የነፃነት ሲቃ… ነፃነት ሰብዓዊነት እንጂ መብት አይደለም!!!

እንደ ማንኛውም ሕይወት ያለው ነገር፣ የሰው-ልጅ እንቅስቃሴዎች በእራስ-ተነሳሽነት ወይም በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሚደረጉ ናቸው።ሰው በደመ-ነፍስና በስሜታዊ ግንዛቤ ላይ በመመስረት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በቀጥታ ለመገንዘብና መቆጣጠር የሚያስችል ሃይል የለውም። በዚህ ረገድ፣ የሰው ኃይል፣ በስሜቱ ወይም የተለያዩ የአካል ክፍሎቹ አማካኝነት የተከሰተውን የፍላጎት ለውጥ፣ ከውጤት-ወደ-ምክንያት፣ የተገላቢጦሽ በመልሶ-እይታ መገንዘብ የሚያስችል ሃይል ነው ያለው። በአጠቃላይ፣ ሰው የሚያደርገውን አካላዊ እንቅስቃሴ እና ስሜታዊ የግንዛቤ ሂደትን በቀጥታ ለመገንዘብና ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል የለውም።

በተፈጥሯዊ ፍላጎት አስገዳጅነት የሚደረጉ እንደመሆናቸው፣ ሰው በእነዚህ እቅስቃሴዎች ላይ የማድረግና ያለማድረግ ነፃነት ሊኖረው አይችልም። ነፃ ያልሆነ ነገር ሊገደብ አይችልም። በተፈጥሮ አስገዳጅነት በሚደረጉ ተግባራት ላይ ነፃ-ፍላጎትና ምርጫ የለም፣ መገንዘብ እና/ወይም መቆጣጠር በማንችለው እንቅስቃሴ ላይ ነፃነት የለም።

ነገር ግን፣ ሰው ነባራዊ እውነታን በመገንዘብ፣ የነገሮችን ምንነት እና የምልክቶችን ትርጉም በመረዳት፣ እንዲሁም በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት በመገንዘብ፤ ሃሳቦችን ይፈጥራል፣ ያዳብራል፣ ይለውጣል። በመሆኑም፣ በአዕምሮው ውስጥ ያሉ ሃሳቦችን ከመገንዘብ፣ ከነባራዊ እውነታ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማነፃፀር፣ በመካከላቸው ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት ከማስላት አንፃር፣ ሰው ቀጥተኛ የሆነ ኃይል (active power) አለው። ስለዚህ፣ ሰው ሃሳባዊ እንቅስቃሴን ለማድረግና ላለማድረግ፣ በእንቅስቃሴው ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል መወሰን ይችላል። ሰው ሃሳባዊ አንቅስቃሴውን ተግባራዊ የማድረግና የመለወጥ አቅምና ብቃት አለው።

ምንም እንኳን በደመ-ነፍስና በስሜታዊ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለመጀመር ወይም ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል ባይኖረውም፣ በሃሳባዊ እንቅስቃሴው ላይ ግን ሙሉና ቀጥተኛ የሆነ ኃይል አለው። በዚህ መሰረት፣ ሰው በአዕምሮው በማሰብና በመምረጥ ብቻ የተለያዩ ተግባራትን መጀመር ወይም መግታት፤ መቀጠል ወይም ማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ኃይል አለው።
በሃሳቡና በፍላጎቱ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ፣ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቀጠል ወይም ለማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯ ኃይል ስላለው፣ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ስለ አንድ ነገር ለማሰብ ወይም ላለማሰብ፣ በሃሳቡ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ መወሰን ይችላል። ስለዚህ፣ ሰው በእራሱ ፈቃድ ሃሳባዊ እንቅስቃሴን የማድረግ፣ እንዲሁም በሃሳቡና አስተሳሰቡ መሰረት የተወሰነ የሰውነት ክፍሉን ማንቀሳቀስ ይችላል።1 በዚህ መሰረት፣ “ፈቃድ“ (Will) ማለት፣ በሃሳብ ላይ ብቻ በመመስረት አንድን ነገር ለመፍጠር ወይም ለማድረግ መሞከር ይሆናል።

ማንኛውም ግለሰብ አንድን ነገር በእራሱ ፈቃድ  ለመፍጠር ወይም ለማድረግ የሚያስችለውን አካላዊ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት፣ በቅድሚያ በጉዳዩ ላይ ሃሳባዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም፣ በተወሰነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ከመሆኑ በፊት ስለ እንቅስቃሴው ማወቅ አለበት። ይህ ካልሆነ፣ በእራስ ሃሳብ ላይ ያልተመሰረተ እንቅስቃሴ በፍቃደኝነት ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚደረግ ነው። ስለዚህ፣ በፍቃደኝነት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በእራስ ሃሳብ፣ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።

ሰው፣ እውነታን ለመገንዘብና ለመረዳት፣ በዚህም በዙሪያው ስላሉ ነገሮች ምክንያታዊ ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት፣ በቅድሚያ እራሱን ማወቅ አለበት። ስለዚህ፣ በዙሪያው ስላሉ ነገሮች ለማወቅ የእራሱን ያለበትን ነባራዊ እውነታ ማወቅ፣ የሚኖርበትን እውነታ ለማወቅ በሕይወት መኖሩን ማወቅ ይኖርበታል። አንድ ሰው በሕይወት መኖሩን የሚያረጋግጥበት አንድና ብቸኛ መንገድ፣ በእራሱ ፈቃድ አካላዊ ወይም ሃሳባዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ነው። ሰው በፍቃዱ ለመንቀሳቀስ እንዲችል እራሱን ማወቅ አለበት፣ ለዚህ ደግሞ በእራሱ ፈቃድ መንቀሳቀስ መቻል አለበት።

ሰው አንድን ተግባር በፈቃዱ ለመከዎን በቅድሚያ ማሰብ ያለበት ሲሆን፣ ስለ ተግባሩ ለማሰብ ግን በቅድሚያ ፍቃደኛ መሆን አለበት። ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከማድረጉ በፊት፤ ምን፣ ለምን እና አንዴት እንደሚንቀሳቀስ መረዳትና ማወቅ ያለበት ሲሆን፣ “ምን?”፣ “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ግን በቅድሚያ ፍቃደኛ መሆን አለበት። በማሰብ ስለ አንድ ነገር ያውቃል፣ ነባራዊ እውነታውን ይረዳል። ስለዚህ፣ ለመፍቀድ ማሰብ – ለማሰብ ፍቃደኛ መሆን አለበት፣ ለማወቅ መፍቀድ – ለመፍቀድ ማወቅ አለበት። በዚህ መሰረት፣ ፈቃድ (will) እና መረዳት (understanding) የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ናቸው።

ሰው፣ አንድን ተግባር በፈቃዱ ለማከናዎን መረዳት፣ ተግባሩን ለመረዳት ደግሞ በቅድሚያ መፍቀድ ካለበት፣ ፈቃድ እና መረዳትን በተናጠል ማየት አይቻልም። በመሆኑም፣ ፈቃድን ከመረዳት ወይም መረዳትን ከፈቃድ መነጠል እስካልተቻለ ድረስ፣ ሁለቱን በጥምረት ማየት ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው፣ ፈቃድ እና መረዳትን እንደ መነሻ ምክንያት፣ የሁለቱን ድምር ውጤት በማጥናት ይሆናል።  በፈቃድ እና መረዳት ጥምረት የሚፈጠር ወይም የሁለቱ ድምር ውጤት የሆነው ነገር “ነፃነት” (liberty) ነው።
“ነፃነት” ማለት “ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል ወይም አስገዳጅ ሁኔታ (necessity) ነፃ ሆኖ ማሰብ ወይም ማድረግ ነው”።’

ስለዚህ፣ ነፃነት የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ፣ ያለ ውጫዊ ኃይል ወይም የሁኔታዎች አስገዳጅነት “አካላዊ እንቅስቃሴ” (physical motion) ወይም “ሃሳባዊ እንቅስቃሴ” (thinking) ማድረግ መቻል ነው። ነፃነት ሊኖር የሚችለው የተንቀሳቃሹ አካል በእራሱ-ተነሳሽነት እና ግንዛቤ መሰረት መንቀሳቀስ ሲችል ነው። ማንኛውም ሰው ቢሆን አንድን ተግባር በእራሱ ፍቃድና ግንዛቤ መሰረት መጀመር ወይመ ያለመጀመር፣ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቀጠል ወይም ላለማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ኃይል አለው።

አንድ ሰው ነፃነት የሚኖረው በተረዳው መንገድ ለመንቀሳቀስ በእራሱና ለእራሱ መፍቀድ ሲችል ነው። 
ሰው ምክንያታዊ ግንዛቤ ሳይኖረው ወይም ፈቃደኛ ሳይሆን በሚያደርገው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ነፃነት ሊኖረው አይችልም። የእንቅስቃሴውን መነሻ-ምክንያት እና ውጤት አውቆና ፈቅዶ ሲያደርግ ብቻ ነው ነፃነት ሊኖረው የሚችለው።

እንቅስቃሴያችን በእራሳችን ፍቃድና ቁጥጥር ስር ሳይሆን ሲቀር፤ በተረዳነው መልኩ ለመንቀሳቀስ የሌላ አካል ፈቃድና ይሁንታ ካስፈለገ፣ በዚህም በመረዳትና ፈቃድ መካከል ልዩነት ሲፈጠር የተንቀሳቃሹ አካል ነፃነት ተገፏል። ስለዚህ፣ ነፃነት የሚገኘው ፈቃድ እና መረዳት እኩል ሲጣማሩ ነው።

ይቀጥላል…

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements