የቦታና ግዜ ገደቦች:ቁ1

በእራስ-ተነሳሽነት ከሚደረግ እንቅስቃሴ አንፃር፣ በሁሉም ቦታና ግዜ በእራሱ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ የሚችል ፍጡር እስከሌለ ድረስ የቦታና ግዜ ገደቦች “ፍፁም” ናቸው። ነገር ግን፣ እነዚህ ተፈጥሯዊ ገደቦች በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያላቸው ገደብ “አንፃራዊ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች የሚያደርጓቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በሦስት ደረጃዎች ይከፈላሉ።

አንደኛ፡- ፍፁም በሆነ ሁኔታ በቦታ እና አካላዊ-አፈጣጠር የተገደቡና በስሜታዊ ደመ-ነፍስ የሚመሩ እንቅስቃሴዎች፣ ሁለተኛ፡- በአካላዊ-አፈጣጠር ብቻ የተገደቡና በስሜታዊ-ግንዛቤ የሚመሩ እንቅስቃሴዎች፣ እና ሦስተኛ፡- በቦታ እና አካላዊ-አፈጣጠር ያልተገደቡና በምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የሚመሩ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በዚህ መሰረ፣ በየደረጃው ያሉ ተሳታፊዎችን፤ ዕፅዋት፣ እንስሳት እና የሰው-ልጅ በማለት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በደረጃ ማስቀመጥ ይቻላል።
ከላይ የተጠቀሱት ሦስት የተግባራዊ እንቅስቃሴ ደረጃዎች፣ “ሰው” ከሌሎች እንስሳት የሚለይበትን መሰረታዊ ምክንያት በግልፅ መረዳት ያስችላል።

ሕይወት ባላቸው ነገሮች መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት በእራስ-ተነሳሽነት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ነፃነት ነው። የዕፅዋት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ፍፁም በሆኑ የቦታና አካላዊ ገደቦች ውስጥ የሚደረግ ነው። በመሆኑም፣ በእራሳቸው-ተነሳሽነት ከቦታ-ቦታ መንቀሳቀስ አይችሉም። ለፍላጎት ለውጥ የአካላቸውን ቅርፅና ይዘትን በመቀያየር በደመ-ነፍስ ከመንቀሳቀስ ባለፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም። አማራጭ ለሌለው እንቅስቃሴ መነሻ-ምክንያት የሆነ ፍላጎት አስገዳጅ ነው። ለዚህ ዓይነት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚደረግ አንቅስቃሴ በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሚደረግና ከመኖር ሕልውና ጋር የተቆራኘ ይሆናል። በዚህ መሰረት፣ ዕፅዋት በሚያደርጉት ደመ-ነፍሳዊ እንቅስቃሴ ነፃነት ሊኖራቸው አይችልም። 

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements