ከራሳችን በቀር ማንንም መስሎ መሄድ አያዋጣንም!!!

የኒዮ-ሊብራሏ አሜሪካ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሆነ የኮሚኒስት ቻይና ሶሻሊዝም ሥርዓት፣ አንዳቸውም ኢትዮጲያን ወደ ብልፅግና ጎዳና አያደርሷትም።

የግለሰብ ነፃነትና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገው የመጀመሪያው ሥርዓት፣ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ (ነፃነት) ጋር አብሮ የሚሄድ ቢሆንም፣ በገሃድ ያለውን የብሔር (የዘር) ልዩነት ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑ ለተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ጥቅም ብቻ የቆመ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይ ለነጭ አሜሪካዊያን እድገትና ብልፅግና ሲያጎናፅፍ፣ የጥቁሮችንና የቀይ ህንዶችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ለማረጋገጥ ግን ወደ 200 ዓመታት ወስዶበታል (1776 እስከ 1960ዎቹ)።

ማህብረሰብን ተቀዳሚ ያደረገውና እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሰረት ያደረገው ሁለተኛው ሥረዓት፣ ከኢትዮጲያኖች የማህበራዊ እና ሞራል እሴቶች ጋር አብሮ የሚሄድ ቢሆንም፣ የግለሰብን ነፃነት ሙሉ-በሙሉ የሚደፈጥጥ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ እንደ መጀመሪያው ሥርዓት የብሔር ልዩነትን ታሳቢ ያደረገ አይደለም።

እ.አ.አ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና የተዘረጋው ሥርዓት የዜጎቹን የማሰብ፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት የሚጥስ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሥርዓቱ በዋናነት ከሀገሪቱ ህዝብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ለ“ሀን” ቻይናዊያንን ጥቅም የቆመ ነው። በተለይ፣ ቻይና በሃይል የግዛቷ አካል ያደረገቻቸው ትቤታዊያን፣ እንዲሁም በምዕራባዊ ቻይና የሚገኙት የቱርክ ዝርያ ያላቸው ሙስሊም ቻይናዊያን እስከ አሁን ራሳቸውን የማስተዳደር (ዴሞክራሲያዊ) መብታቸውን እንደተነፈጉ አሉ።

በአጠቃላይ፣ የኒዮ-ሊብራሎቹ ሥርዓት ለግለሰብ መብትና ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ጥቅም ለማስከበር የተዘረጋ ነው። የኮሚኒስቶቹ ሶሻሊዝም ደግሞ ለብዙሃን መብትና ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የግለሰቦችን መብት የሚጥስ ነው። ሁለቱንም ሥርዓቶች በኢትዮጲያን ለመዘርጋት የሚያስችል መሰረት የለም።

እንደ አሜሪካ በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጲያ ለመዘርጋት እንዲቻል የግለሰብ ልዕልና እና ሙሉዕነትን ማዕከል ያደረጉ ማህበራዊ እሴቶች የሉንም። ለአንድ ኢትዮጲያዊ፣ ቋንቋው እና የፊት ገፅታው ቀርቶ፣ መጠሪያ “ስሙ“ እንኳን ከግለሰባዊ መጠሪያነት አልፎ ማህብረሰባዊ ማንነቱን ያሳብቃል። በእኛ ሀገር ነባራዊ እውነታ ግለሰባዊ ማንነትን ከማህብረሰባዊ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ ነጥሎ ማስቀመጥ አይቻልም።

“ብዙሃንነትን” የማያስተናግድ ሥርዓት ኢትዮጲያን ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት አይወሰዳትም።  በኢትዮጲያ ነባራዊ እውነታ የ“ብዙሃንነት” ፅንሰ-ሃሳብ እንደ ቻይና “የቁጥር ብዙነትን” (Majority) ሳይሆን በባህል፣ ቋንቋ፣ አኗኗር እና በሌሎች ማህበራዊ እሴቶች ዘንድ ያለንን ልዩነት “Diversity“ የሚያንፀባርቅ ነው።

በአጠቃላይ የምዕራቡ ሆነ የምስራቁ ዓለም የፖለቲካ እሳቤዎች  በኢትዮጲያ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር አብረው የሚሄዱ አይደሉም።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements