መብት እና ነፃነት፡ቁ5

ምንም እንኳን እንደ ነፃነት ምሉዕነት ባይኖራቸውም፣ ፍትህ እና እኩልነት ከነፃነት ጋር በአንድነት ሲጠቀሱ መስማት የተለመደ ነው። በመሰረቱ ነፃነት ውስጣዊ መብት እንደመሆኑ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ ነው። ፍትህ እና እኩልነት ግን ከሰው-ልጅ የውጫዊ እንቅስቃሴው ነፃነት ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለዚህ፣ ፍትህ እና እኩልነት ሰው በነፃነት ውጫዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የሚያስችሉ መብቶች እንደመሆናቸው የሰውን ተፈጥሯዊ ባህሪ፣ ነፃነትን ለማስከበር የተቀመጡ መብቶች ናቸው። በመሆኑም፣ እነዚህና ሌሎች መብቶች በነፃነት ውስጥ የሚረጋገጡ መሆናቸው ናቸው።

ለእኛ እንዲከብሩልን የምንሻው ነፃነት ሌሎች እንድናከብርላቸው ከሚሹት ነፃነት ጋር እኩልና ተመሳሳይ እንደመሆኑ በነፃነት ውስጥ ፍትሃዊነትና እኩልነት ይረጋገጣሉ።

ለምሳሌ፣ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው። እነዚህ ሰው በራሱ-ተነሳሽነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ህያውነቱን እንዲያረጋግጥ የሚያስችሉ መብቶች ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካል ደህንነቱ የተከበረለት ሰው በራሱ ፍላጎት እና ምርጫ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ነፃነት ይኖረዋል።

በነፃነት የማሰብ፣ የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራትና የመጠቀም መብቶች ለማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የተሰጡ ናቸው። ስለዚህ ሰብዓዊ መብቶች በዋናነት የሰውን ነፃነት በማስከበር ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው።

በአጠቃላይ፣ መብት ማለት አንድ ሰው ወይም አካል በአንድ ነገር ወይም ጉዳይ ላይ የሚፈልገውን ለማድረግ ሆነ ላለማድረግ የሚያስችለው ስልጣን ነው።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements