የ’እንትን’#ፌዴራላዊ_ዴሞክራሲያዊ_ዕድር_እናቋቁም!

የ’እንትን’#ፌዴራላዊ_ዴሞክራሲያዊ_ዕድር_እናቋቁም!
*****************************
”ብሔራዊ አንድነት” ማለት ልክ በመዋጮ የሚቋቋም “ማህበር” አንደማለት ነው። እንደውም የመረዳጃ “ዕድር” ብንለው ነገሩን በደንብ ለመግለፅ ይጠቅመናል። ዕድር፣ ወይ በፍላጎትህ አሊያም “ቀባሪ ታጣለህ” ብለው፣ ለምነውና አስፈራርተው ያስገቡህል። ከገባህ በኋላ በመዋጮ እና በትዕዛዝ ያጨናንቁኋል። በተለይ የዕድሩ ሊቀ-መንበር፣ ፀሃፊ፣ ገንዘብ ያዥ፣ እና አንዳንድ ‘እወደድ ባዮች’ ዕድሩን ለቀህ እንዳትወጣ ይለማመጡሃል፤ ሲብስባቸው ደግሞ፣ ያው እንደተለመደው “ቀባሪ ታጣለህ” እያሉ ያስፈራሩሃል። የመጀመሪያ ሦስቱ፣ ዕድሩን ወደ “ዕቁብ” ቀይረው እየተጠቀሙ ስለሆነ ነው። ‘እወደድ ባዮቹ’ ለአንተ አስበው ሣይሆን ‘እራሣቸው” ቀባሪ እንዳያጡ” ሰግተው ነው። እነዚህ፣ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ከዐድሩ ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው።

እያንዳንዱ ግለሰብ የዕድሩ አባል ሆኖ መቀጠል የሚችለው “መዋጮ” እስከ ከፈለ ድረስ ብቻ ነው። መክፈል ስታቆም፣ ‘አትሂድብን’ ሲሉህ የነበሩት እራሣቸው ከዕድሩ አመናጭቀው ያስወጡሃል። እን…ጂ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት’ጋ ሄደህ “ከዕድሩ አስወጡኝ” ካልክ “የምትታለብ ላም ወተቷን አልቦ የሚጠጣውን ‘እባክህ ሽጠኝ’ እንዳለችው ይቆጠራል። ‘መዋጮ እየከፈልኩ ከዕድሩ ተጠቃሚ ለመሆን እስክሞት መጠበቅ የለብኝም! …አብዮቱ ከተመልካችነት ወደ ተጠቃሚነት ተሸጋግሯል!” እያልክ እንደ ‘በቅሎ’ እርገጣቸው። ከምትውጠው በላይ ሲያጎርሱህ ‘ዝም’ ትላለህ። ግመዱ እስክትበጥስ ከጠበቁህ አሪፍ ነው። ታዲያ፣ ገመዱን አሣጥረው እንዲያስሩህ፣ ልክ እንደበጠስክ “ስሞት ለተራበ ጅብ ስጡኝ” እያለክ ከዕድሩ ዉጣና ‘ሽ…..ው” በል። ከዚያ፣ ተመሣሣይ “አቋም” ያላቸውን የዕድር-ሽፍቶች አስተባብረህ ሌላ “ዕድር” አቋቁም። በቃ!

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በነባሩ ዕድር ተጠቃሚ ስላልሆንክ ነው አዲስ የምታቋቁመው። በዚያም ተጠቃሚ ስትሆን ከነባሩ እድር ለምነህ፣ አሳምነህ፣ አስፈራርተህ፣ ወይም በአጋጣሚ አባል ያደረካቸው፣ ዕድሩ በተቋቋመ ሣምንቱ አሁን አንተ የሚሰማህን እንደሚሰማቸው፤ የምታስበውን እንደሚያስቡ ልታውቅ ይገባሃል። ልክ እንደ ሌባ፣ ‘ዕድር ስታቋቁም ትስማማለህ፣ ከተቋቋመ በኋላ ትጣላለህ’። እነ ጆን ጋራንግ እና ሳልቫ ኪር ያቋቋሙት ደቡብ_ሱዳን ተብሎ የሚጠራውን ዕድር ታውቃለህ?

Advertisements