ሃሳብና ማሰብ

ሌሎች እንስሳት እንደ ሰው ነገሮችን የመገንዘብ፣ መረጃዎችን የማጠናቀር፣ ሃሳቦችን የመፍጠርና በመካከላቸው ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት የመገንዘብ አቅም ወይም የማሰብ ተፈጥሯዊ ችሎታ የላቸውም። በዚህ ምክንያት፣ ሌሎች እንስሳት እንደ ሰው ሃሳባዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም።

ሰው፣ ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ በነገሮች፣ ክስተቶች እና ሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት ያጠናል፤ በቦታና ግዜ ሳይገደብ ሃሳባዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል። ተፈጥሯዊ እውነታን በሦስት የግዜ እይታዎች፤ ካለፈው፣ ከአሁኑና ከወደፊቱ ግዜ አንፃር መገንዘብና መረደት ይችላል። በዚህ ተፈጥሯዊ ችሎታ አማካኝነት ሰው ከሌሎች እንስሳት በተሻለ እውነታን መገንዘብና መረዳት (understanding) ይችላል።

የሰው ተግባራዊ እንቅስቃሴ፣ እጅግ ብዙ መረጃዎች ከተሰበሰቡና ፈጣን በሆነ ሁኔታ በአዕምሮው ከተቀናበሩ በኋላ በሚከሰት የፍላጎት ለውጥ መንስዔነት የሚደረግ ነው። የስሜት ህዋሳት ተፈጥሯዊ ተግባራቸውን እስካልተቋረጡ ድረስ ስሜትን ወደ አዕምሮ ያስተላልፋሉ። እንደ ስሜት ህዋሳት፣ ተፈጥሯዊ ተግባሩ እስካልተቋረጠ ድረስ አዕምሮ’ም የስሜት መልዕክቶችን ይገነዘባል።

የሰው አዕምሮ በስሜት ህዋሳት አማካኝነት የሚላኩለትን መረጃዎችን መገንዘብ፣ ማጠናቀርና ማሰብ ይችላል። ይሁን እንጂ፣ የሰው-አዕምሮ ተፈጥሯዊ ተግባሩን እስካላቋረጠ ድረስ “አለማሰብ” አይችልም። ሰው’ም፣ የመኖር ሕልውናው እና ግንዛቤውን ሳያጣ፣ የአዕምሮውን ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ማቋረጥ አይችልም።

አንድ ሰው፤ ሃሳብን ላለማሰብ ከማሰብ ባለፈ አዕምሮው እንዳያስብ ማድረግ፣ በአዕምሮው ውስጥ ምንም ዓይነት ሃሳብ እንዳይኖር ሊያደርግ አይችልም። በመሆኑም፣ “ማሰብ” በእራሱ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። እንደ አካላዊ እንቅስቃሴ ሀሉ፣ የሃሳባዊ እንቅስቃሴን መንስዔ በቀጥታ መገንዘብና መቆጣጠር አይቻልም።
ምንም እንኳን ሰው አለማሰብ ባይችልም፣ ስለ አስተሳሰቡ ግን ማሰብ ይችላል።

ሰው በአዕምሮው ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ላይ ቀጥተኛ ኃይል ባይኖረውም፣ በሃሳባዊ-እንቅስቃሴ ላይ ግን አለው። ሃሳብን ማስቀረት አይቻልም፣ ሃሳብን መቀየር ግን ይችላል። በዚህም፣ አንድን ሃሳብ በሌላ ሃሳብ በመቀየር በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ትስስር ማጤን ይችላል። ሰው፣ ምንም ሃሳብ አለማሰብ ባይችልም፣ አንድን ሃሳብ “ለማሰብ” ወይም “ላለማሰብ“ መወሰን ይችላል።

ሰው አዕምሮውን እንቅስቃሴ ማስቆም ባይችልም፣ የእቅስቃሴውን አቅጣጫ መምረጥና መወሰን ይችላል። ስለዚህ፣ ሰው የሚያደርገውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከመገንዘብና መቆጣጠር አንፃር ሁለት ዓይነት ሃይሎች አሉት። እነዚህ ሃይሎች ከሰው-ልጅ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ከማየታችን በፊት የኃይልን ፅንሰ-ሃሳብ በአጭሩ ማየት ያስፈልጋል። 

https://ethiothinkthank.wordpress.com