“ነፍስ” እና “ፍላጐት”፡ ቁ2

ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ እንቅስቃሴው በውስጡ ካለ የማያቋርጥ ተፈጥሯዊ ፍላጎት የሚመነጭ ነው። ይህ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ያለ ማቋረጥ ሁኔታ የሚቀያየር ሲሆን በተወሰነ ግዜ፣ ቦታና ምክንያት አንድ ፍላጎት ከሌሎች ፍላጎቶች በተለየ ሁኔታ ጎልቶ ይወጣል። በዚህ መልኩ ጎልቶ የሚወጣ ፍላጎት በአካል እና በባህሪ ላይ የላቀ ተፅዕኖ በመፍጠር ለተግባራዊ እንቅስቃሴ መንስዔ ይሆናል።

“በእራስ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ” የሚችል ነገር ለእንቅስቃሴው መነሻ የሆነ “ተፈጥሯዊ ፍላጎት” በውስጡ እንዳለ ይጠቁማል። በመሆኑም፣ ተንቀሳቃሹ ነገር፣ ያለ ውጫዊ አካል አነሳሽነት ወይም አስገዳጅነት፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ተፈጥሯዊ አቅም አለው።

ፍላጎት የሌለው ነገር በእራሱ-ተነሳሽነት ለመንቀሳቀስ አይችልም። በእራሱ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ የማይችል ነገር፤ ተፈጥሯዊ ፍላጎቱ ተሟጦ ያለቀ ወይም ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ፍፁም የማይችል፣ በዚህም የመኖር ሕልውናው ያከተመ፣ “በሞት” ከህያውነት ወደ ግዑዝነት የተቀየረ መሆኑ ይጠቁማል። በዚህ መሰረት፣ በእራስ-ተነሳሽነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ፍላጎት የሕይወት ፅንሰ፣ “ነፍስ” ነው።

‘በእራስ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ መቻል፣’ ተንቀሳቃሹ ሕይወት (ነፍስ) እንዳለው ከመጠቆም ባለፈ ሌላ ነገር/ባህሪ አይጠቁምም። ነፍስ ያለው ነገር ሁሉ በእራሱ-ተነሳሽነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ተመሳሳይ የሆነ ባህሪ እንዳላቸው ያሳያል። ሁሉም በእራስ-ተነሳሽነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ኃይል አላቸው። ይሁን እንጂ፣ ሁሉም ሕይወት ያላቸው ነገሮች፣ የእንቅስቃሴያቸው መነሻ የሆነውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት መቆጣጠር አይችሉም። ሕይወት ያለው ነገር እንቅስቃሴ “በእራስ-ተነሳሽነት” ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ መነሻ የሆነውን የፍላጎት ለውጥ በቀጥታ ለመገንዘብ የሚያስችል ኃይል (active power) የላቸውም። በመሆኑም እንቅስቃሴያቸው የሚመራበትና በተፈጥሯዊ ፍላጎት ላይ ያለን የማያቋርጥ ለውጥ ወይም እንቅስቃሴ በቀጥታ ለመገንዘብ፣ ለመቆጣጠርም ሆነ ለመለወጥ አይችሉም። እንቅስቃሴው “ክስተት” እንደመሆኑ መጠን፣ ለክስተቱ መንስዔ የሆነውን የማያቋርጥ የፍላጎት ለውጥ መገንዘብ ወይም መቆጣጠር፣ በዚህም ለሚያደርገው እንቅስቃሴ አማራጭ እና ምርጫ ሊኖረው ካልቻለ፣ ተግባሩ በውስጣዊ አካል አስገዳጅነት የተፈፀመ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ስለዚህ በእራስ-ተነሳሽነት መንቀሳቀስ፣ ውስጣዊ በሆነ አስገዳጅ ሁኔታ የሚደረግ እንቅስቃሴ ከመሆን ያለፈ ሌላ ትርጉም የለውም።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements