ከደጋፊና ተቃዋሚ ባሻገር!!!

“ኢህአዴግ በደቡብ ኮሪያው ልማታዊ መንግስት ሳይሆን በኮሚኒስቷ ቻይና የአመራር ዘይቤ መሰረት ሀገሪቷን እያስተዳደረ ይገኛል።…በልማት ስም ከዴሞክራሲ ይልቅ አምባገነናዊ ስርዓት በሀገራችን ስር እየሰደደ ነው!” ይህ ሃሳብ “ስህተት” ሆነ “ትክክል”፣ በሁለቱም አቅጣጫ ተጠቃሚው ኢህአዴግ ነው።    
1ኛ) ሃሳቡ “ስህተት” ከሆነ ስህተትነቱ የኢህአዴግን የአስተዳደር ዘይቤ ትክክለኝነት ያረጋግጣል። የተሳሳተ ሃሳብ ባይኖር የትክክለኝነት ፅንሰ-ሃሳብ ጭራሽ አይኖርም ነበር።

2ኛ) ሃሳቡ “ትክክል” ከሆነስ፣ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ኢህአዴግ አውቆና ፈቅዶ የተሳሳተ አቅጣጫ ተከትሎ ራሱን ለዉድቀት ስለማይዳርግ፣ ሃሳቡ ትክክል ከሆነ ፖርቲው ወደ  ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመለስ ወቅታዊ ጥቆማ ይሆናል።

ስለዚህ፣ ዘወትር በEBC የሚሰጡ ‘እንጨት-እንጨት’ የሚሉ አስተያዬቶች እንደ መሪ ድርጅት ለኢህአዴግ ፋይዳ-ቢስ ወሬዎች ናቸው። (ደርግ አንድም ግዜ ‘ተሸነፍኹ’ ሳይል እንደተሸነፈ ልብ ይለዋል።) በተቃውሞ የሚሰጡ አስተያዬቶች ግን ለኢህአዴግ “ቁንጅናውን” ወይም “አስቀያሚነቱን” የሚያሳዩ መስታዎት ናቸው።

ኢህአዴግ፤ የትክክለኝነቱና ስህተትነቱ አንፃራዊ ማሳያ የነበሩትን ሁሉ እያሳደደ ለእስር ቤትና ስደት በመዳረግ መስታዎቱን ከሰበረ በኋላ፣ አሁን ልክ በእርጅና ብዛት ውበቷ እንደረገፈ ሴት፣ ሲሳቅበት’ም የተሳቀለት እየመሰለው  በየቦታው ሲያገጥ ይውላል።

ኢህአዴግ ለመጨረሻ ግዜ ፊቱን በመስታዎት የተመለከተው የዛሬ 10 ዓመት ነው። ያኔ ከፊቱ ላይ የነበረውን አቧራ መጥረግ ችሎ ነበረ። ከ1987-1997 ያን ያህል አቧራ ከፊቱ ላይ መኖሩ በራሱ አሳፍሮት ነበር።

አሁንስ…???? የኢህአዴግ ፊት በኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ተጨማዶ ጃጅቷል። ከደሃ ህዝብ በሰበሰበው ሙስና ብዛት በአንገቱ ላይ የወጣው እንቅርት አስቀያሚ ፍጥረት አስመስሎታል። በቃ ሲያዩት ያስጠላል! አዋቂነቴን ያጎላል ብሎ የተሰራው የድግሪ ሜክ-አፕ እንደ ማይክል ጃክሰን ከእንጨት የተሰራ አፅም አስመስሎታል።  ያን የገረጣ አስቀያሚ ፊት ይዞ የካቲትና ግንቦት በመጣ ቁጥር የሚያሰማውን ዲስኩር መስማት የሰለቸው ህዝብ በየአድባሩ እየሄደ “እባክህ አምላኬ፣ ከዚህ አስቀያሚ ፍጥረት ገላግለኝ”  ብሎ ይማፀናል። ኢህአዴግ ሆይ፣ አይን ካለህ እይበት፣ አንገት ካለህ ዙርበት። እ…ይ እኔ እንዳዬሁት።

ይሄን ሁሉ የምልበት “የነውጥ፣ ብጥብጥ፣ ሽብር፣…” ሰይጣናዊ መንፈስ ተፀናውቶኝ ሳይሆን፣ በታሪካዊ አጋጣሚ ሁላችንም የተሳፈርንባት “የኢትዮጲያን መርከብ” የመዘወር እድሉ የኢህአዴግ ስለሆነ ነው።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements

One thought on “ከደጋፊና ተቃዋሚ ባሻገር!!!

  1. ከምርጫው በፊት የተፃፈ ቢሆንም ከምርጫው በኋላ ያለውን ድባብ የሚገልፅ ሆኖ ስላገኘሁት በድጋሜ አውጥቼዋለሁ።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡