የፍላጐትና ምርጫ ነፃነት፡ቁ3

ሕይወት ያላቸው ነገሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቦታና ግዜ ተፈጥሯዊ ገደቦች የተገደበ ነው። ሕይወት” በቦታና ግዜ ተፈጥሯዊ ገደቦች ውስጥ የሚደረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ናት። በእራሱ ተነሳሽነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚችል ነገር ሁሉ ሕይወት አለው። በሌላ አነጋገር፣ በሌላ አካል አነሳሽነት ወይም አስገዳጅነት ብቻ የሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ ሕይወት የለውም።

ሁሉንም የሕይወት እንቅስቃሴ በእራሱ-ተነሳሽነት የሚያደርግ ፍጡር የለም። ግዑዝ ነገር፣ ለእንቅስቃሴው መነሻ የሚሆን የፍላጎት ለውጥ የሌለው እንደመሆኑ፣ በሌላ ውጫዊ አካል አስነሽነት/አስገዳጅነት የማያቋርጥ የለውጥ እንቅስቃሴ ያደርጋል።

ማንኛውም ሕይወት ያለው ነገር’ም ቢሆን፣ የተወሰነውን በእራሱ-ተነሳሽነት፣ የተቀረው እንቅስቃሴ ደግሞ በነገሮች አስገዳጅነት ያደርጋል። ይህን በነገሮች ላይ እየተካሄደ ያለን ለውጥ በመገንዘብና መረዳት ረገድ የተለያየ አቅም እንዲኖራቸው አድርጓል።

በግንዛቤ ረገድ ካለው ልዩነት በስተቀር ከተፈጥሯዊው የለውጥ እንቅስቃሴ ውጪ የሚሆን ነገር ሊኖር አይችልም። በመሆኑም፣ መንስዔው ተነሳሽነት ሆነ አስገዳጅነት ሁሉም ነገር በማያቋርጥ የለውጥ እንቅስቃሴው ውስጥ ነው። በአጠቃላይ፣ ተፈጥሮን ከፈጠረ ፈጣሪ በስተቀር ሁሉም ነገር ለዚህ ለተፈጥሯዊ ሕግ ተገዢ ነው።  ነገር ግን፣ በተፈጥሮ-አስገዳጅነት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በመልሶ-እይታ ከመገንዘብ ባለፈ አነሳሳቸውን በቀጥታ ለመገንዘብ ወይም ለመቆጣጠር አይችልም።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements