ሀገሪቱ እያደረገች ያለው ሽግግር፤ ከ’ዕዝ-መር’ ወደ ‘ገበያ-መር’ ሆነ…ከግብርና-መር’ ወደ ‘ኢንዱስትሪ-መር’፤……..

ወደ ገበያ-መር የኢኮኖሚ ስረዓት የሚደረገው ሽግግር ያለ ‘ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት’ (ጥ.አ.ተ) ልማት እና እድገት ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።
በአጠቃላይ፣ ‘ገበያ-መር’ የኢኮኖሚ ስረዓት በንድፈ-ሃሣብም ሆነ በተግባር፤ የስረዓቱ መነሻ-እና-መድረሻ፣ ‘የዳበረ የግል ኢኮኖሚ’ ነው። ሆኖም ግን፣ በተመሣሣይ የሽግግር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሃገራት የገጥማቸው ችግር፣ ከዚህ ቀደም ይከተሉት በነበረው ርዕዮተ-አለም እና ፖሊሲዎች ምክኒያት፣ የግል ኢኮኖሚው ከሞላ-ጎደል ‘የለም’ በሚባልበት ደረጃ ላይ የነበረ መሆኑ ነው።

ለምሣሌ፣ በኢትዮጲያ ጥ.አ.ተን አስመልክቶ ግልፅ የሆነ አቅጣጫ የተቀመጠው በ1990 ዓ.ም ነበር። በግዜው በሀገሪቱ ከነበሩት የቢዝነስ ተቋማት ውስጥ 0.1% መካከለኛ እና ትላልቅ የሚባሉ ተቋማት የነበሩ ሲሆን የተቀረው 99.9% ግን ጥ.አ.ተ ነበሩ። ከነበራቸው የምርት መጠን አንፃር ሲታይ ግን ጥ.አ.ተ የነበራቸው ድርሻ 27% ብቻ ነበር። ይህ የሚያሳየው፣ በግዜው የነበሩት 1,006,539 ጥ.አ.ተ፣ በቁጥር ብዙ ቢመስሉም፣ የነበራቸው ምርታማነት ደረጃ ግን እጅግ በጣም ዝቅተኛ የነበረ መሆኑን ነው።

በተጨማሪ፣ በቁጥር 909 ብቻ የነበሩት ‘መካከለኛ እና ትላልቅ’ ደረጃ የሚመደቡ ተቋማት፣ በግዜው ዘርፉ ከነበረው አመታዊ የምርት መጠን ውስጥ 73% የሚሆነውን ይሸፍኑ ነበር። ይህ ደግሞ፣ ገበያ-መር የሆነ የኢኮኖሚ ስረዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ‘መዋቅር’ ነበረ ብሎ ለማለት አያስደፍርም።

ሀገሪቱ እያደረገች ያለው ሽግግር፤
ከ’ዕዝ-መር’ ወደ ‘ገበያ-መር’ ሆነ…ከግብርና-መር’ ወደ ‘ኢንዱስትሪ-መር’፤ እነዚህ የጥ.አ.ተ ባለንብረቶች እና ማህበራት….-

1.እነዚህ…መንግስት‘ለማስፋፊያ’እያለ በ“ልማታዊ ድጋፍ”ስም የሚሰጣቸውን ብድር/ብር በአራጣ የሚያበድሩ፣

2.እነዚህ…ሲሻቸው ለ’ማሽን መግዣ’ ብለው ተበድረው የ’ግል መኖሪያ ቤት’ የሚሰሩበትና ‘ብድርና ቁጠባ’ ተቋሙ ‘የማይሸጥ-የማይለወጥ’ አሮጌ ማሽን ነቅሎ ሲወስድ ዳር ቆመው የሚስቁ፣

3.እነዚህ…የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ እንዲሣተፉ የተፈጠረላቸው ዕድልን ተጠቅመው የኮንደሚኒየም ቤቶችን በር እና መስኮት ሸፋፋ፣ ጠማማ፣ ወልጋዳ፣ ሰባራ፣ ደንቃራ፣…ያደረጉ…ወዘተ

እ…ነ…ዚ…ህ… የጥ.አ.ተ ባለንብረቶች እና ማህበራት፣ በ‘ኪራይ ሰብሳቢነት’ በሽታ አቅላቸውን ስተው፣ የሀገሬን ልማት እና እድገት አግተው ድርድር ከመጀመራቸው በፊት…አደብ ይግዙ!!!!

©ስዩም ተሾመ

Advertisements