መብት እና ነፃነት-ቁ1

በእንቅስቃሴያቸው ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ግለሰቦች መካከል፣ የአንዱ ነፃነት በሌላኛው ግለሰብ ግዴታውን መወጣት የሚወሰን እንደመሆኑ፣ ግዴታን የሚያስገድድ ስልጣን በሌለበት ሁሉን-አቀፍ የነፃነት መርህ ውድቅ ይሆናል። የሰዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሁሉን-አቀፍ የነፃነት መርህ የማይመራ ከሆነ፤ የመብትና ግዴታ፣ የትክክልና ስህተት፣ የጥሩና መጥፎ፣ የፍትሃዊነትና ኢ-ፍትሃዊነት እሳቤዎች መሰረት ይናዳል።

ግዴታ የሌለበት ነፃነት ‘ያለገደብ መንቀሳቀስ መቻል ወይም እንቅስቃሴን የሚገድብ ውጫዊ ኃይል ያለመኖርን የሚያሳይ ነው’። “ነፃነት” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ በዋናነት በቦታ ገደብና ልቀት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ከሰው-ልጅ የፍላጎትና የምርጫ ነፃነት ይልቅ የሌሎች እንስሳትን እና ጉዑዝ ነገሮችን አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያንፀባርቅ ነው።በዚህ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት የሰው ልጅን ነባራዊ ሁኔታ ለመግለፅ መሞከር ፍፁም ስህተት ነው። “ከምንም ዓይነት እገዳ ወይም ገደብ ነፃ መሆን” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነፃነት፥ ግዴታ የሌለው “መብት” ነው። ሃሳቡን በግልፅ ለመረዳት የ“መብት”ን ፅንሰ-ሃሳብ በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል።

Ethio-think-thank

Advertisements