ግዑዝነት እና ነፃነት

በእራስ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ (self-initiated motion) የማይችል ነገር ሁሉ “ግዑዝ” ነው። ድንጋይ ግዑዝ ነው፣ ስለዚህ ሕይወት የለውም። ሕይወት ያለው ነገር ከግዑዝ ነገር የሚለየው በእራሱ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ የሚያስችለው ኃይል ስላለው ነው። ሕይወት ያለው ነገር በእራሱ ተነሳሽነት ለሚያደርገው ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ የሚያስፈልገውን ነፃነት ሲያጣ ወደ ግዑዝነት ይቀየራል፣ ይሞታል።

እንበልና ወደ አንዲት ድመት አቅጣጫ ድንጋይ ወረወርኩና ድመቷ ሮጠች። በዚህም እኔ፣ ድመቷና ድንጋዩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አድርገናል። ነገር ግን፣ የእኔና የድመቷ እንቅስቃሴ ከድንጋዩ የሚለየው በእራሳችን-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ ስለቻልን ነው። ድንጋዩ  ግን በእራሱ መንቀሳቀስ የሚያስችል ሃይል የለውም። ስለዚህ፣ በውጫዊ ኃይል ሊገደብ የሚችል ነፃነት ሊኖረው አይችልም።

ግዑዝ ነገር ለተወሰነ ቅፅበት እንኳን ቢንቀሳቀስ፣ እንቅስቃሴው በእራሱ-ተነሳሽነት ሳይሆን በሌላ ውጫዊ ኃይል አነሳሽነት የተከሰተ ስለሆነ ሕይወት እንዳለው ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። በአጠቃላይ፣ በእራሱ-ተነሳሽነት የማይንቀሳቀስ ነገር በእራስ-ተነሳሽነት ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልገው ውስጣዊና ተፈጥሯዊ ፍላጎት እንጂ ነፃነት አይደለም።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements