አካላዊና ሃሳባዊ እንቅስቃሴ

እንደ ማንኛውም ሕይወት ያለው ነገር፣ የሰው-ልጅ እንቅስቃሴዎች በእራስ-ተነሳሽነት ወይም በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሚደረጉ ናቸው። ከዚህ አንፃር፣ የሰውን እንቅስቃሴ“አካላዊ” እና “ሃሳባዊ” በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል።

በውስጡ ያለው የማያቋርጥ የፍላጎት ለውጥ ያለ ምንም ማቋረጥ እንዲንቀሳቀስ ስለሚያደርገው፣ የሰው አካል፣ የአካል ክፍሎቹ፣ የአካል ክፍሉ ሕዋሳት…ወዘተ፣ በአጠቃላይ.፣ የሰው አካላዊ ማንነቱ ቋሚ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለ ነው። በዚህ ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደት፣ ሰው በውጫዊና ውስጣዊ አካሉ፣ የአካል ክፍሎቹ ወይም ሕዋሳቱ ላይ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ በቀጥታ መገንዘብ አይችልም።

ለምሳሌ፣ ሰው የአካሉ እድገትና ማርጀት፣ የሰውነቱን ዉፍረትና ቅጥነት፣ የሕዋሶቹንንና የነርቮቹን ቅፅበታዊ እንቅስቃሴ፤ የርሃብንና የሕመምን ስሜት…ወዘተ፣ በአጠቃላይ በደመ-ነፍስና በስሜታዊ ግንዛቤ እየተመራ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በቀጥታ ለመገንዘብ አይችልም።

እንቅስቃሴዎቹ የሚጀምሩበትንና የሚካሄዱበትን መንገድ፣ በዚህም የፍላጎት ለውጥ የሚፈጥሩበትን ሂደትና ለአካላዊ ወይም ሃሳባዊ እንቅስቃሴ መነሻ የሚሆኑበትን መንገድ በቀጥታ መገንዘብ ካልተቻለ፣ ሰው እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለመቀበል እንጂ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል የለውም። ስለዚህ እንቅስቃሴው በእራስ-ተነሳሽነት የሚደረግ አይደለም።

በዚህ ረገድ፣ የሰው ኃይል፣ በስሜቱ ወይም የተለያዩ የአካል ክፍሎቹ አማካኝነት የተከሰተውን የፍላጎት ለውጥ፣ ከውጤት-ወደ-ምክንያት የተገላቢጦሽ በመልሶ-እይታ መገንዘብ የሚያስችል ነው። በተመሳሳይ፣ የስሜት ሕዋሳቱና የአዕምሮው ክፍል ተፈጥሯዊ ባህሪ፣ የሰውን ስሜታዊ ግንዛቤ ያለማቋረጥ እንዲቀያየር ያደርጉታል። በዚህ ምክንያት፣ መሰረታዊ የሆነውን የእነዚህ ክፍሎች እንቅስቃሴ፤ መረጃዎችን ከስሜት ህዋሳት ተቀብሎ በማቀናበር ስሜታዊ ግንዛቤ (perception or perceptual understanding) የሚፈጠርበትን ሂደት በመልሶ-እይታ ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ ለመገንዘብና ለመቆጣጠር አይችልም።

በአጠቃላይ፣ ሰው የሚያደርገውን አካላዊ እንቅስቃሴ እና ስሜታዊ የግንዛቤ ሂደትን በቀጥታ ለመገንዘብና ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል የለውም። በመሆኑም፣ ከዚህ አንፃር የሚያደርጋቸውን አካላዊና ሃሳባዊ እንቅስቃሴዎች በእራስ-ተነሳሽነት የሚያደርጋቸው አይደሉም። በተፈጥሯዊ ፍላጎት አስገዳጅነት የሚደረጉ እንደመሆናቸው፣ ሰው በእነዚህ እቅስቃሴዎች ላይ የማድረግና ያለማድረግ ነፃነት ሊኖረው አይችልም። ነፃ ያልሆነ ነገር ደግሞ ሊገደብ አይችልም።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements