ለምን እና እንዴት???

ሰው “ምክንያታዊ ፍጡር” ነው። በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ ይችላል። በራሱ ፈቃድ መንቀሳቀስ የሚችለው ‘ለምን’ እና ‘እንዴት’ እንደሚንቀሳቀስ መረዳት ስለሚችል ነው። ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባሕሪ ሲሆን “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉት ጥያቄዎች ደግሞ የዚህ ዋና መገለጫዎች ናቸው። ስለዚህ፣ የሰው-ልጅ እንቅስቃሴውን “ለምን-እና-እንዴት” በሚሉት ጥያቄዎች እንዲመረምር ችሎታ የተሰጠው ሲሆን ይህን ተግባር እንዲያከናውን ተፈጥሯዊ ባህሪው ያስገድደዋል።

ጥያቄዎቹን አዘውትሮ የሚጠይቅ ግለሰብ፣ ወይም እነዚህ ጥያቄዎች በስፋት በሚስተናገዱበት የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ይዳብራል። የተሻለ ዕውቀት ያለበት የሕብረተሰብ ክፍል፣ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ከሚያውቃት ተፈጥሮ ጋር ግብግብ እንደመግጠማቸው ከተፈጥሮ ሕግ ጋር የማይጋጭ፣ ከነባራዊ እውነታ ጋር አብሮ የሚሄድ ኑሮና አኗኗር ይኖራቸዋል። በቁሳዊ ሀብት እና ንብረት፣ በሳይንሳዊ ዕውቀትና ሥነ-ጥበብ ያድጋሉ። በዚህም፣ የዳበረ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ይኖራል፣ ጠቃሚ የሆኑ ባሕላዊና መንፈሳዊ እሴቶች ይሰርፃሉ። በእንዲህ ያለ ሕብረተሰብ ውስጥ የተሻለ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ይዘረጋል፣ ሥልጣኔ (Civilization) ይወለዳል። ሥልጣኔ ባለበት የበለፀገ ሕብረተሰብ፤ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ባህል እና ማህበራዊ አደረጃጀት ይኖራል።

የለውጥና መሻሻል መንፈስ ባለበት የሕብረተሰብ ክፍል ሥልጣኔ ይወለዳል፣ ሥልጣኔ ያድጋል፣ እድገትና ብልፅግና ይጨምራል። የለውጥና መሻሻል መንፈስ የሚኖረው “ለምን?” እና “እንዴት?” ብለው የሚጠይቁ ግለሰቦች ባሉበት፣ ጥያቄዎቹ በስፋት በሚያስተናግዱበት ሕብረተሰብ ዘንድ ነው።

እነዚህን ጥያቄዎች ለማስተናገድ ፈቃደኛ ያልሆነ የሕብረተሰብ ክፍል፤ ያለና የነበረን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዳለና እንደነበረ እንዲቀጥል በማድረግ ለውጥን ያደናቅፋል። ለችግሩ መንስዔ በሆነ አካሄድ መፍትሄ ሊመጣ አይችልም።

ለችግሩ መፍትሄ በመፈለግ ሁኔታውን መቀየር በማይቻልበት ሁኔታ መሻሻል ሊኖር ስለማይችል፣ ለውጥ በሌለበት መሻሻል አይኖርም። ለውጥና መሻሻል በሌለበት ሥልጣኔ ይሞታል፤ እድገትና ብልፅግና ይጠፋል፣ ድህነትና ኋላ-ቀርነት ይነግሳል። 

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements