሜ” እንደ እኔ በፓናል ውይይቱ ላይ ልምድና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

በመጀመሪያ በሀገሩ ስላለው የኢንተርኔት አጠቃቀምና ነፃነት ሁኔታ እንዲናገር እንደል የተሰጠው “ፔፔ” ነበር። “ፔፔ” በቀላሉ ከሰው ጋር መግባባት የሚችልና ጨዋታ አዋቂ ነው። በሀገሩ ዩጋንዳ የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በዚህም የላቀ ዕውቅና የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውለታል። በውይይቱ ወቅት የኢንተርኔት ነፃነትን ከግል ሕይወቱ ጋር አቆራኝቶ ያቀረበበት ሁኔታ ደግሞ እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር። “እኔና ጓደኞቼ” ይላል ፔፔ፡- 

“ እኔና ጓደኞቼ ከካምፓስ ከተመረቅን በኋላ በአመት አንዴ የመገናኘት ልማድ አለን። ያው እኔ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ስለምሰራ መንግስት ከብዙ ሰዎች ጋር እንድገናኝ አይፈልግም። …አመፅና ሁከት የምቀሰቅስ ስለሚመስላቸው በተደጋጋሚ ያስሩኛል። እስካሁን ድረስ ከስድስት ግዜ በላይ አስረውኛል። አንድ ቀን ታዲያ ከካምፓስ ጓደኞቼ ጋር አንድ ላይ ተሰብስበን እየተወያየን ሳለ ፖሊሶች በሩን በኃይል በርግደው ገቡ። በዚህ ቅፅበት በቲዊተር (Twitter) ገፄ ላይ “Arrested” ብዬ ፃፍኩ። በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ዲፐሎማቶች ይህን ፅሁፍ እንዳዩ እኔን ለማስፈታት በየፊናቸው መሯሯጥ ጀመሩ …

ከፖሊስ አዛዡ “በአስቸኳይ ይፈታ” የሚለውን መልዕክት ይዞ የመጣው ፖሊስ በሩን ሲያንኳኳ በታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ሁለት ፖሊሶች እጅግ ፀያፍ ተግባር ሊፈፅሙብኝ እየተዘጋጁ ነበር። በግልፅ ልንገራችሁ፤ አንዱ ፖሊስ የውስጥ ሱሪዬን እያወለቀ ነበር፣ ሌላኛው ፖሊስ ደግሞ “he was erecting…” አዎ…በቲውተር ገፄ ላይ የፀፍኳት አንዲት ቃል በግብረ-ሰዶም ፖሊሶች ሊፈፀምብኝ ከነበረው የአስገድዶ መድፈር ታድጋኛለች። ጥቃቱ ተፈፅሞብኝ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ከፊታችሁ ቆሜ ለመናገር የሚያችል የራስ መተማመን አይኖረኝም። በእርግጠኝነት አሁን ያለኝን ስብዕናና የራስ መተማመን ያሳጣኝ ነበር…”

“ፔፔ” ላይ ከደረሰው በደልና ስቃይ አንፃር የእኔ በጣም ቀላል እንደሆነ ተሰማኝ። እኔን በጣም የገረመኝ፣ የትም ሀገር ቢሆን የአምባገነን መንግስታት ሥራና ተግባር አንድና ተመሣሣይ ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁ ሰዎችን ያስራሉ፥ ይደበድባሉ፥ ያሰቃያሉ፥ ይገድላሉ፥…ወዘተ። እነዚህን አምባገነን መንግስታት ከፊል እና ፍፁም በማለት ለሁለት ክፍሎ ማየት ይቻላል።  

ከፊል አምባገነን የሆኑ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦትንና ተጠቃሚዎቹን መቆጣጠር የሚሹት ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚደብቁት ነገር ስላለ ነው። የተዝረከረከ የመንግስት የአሰራር ግድፈቶችን፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ማጭበርበሮችን፣ እንደ ሙስና ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን ወይም ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮችን ከማህብረሰቡ መደብቅ ይሻሉ። ስለዚህ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት እነዚህን ችግሮች የሚያጋልጡ ሰዎችን ብዙ ግዜ ያስፈራራሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ ያስራሉ።

ከላይ በተተቀሰው የውይይት መድረክ ተሳታፊ የነበረችው ኬኒያዊቷ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ “ሳሎሜ” በኬኒያ ስላለው የኢንተርኔት ነፃነት የሰጠችው አስተያየት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። “ሳሎሜ” ቅድሚያ የሰጠችው በቀጣዩ አመት በኬኒያ ስለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ነበር። የኬኒያ መንግስት ጎረቤት ዩጋንዳን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፣ በምርጫ ወቅት አመፅና ብጥብጥን ለመከላከል በሚል የኢነተርኔት አገልግሎትን ሊዘጋ እንደሚችል ስጋቷን ገልፃለች።

ፍፁም አምባገነን የሆኑ መንግስታት ግን የኢንተርኔት አገልግሎትን ከማቋረጥና መከታተል አልፎ-ተርፎ ተጠቃሚዎቹን ከማስፈራራት፥ ማሰርና መደብደብ እስከ መግደል ሊደርሱ ይችላሉ። የኢንተርኔት ግንኙነት መረቡን በከፊል ሳይሆን ሙሉ-ለሙሉ መቆጣጠር ይሻሉ። የተወሰኑ ሰዎችን ሳይሆን ሁሉም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለመከታተል ይሞክራሉ። ምክንያቱም፣ ፍፁም አምባገነን የሆኑ መንግስታት እንዳይታወቅ የሚሹት የፈፀሙትን ስህተት ወይም ለሕዝብ የተናገሩትን ውሸት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በእውን የሚያውቀውን እውነት ለመደበቅ ይጥራሉ።

ለምሳሌ፣ እኔ በማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ወንጀል” ተከስሼ ለ82 ቀን ታስሬያለሁ። ሰብዓዊ ክብሬንና ስብዕናዬን በሚነካ መልኩ ተደብድቤያለሁ፥ ተሰድቤያለሁ። ነገር ግን፣ ስለተፈፀመብኝ በደልና ጭቆና እንኳን በነፃነት ለመናገርና ለመፃፍ እንኳን ያስፈራኛል። ምክንያቱም፣ በእኔ ላይ በእውን የፈፀሙብኝን ነገር ሌሎች በምናብ እንኳን እንዳያውቁት ይፈልጋሉ። አንተ በእውን ስለሆንከው ወይም በገሃደድ ስለምታውቀው ነገር በግልጽ መናገርና መፃፍ በራሱ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ወንጀል” በሚል ዳግም ሊያስከስስ ይችላል።

በአጠቃላይ፣ አምባገነኖች ከምንም በላይ የሚጠሉትና የሚፈሩት እውነትን ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት የእነሱን ውሸት አጋለጥክ ወይም በእውን የምታውቀውን ፃፍክ፣ ዞሮ-ዞሮ ያው እነሱ የሚጠሉትን ተግባር ፈፅመሃልና በሄድክበት መውጫና መግቢያ ያሳጡሃል። ስለዚህ፣ ወይ እነሱን ፍርተህ ትኖራለህ፣ አሊያም ያመንክበትን አድርገህ የሚመጣውን ትቀበላለህ።

ከዮናታን ተስፋዬ የባሰ “አሸባሪ” ከቶ ከወደየት ይገኛል?

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ በተከሰሰበት የሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል። በዮናታን የተከሰሰው “በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም አንቀፅ(4) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ” ነው። በዚህም የኦነግ ዓላማን ለማሳካት አመፅና ብጥብጥ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በፌስቡክ ገፁ ላይ በሚወጣቸው ፅሁፎች የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር እና ማነሳሳት ወንጀል ተከሷል። በማስረጃነት የቀረበው ከሕዳር 24/2008 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 11/2008 ዓ.ም ባሉት ቀናት በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣቸው ፅሁፎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በ2ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሰው እንዲህ ይላል፡-
“በቀን 11/04/08 ዓ/ም (ዲሰምበር 21 2015 4፡32 AM) ከቀኑ 10፡32 በሚጠቀምበት ፌስቡክ ‘ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም የለውም’ በሚል ከፃፈው ፅሁፍ ውስጥ ‘አምና ከ40 በላይ የኦሮሞ ተማሪዎችን ገደሎ ችግር የፈታ የመሰለው ኢህአዴግ ዘንድሮም ከአምናው ሳይማር ዜጎችን በመግደል ችግሩን ለመፍታት እየጣረ ነው። በቀና መንገድ ችግር ከመፍታት አፈና ምላሽ ሆኗልና ወደ የማይቀረው አመፅ እየተንደረደርን መሆኑን የሰሞኑ ተቃውሞና የገጠመው ምላሽ ከበቂ በላይ አስረጂ ነው’ የሚል ቀስቃሽ የሆነ ፅሁፍ በመፃፍ ሌሎችን እንዲነሳሱ በማድረጉ” አቃቤ ሕግ ለፌዴራል ክፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ካቀረበው የክስ ቻርጅ ውስጥ የተወሰደ

ታዲያ ይህ ፅሁፍ እንዴት ሆኖ ዮናታን በተከሰሰበት የሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል? በእርግጥ ለዚህ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በክስ ቻርጁ የተጠቀሱ ፅሁፎችን አንድ-በአንድ ብንመለከት “ይሄ እንዴት ፅሁፍ የሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል?” እያላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይሁን እንጂ፣ በሕግ መሠረት ለአንዱም ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አታገኙም። በእርግጥ ጥያቄው መልስ-አልባ ሆኖ ሳይሆን የተሳሳተ ስለሆነ ነው። ለተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ጥያቄውን ማስተካከል ነው። ለምሳሌ፣ ከላይ የተጠቀሰው ፅሁፍ “እንዴት በሽብር ወንጀል ተከሳሽ ላይ ማስረጃ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል?’ ብሎ መጠየቅ ስህተት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ “ከሳሽ ወይም መንግስት ለምን በዚህ ፅሁፍ ተሸበረ?” በሚል መስተካከል አለበት።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠበትን አግባብ በጥሞና ሲከታተል ለነበረ ሰው “ኢህአዴግ ችግርን ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም የለውም” የሚለው ፅሁፍ ይዘት ሙሉ-በሙሉ “እውነት” እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው። በተለይ በአምቦ ከተማ በተፈጠረው ችግር ተማሪዎች መገደላቸው የማይካድ ሃቅ ነው። በሕዳር 2008 ዓ.ም የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴው እንደገና ሲቀሰቀስ የኢህአዴግ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ ችግሩን በቀና መንገድ ከመፍታት ይልቅ በኃይል ለማፈን በመሞከሩ ሀገሪቷን ለከፍተኛ አመፅና አለመረጋጋት ዳርጏታል። በዚህ ምክንያት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን፣ ብዙ ሺህዎችን ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውንና ከመኖሪያ ቄያቸው መፈናቀላቸውን፣ እንዲሁም በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብና የመንግስት ንብረት መውደሙን ማንም አያስተባብልም። ሌላው ቀርቶ ዮናታንን የከሰሰው መንግስት እንኳን ይህን ሃቅ ሊያስተባብል አይችልም።

ታዲያ የዮናታን ፅሁፍ ሙሉ በሙሉ የማይካድ ሃቅ ሆኖ ሳለ ፀኃፊው በሽብር ወንጀል የተከሰሰው ለምንድነው? ፀኃፊው “በሌላ ዓይነት የሽብር ድርጊት ተሰማርቶ ነበር” ቢባል እንኳን ይህን ፅሁፍ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ ስለዚህ፣ ተከሳሽ፥ ዮናታን ተስፋዬ የፈፀመው የወንጀል ተግባር በተጠቀሰው ፅሁፍ እውነትን በትክክል መግለፁ ነው። በከሳሽ፥ የኢህአዴግ መንግስት ላይ የደረሰው ጉዳት ደግሞ እውነት እንዲያውቅ መደረጉ ነው።

በመሰረቱ፣ እውነታን ከሌሎች መደበቅ በሚሹ ዘንድ ስላለፈው፣ ስለአሁኑ ወይም ስለወደፊቱ ግዜና ሁኔታ በትክክል መናገርና መፃፍ ከአሸባሪነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። በተለይ አምባገነን መንግስታት ደግሞ ሀገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ፣ ሕዝቡ ስለሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ሌላው ቀርቶ ስለራሳቸው ሥራና አሰራር ማንም እንዲያውቅባቸው አይፈልጉም። ምክንያቱም፣ ሁሉም አምባገነን መንግስታት በስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉት፤ አንደኛ፡- ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ስለ ፖለቲካዊ መብቱና ነፃነቱ በቂ ግንዛቤ ከሌለው፣ ሁለተኛ፡- የሲቭል ማህበራትና ድርጅቶች በፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ካላደረጉ እና ሦስተኛ፡- የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ ከሌለው ነው።

ነገር ግን፣ የኢንተርኔት ፋይዳና አጠቃቀም ከላይ ከተጠቀሰው ሁኔታ ፍፁም ተቃራኒ ነው። ለምሳሌ፣ አንድ በጉዳዩ ላይ የተሰራ ጥናት የሚከተለውን ድምዳሜ አስቀምጧል፡-
“Four separate areas of Internet use threaten authoritarian regimes: mass public use, civil society organizations (citizens’ pressure groups), economic groups and the international community.”

እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድህረ-ገፆች በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንደ የውይይት መድረክ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል። ዜጎች ሃሳብና መረጃን በቀላሉ እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የሙያና ሲቭል ማህበራት ከሕብረተሰቡ ጋር አሳታፊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው እና በፖለቲካው ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛሉ። የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስችላሉ። በዚህ ምክንያት፣ እንደ ኢህአዴግ ባለ አምባገነናዊ መንግስት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ ይጋርጣሉ።

በአጠቃላይ፣ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ባወጣቸው ፅሁፎች ምክንያት በሽብርተኝነት ወንጀል መከሰሱና በዚህም ጥፋተኛ ሆኖ የመገኘቱ ሚስጥርን ለመረዳት ከዚህ ጋር አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በክስ ቻርጁ ላይ በማስረጃነት የቀረቡትን ጽሁፎች በዝርዝር መመልከት ብቻ ይበቃል። ዩናታን ከሕዳር – ታህሳስ 2008 ዓ.ም ባሉት ቀናት በሀገሪቱ ስለተከሰተው አመፅና አለመረጋጋት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ የያዙ ፅሁፎችን በፌስቡክ ገፁ ላይ አውጥቷል። በእነዚህ ፅሁፎች አማካኝነት ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል፣ የተለያዩ የሲቨል ማህበራትና ድርጅቶች፣ እንዲሁም የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ በወቅቱ ስለነበረው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው አድርጓል። በዚህም በኢህአዴግ መንግስት ላይ የሕልውና አደጋ እንዲጋረጥ የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክቷል። በወቅቱ በሀገሪቱ ስለነበረው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር፣ ሕዝቡ ስለሚያነሳቸው የመብትና ነፃነት ጥያቄዎች፣ እንዲሁም የመንግስትን ሥራና አሰራር በመተቸትና በመፃፍ የኢህአዴግ መንግስትን አሸብሯል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት የፀረ-በሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ጠቅሶ ከሰሰና ጥፋተኛ ነህ አለው። በእውነት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ ክፉኛ ለሚያሸብረው መንግስት ከዮናታን ተስፋዬ የባሰ አሸባሪ ከቶ ከወደየት ይገኛል?

የተሳሳተ ሃሳብን መገደብ በራሱ ስህተትና ጎጂ ነው (ለአብርሃ ደስታ)

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ የዓረና ትግራይ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ያወጧት ፅሁፍ እና ይህን ተከትሎ ከፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ የተሰጠው ምላሽ ነው። አቶ አብርሃ ደስታ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ በሰጡት ምላሽ የግለሰቡ ተግባር ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለውና ፓርቲውንም እንደሚጎዳ ገልፀው፣ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውን አስታውቀዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፄ ላይ ባወጣሁት ፅሁፍ የዓረና ፓርቲ ተግባሩን ከማውገዝ አልፎ በአቶ ዘነበ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የአስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ የግለሰቡን “ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት” የሚገድብና ለዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት እታገላለሁ ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ እንደሆነ ገልጬያለሁ። ሆኖም ግን፣ አቶ አብርሃ ደስታ ለአስተያየቴ የሰጡት ምላሽ በተጨባጭ እውነታና በነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ስለዚህ፣ በዚህ ፅሁፍ እንግሊዛዊው ፈላስፋ “John Stuart Mill” ስለ ሃሳብና የአመለካከት ነፃነት ጥልቅ የሆነ ትንታኔ የሰጠበት “On Liberty” የተሰኘውን መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ።

ይህ ፅሁፍ አቶ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ስላወጡት ፅሁፍ “ትክክለኝነት” ወይም “ስህተትነት” ትንታኔ ለመስጠት ወይም ለማስተባበል የቀረበ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ “አቶ ዘነበ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የፃፉት ሃሳብ ፍፁም ስህተት ነው” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ይሁን እንጂ፣ በዚህ ምክንያት በፓርቲው አመራሮችና ደጋፊዎች እየደረሰባቸው ያለው ጫና እና በቀጣይ ሊወሰድባቸው የሚችለው አስተዳደራዊ እርምጃ ስህተት ከመሆኑ በተጨማሪ ለፓርቲውና ለማህብረሰቡ ጎጂ መሆኑን ለማሳየት የቀረበ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚከተሉትን ሦስት የመከራከሪያ ሃሳቦች ቀርበዋል፡-

1ኛ፡- የዓረና ፓርቲ የተሳሳተ ሃሳብን የመከልከል ስልጣን የለውም

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የዓረና ፓርቲ ሊቀመንበር በሰጡት ምላሽ፤ “የሃሳብ ነፃነት የዴሞክራሲ መርህ ከሆነ፣ ዴሞክራሲ ደግሞ የሕዝብ የበላይነትን ማክበርና ማረጋገጥ ከሆነ፣ ሕዝብን ለማዋረድና ለመሳደብ የሚሰጥ ነፃነት የለም። …ዓረና ለሕዝብ የሚታገል ድርጅት ነው። ፀረ-ሕዝብ ከሆንክ ታዲያ ፀረ-ዓረና ነህ። ፀረ-ዓረና ከሆንክ ደግሞ የዓረና አካል አይደለህም” ብለዋል። የዓረና ፓርቲና የሚወክለው ሕዝብ አንድ መሆናቸውን እና በአቶ ዘነበ ላይ የሚወስደው እርምጃ በዋናነት የሕዝብን የበላይነት ለማስከበርና ለማረጋገጥ እንደሆነ ከአስተያየቱ መረዳት ይቻላል። ነገር ግን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ “John Stuart Mill” እንዲህ ብሏል፡-
“Let us suppose, therefore, that the government is entirely at one with the people, and never thinks of exerting any power of coercion unless in agreement with what it conceives to be their voice. But, the power itself is illegitimate. The best government has no more title to it than the worst… They have no authority to decide the question for all mankind, and exclude every other person from the means of judging.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 13

“የዓረና ፓርቲ የሚወክለውን ሕዝብ የበላይነት ለማስከበር ነው” በሚል አቶ ዘነበ የተሳሳተ ሃሳቡን እንዳይገልፅ ለመገደብና ይህን ተከትሎ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስልጣን የለውም። አቶ አብርሃ ደስታ ግለሰቡ ፀረ-ሕዝብ የሆነ አቋም በይፋ አንፀባርቋልና በአባልነት መቀጠል የለበትም ማለታቸው ፍፁም ስህተት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ ተግባራቸው ያለ በቂ ማስረጃና ጥፋት በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት ከዳረጋቸው ገዢው ፓርቲ ጋር አንድና ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል። በአጠቃላይ፣ ኢህአዴግ/ሕወሃት ሆነ ዓረና ትግራይ በአቶ ዘነበ ሲሳይ አዕምሮ ውስጥ ሊነሳ የሚችለውን ጥያቄ ዓይነትና አግባብነት የመወሰን ስልጣን የላቸውም።

2ኛ፡- የተሳሳተ ሃሳብን መከልከል በራሱ ስህተት ነው!

እንደ አቶ አብርሃ ደስታ አገላለጽ፣ ስለ ሃሳብ ነፃነትና የሕዝብ የበላይነት የተሳሳተ ያላቸው ግለሰቦች የዓረና ፓርቲ አባል ሆነው መቀጠል የለባቸውም። በዚህ መሰረት፣ እንደ አቶ ዘነበ ያሉ የሕዝብን ክብር በሚነካ መልኩ የተሳሳተ ሃሳብ የሚያንፀባርቁ ግለሰቦች ከዚህ ተግባራቸው ሊታገዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ነገር ግን፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ ይህ አመለካከት “ሁሉንም ነገር አውቃለሁ” ከሚል ፍፁማዊነት (infallibility) የመጣ እንደሆነ እንደሚከተለው ይገልፃል፡-
“There is no greater assumption of infallibility in forbidding the propagation of error, than in any other thing which is done by public authority on its own judgment and responsibility. Judgment is given to men that they may use it. Because it may be used erroneously, are men to be told that they ought not to use it at all? An objection which applies to all conduct can be no valid objection to any conduct in particular…”
On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 15

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እንዳንድ ሰዎች ገና-ለገና የተሳሳተ ሃሳብ ሊያስቡ ይችላሉ፣ ወይም ደግሞ ከሕግና የሞራል ስነ-ምግባር ውጪ የሆነ ተግባር ሊፈፅሙ ይችላሉ በሚል በራሳቸው ሕሊና እንዳያስቡና የግል አመለካከታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ሊከለከሉ አይገባም። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ሕሊና ማሰብ እንዲችል ሆኖ የተፈጠረ እንደመሆኑ፣ ሁለትና ሦስት ግዜ የተሳሳተ ሃሳብ ስላንፀባረቀ የሃሳብ ነፃነቱን እስከ መጨረሻው ሊያጣ ይገባል ማለት አይደለም።

አቶ ዘነበ ሲሳይ እንደ ማንኛውም ሰው በራሱ ህሊና የሚያስብ ነው። የራሱን ሕይወት ከመምራት አልፎ-ተርፎ ሀገርና ሕዝብን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመምራትበሚያስችለው መልኩ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ነገር ግን፣ ከዕለታት አንድ ቀን በውስጡ ሲመላለስ የነበረን ሃሳብ በፌስቡክ ገፁ ላይ በመፃፍ ሃሳቡን ገለፀ። ነገር ግን፣ በዓረና አመራሮችና ደጋፊዎች ዘንድ የፅሁፉ ይዘት “እወክለዋለሁ” የሚለውን ሕዝብ ክብር የሚያጎድፍና የፓርቲውን የሥነ-ምግባር ደንብ የሚጥስ ሆኖ ተገኘ። በዚህ ምክንያት፣ ግለሰቡ የፓርቲው አባል ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል ሊቀመንበሩ ጠቁሟል።

እዚህ ጋር አብርሃ ደስታ ራሱ ፍርድ ቤት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ያጋጠመውን መጥቀስ ይቻላል። በወቅቱ አብርሃ ደስታ ያለ በቂ ማስረጃና ወንጀል ተከስሶ ለእስርና እንግልት በተዳረገበት ወቅት ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኞች ከራሳቸው ሕሊና ይልቅ ለባለስልጣናት ተገዢ መሆናቸው አበሳጭቶት ችሎት ፊት በማጨብጨብ ተቃውሞውን መግለፁ የሚታወስ ነው። በእርግጥ ዳኞቹ ለሕሊናቸው ተገዢ አለመሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ አብርሃ ደስታ በማጨብጨቡ ግን ደንብ ጥሷል። ችሎት ፊት በአጨበጨበ ቁጥር ችሎት ተዳፍረሃል ተብሎ ቅጣት ተበይኖበታል። ዳኞቹ ባለስልጣናቱን ፈርተው ለእውነትና ለሕሊናቸው ተገዢ መሆን እንደተሳናቸው ሁሉ፣ አቶ ዘነበም እነ አብርሃን ፈርቶ ሃሳቡን ከመግለፅ መቆጠብ ነበረበት?

በእርግጥ አብርሃ ደስታ በችሎት ፊት በማጨብጨብ ተቃውሞውን የገለጸው ለምንና እንዴት ነበር? በችሎት ላይ የተሰየሙት ዳኞች ከአቃቤ ሕግና ፖሊስ የቀረበላቸውን የተሳሳተ ማስረጃ ትክክለኝነት ሳያጣሩ የጥፋተኝነት ብይን ስለሰጡ ነው። አብርሃ ደግሞ የቀረበበትን ማስረጃ ሃሰት እንደሆነ ለማስረዳት ሲሞክር የእሱን እውነት ለመስማት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው፣ በዚህም በዳኞቹና በፍርድ ቤቱ እምነት በማጣቱ ምክንያት አልነበረም?

አዎ…አብርሃ ደስታ በችሎቱ ፊት በማጨብጨብ ተቃውሞውን የገለጸበት ምክንያት በውስጡ ያለውን እውነት ተናግሮ የቀረበበትን የሃሰት ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ ተናግሮ ለማስረዳት እድል ስለተነፈገው ነው። ዳኞቹም የእሱን እውነት ለመስማትና የቀረበበትን የሃሰት ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ የሚያስቸል የራስ-መተማመን ስላልነበራቸው ነው። ታዲያ እውነትን ተናግሮ በፍርድ ቤት የቀረበበትን የሃሰት ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ ሲታገል የነበረው አብርሃ ድስታ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፁ ላይ የፃፈውን የተሳሳተ ሃሳብ የራሱን እውነት ተናግሮ ግለሰቡን ማሳመንና ሃሳቡን ውድቅ ማድረግ እንዴት ይሳነዋል? ትክክለኛ ሃሳብና አመለካከት ያለው የፓርቲ ሊቀመንበር አንድ አባል የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከቱን በውይይት ከማዳበርና ከማሻሻል ይልቅ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ለምን ይጣደፋል?

3ኛ፡- የተሳሳተ ሃሳብን መገደብ ጎጂ ነው!

በአጠቃላይ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቀውስ የሚፈጠረው፤ የዜጎች መብትና ነፃነት የሚጣሰው፣ እኩልነትና ፍትህ የማይረጋገጠው የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት ስላለ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሰዎች የራሳቸውን እውነት በነፃነት እንዳይናገሩ በመከልከላቸው፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ በመገደባቸው ምክንያት ነው። በተለይ ደግሞ ሰዎች በውስጣቸው ያለውን የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት በነፃነት እንዳይገልፁ ሲከለከሉ ከማንም በፊት ተጎጂ “እውነት” ናት። ምክንያቱም፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ ስህተትና ውይይት “እውነት” የሚረጋገጥበት ብቸኛ መንገድና የሰው ልጅ አሁን ለደረሰበት የዕውቀት እና ሞራል ደረጃ ምንጭ እንደሆኑ ይጠቅሳል፡-
“ …the source of everything respectable in man either as an intellectual or as a moral being, he is capable of rectifying his mistakes, by discussion and experience. Wrong opinions and practices gradually yield to fact and argument; but facts and arguments, to produce any effect on the mind, must be brought before it. The whole strength and value, then, of human judgment, depending on the one property, that it can be set right when it is wrong, reliance can be placed on it only when the means of setting it right are kept constantly at hand.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 16

በመጨረሻም፣ አቶ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው ፅሁፍ ምክንያት በፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት የተለየ ጫና የሚደረግበት ከሆነ፣ እንዲሁም የዓረና ፓርቲ አመራሮች ለዚህ ተግባሩ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስዱበት ከሆነ ከግለሰቡ ባላይ ተጎጂ የሚሆነው ፓርቲውና የሚወክለው ሕዝብ ነው። ምክንያቱም፣ በአቶ ዘነበ ላይ የሚደረግባቸው ጫናና የሚወሰድባቸው እርምጃ በቀጣይ ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች በውስጣቸው ያለውን የተሳሳተ ሃሳብና አመለካካት እንዳይገልፁ ይገድባል። ይህ ደግሞ በፓርቲው የወደፊት እንቅስቃሴና በማህብረሰቡ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ይህን አስመልክቶ “John Stuart Mill” ያለውን በመጥቀስ ሃሳቤን እቋጫለሁ፡-
“…the peculiar evil of silencing the expression of an opinion is, that it is robbing the human race; posterity as well as the existing generation… If the opinion is right, they are deprived of the opportunity of exchanging error for truth: if wrong, they lose, what is almost as great a benefit, the clearer perception and livelier impression of truth, produced by its collision with error.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 13