ዘላቂ የሆነ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እድገት በሠራተኛ ቅጥር እንጂ በገንዘብ ቁጥር አይለካም! በስዩም ተሾም

“እድገት” ለአነድ ቢዝነስ ተቋም የስኬታማነት ምልክት ከመሆን ባለፈ፣1በአሠራር እና የሥራ አመራር ሂደት ተቋሙ ሥረ-ነቀል ለውጥ ማምጣት እንደቻለ ማሳያ ነው።2የቢዚነስ ተቋምን እድገት ከምንለካባቸው የተለያዩ ዓይነት መስፈርቶች ውስጥ፡- የሽያጭ ገቢ መጠን፣ የሠራተኛ ቅጥር፣ የንብረት መጠንና ምርታማነት፣ የትርፍ ገቢ፣ እና ካፒታል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።3ብዙውን ግዜ የጥ.አ.ተን እድገት ለመለካት የሚያገለግሉት መስፈርቶች የሽያጭ መጠን እና የሠራተኛ ቅጥር ናቸው።4በ2003 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኢትዮጲያ የጥ.አ.ተ ልማት ስትራቴጂ እንደሚያሳየው ከሆነ የዘርፉ ተቋማትን እድገት ለመለካት የሚያገለግሉት መስፈርቶች በዋናነት የንብረት መጠን እና የሰው ሃይል ናቸው።5

ስለ ጥ.አ.ተ ‘እድገት’ በምንናገርበት ግዜ ከግንዛቤ ማስገባት ያለብን ነገር እድገቱ እንደለካንበት መስፈርት የሚለያይ መሆኑን ነው።6በተለይ በኢትዮጲያ፣ ተቋማቱ በብዛት ወደ ሥራ የገቡት ከአጭር ግዜ በፊት እንደመሆኑ፣ ለረጅም ግዜ የቆዩትም ቢሆን ወጪና ገቢያቸውን በተሟላ ሁኔታ የመመዝገብ ልምድ ወይም አሠራር ስለሌላቸው፣ የተከታታይ አመታት የገቢ እና የካፒታል መጠን መረጃን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ፣ የእድገት ትንበያው በቅርብ አመታት ውስጥ ብቻ በተመዘገበው የሽያጭ ገቢ እና የካፒታል መጠን፣ ወይም በተሳታፊዎች ግምት ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን ስለእድገቱ ሙሉ መረጃ አይሰጥም። በአንፃሩ፣ በተለያዩ ግዚያት በተቋሙ የተቀጠሩና የሰሩ ሠራተኛን ብዛት ማወቅ ይቀላል።

መረጃውን በቀላሉ ማግኘት እንዳለ ሆኖ የእድገቱን ዘላቂነት ለማሳየትም የሠራተኞች ቁጥር/ቅጥር ተመራጭ ነው። የሽያጭ ገቢ በገበያ እና ሌሎች የተለያዩ ወቅታዊ ሁኔታዎች ተፅዕኖ ስር ስለሚወድቅ እድገቱ ዘላቂ ስለመሆኑ አያሳይም። በአንፃሩ የተቋሙ የካፒታል መጠን በገቢ ላይ ሳይሆን ከተጣራ ትርፍ የሚገኝ እንደመሆኑ በተሻለ ሁኔታ የተቋሙን የመስፋፋት አቅም መለካት ያስችላል። ነገር ግን፣ አንድ ተቋም የገቢ መጠኑ ስለጨመር ብቻ የሠራተኛ ቅጥር አያካሄድም። ከዚያ ይልቅ፣ በቂ የካፒታል ክምችት ኖሮት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ሲያደርግ ነው ወደ ሠራተኛ ቅጥር የሚሄደው። ስለዚህ፣ ከሁሉም መስፈርቶች በላቀ ሁኔታ የዘርፉ እድገት ዘላቂ ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚቻለው የሠራተኞች ቅጥርን እንደ ዋና መለኪያ መስፈርት ስንጠቀም ነው።

በተጨማሪ፣ ለጥ.አ.ተ ልማት ትኩረት የተሰጠበት ዋና ምክኒያት ለሀገሪቱ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ድህነትን ለመቀነስ መሆኑ ሲታሰብ የሠራተኛ ቅጥርን እንደ ዋና የእድገት መለኪያ መስፈርት መጠቀም ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንዳለው ያሳያል። ምንም እንኳን ጥናቱ ከተካሄደበት ቦታ አንፃር በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን እውነታ ባያሳይም፣ የሚኒሌክ እና ቺናን ጥናት በኢትዮጲያ የጥ.አ.ተ እድገት ከሠራተኛ ቅጥር አንፃር ሲለካ አመርቂ አለመሆኑን ያሳያል። ይህ ጥናት፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የሥራ እድልን ከመፍጠር አንፃር እድገታቸው አዝጋሚ እነደሆነ፤ በዓመት የ3.86% እድገት ወይም በአመት በአማካይ 0.18 ሠራተኞች እንደሚቀጥሩ፣ ይህም ከሎሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በጣም ደካማ መሆኑን ያረጋግጣል።7

በአጠቃለይ፣ ከማህብረሰባዊ እይታ አንፃር ሲታይ አግባብነት ያለው መስፈርት የሠራተኛ ቅጥር ሲሆን ከጥ.አ.ተ አንቀሳቃሾች (ባለቤቶች/አስተዳዳሪዎች) እይታ አንፃር የሽያጭ መጠን፤8እና ተቋሙ ያለውን የመስፋፋት አቅም ከመለካት አንፃር ደግሞ የካፒታል መጠን የተሻሉ መስፈርቶች ናቸው። ስለዚህ፣ በኢትዮጲያ የዘርፉ ተቋማትን እድገት በመለካቱ ሂደት ከሽያጭ ገቢ እና የካፒታል መጠን ይልቅ የሠራተኛ ቅጥር ከሌሎቹ ቅድሚያ ሊሰጠው እና እንደ ዋና የእድገት መለኪያ መስፈርት ሊወሰድ ይገባል። ይህ ሲሆን፣ ጠቅላላ የዘርፉን እድገት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ተቋም እድገት ቀጣይነት ያለው እና ዘላቂ ስለመሆኑ ጠቃሚ መረጃ ይሰጠናል።

*************ማስታዎሻ**********
በዚህ እና ሌሎች መድረኮች የማቀርባቸው የጥናታዊ ዳሰሳ ፅኁፎች በዋናነት በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት (ጥ.አ.ተ) ዘርፍ ዘላቂ የሆነ እድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ የግሌን ሞያዊ አስተዋፅዖ ለማበርከት በማሰብ የሚቀርቡ፤ በዋናነት በባለድርሻ አካላት ዘንድ የጠራ ግንዛቤ በመፍጠር ይህን ሀገራዊ ጥረት ለማገዝ ያለሙ መሆናቸውን ማስታወስ እወዳለሁ።

***********ማጣቀሻዎች**********
1. Gilbert, A.B., McDougall, P.P & Audretsch, D.B. (2006). New Venture Growth: A Review and Extension. Journal of Management 2006 32: 926.
2. Wiklund, J., & Shepherd, D. (2003). Aspiring for, and Achieving Growth: The Moderating Role of Resources and Opportunities. Journal of Management Studies 2003 40:8.
3. Wiklund, J., Patzelt, H., & Shepherd, D. A. (2009). Building an integrative model of small business growth. Small Bus Econ (2009) 32:351–374.
4. Barbero, J., L., Casillas J., C., & Feldman H., D. (2011). Managerial capabilities and paths to growth as determinants of high-growth small and medium-sized enterprises. International Small Business Journal 2011 29:671.
5.Micro and Small Enterprise Development Strategy, provision framework and methods of Implementation (January, 2011). Federal Democratic Republic of Ethiopia: January 2011, Addis Ababa, Ethiopia.
6. Delmar, F. and Davidsson, P. and Gartner, W. (2003) Arriving at the high growth firm. Journal of Business Venturing 18(2):pp. 189-216.
7. Minilek, K. and Chinnan, K.P.M (2012). Employment growth and challenges in small and micro enterprises Woldiya, North East Amhara region, Ethiopia. Educational Research and Essays Vol. 1(2), pp. 21 – 26, April 2012.
8. Janssen, F. (2009) The Conceptualisation of Growth: Are Employment and Turnover Interchangeable Criteria? Journal of Entrepreneurship 2009 18: 2

Advertisements