የነፃነት ሲቃ… (ካለፈው የቀጠለ…)

የአንድ ግለሰብ አንቅስቃሴ “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” የሚሆነው ተግባሩ በእራሱ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነ አይደለም። ማንኛውም ዓይነት ተግባር በእራሱ ጥሩ ወይም መጥፎ ቢሆን ኖሮ “ስህተት” አይኖርም ነበር።
    
ከዚያ ይልቅ፣ የአንድ ተግባር ጥሩነት ወይም መጥፎነት የሚወሰነው በእንቅስቃሴያችን አግባብነት ነው። “አግባብነት” ያለው ተግባር (expedient)፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲደረግ በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ የሚከናዎን፣ ተቀባይነት እና ጠቀሜታ ያለው ተግባር ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ ደግሞ አግባብ-ያልሆነ (inexpedient) ተግባር ነው። ነገር ግን፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያችን አግባብነት ያለው ወይም የሌለው ስለመሆኑ፣ ከጥሩና መጥፎ የሞራል እሳቤ ባለፈ፣ ግልፅና ወጥነት ባለው መልኩ ለመለየት የሚቻለው፣ ጉዳዩን ከሰው-ልጅን ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር አያይዞ ማየት ያስፈልጋል።

የተግባራዊ እንቅስቃሴያችን አግባብነት ወይም የሞራል እሴቶቻችን ከመሰረታዊ የተፈጥሮ ባህሪያችን ጋር የተቆራኙ ናቸው። የአንድ ተግባር አግባብነት የሚመዘነው እንቅስቃሴው በእኛ እና በሌሎች ሰዎች ነፃነት ላይ ባለው ተፅዕኖ መሰረት ሲሆን የሞራል እሴቶቻችንም ከዚህ አንፃር የተቃኙ ናቸው።

አንድ ግለሰብ፣ አውቆና ፈቅዶ በሚያደርገው አካላዊና ሃሳባዊ እንቅስቃሴ የሚኖረው ነፃነት የሌሎች ሰዎችን ነፃነት እንዳይፃረር ከሚያደርግ ግዴታ ጋር በተጣመረ መልኩ የተሰጠ ነው። ስለዚህ፣ ማንኛውም ግለሰብ ‘የሌሎች ሰዎችን ነፃነት እንዳይፃረር ተፈጥሯዊ ግዴታና ኃላፊነት አለበት። ማንኛውም ዓይነት ተግባር በእራሱ ወይም በአላማው፣ በሁሉም የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች ነፃ-ፍላጎት እና ምርጫ ላይ ተፅዕኖ እስካልፈጠረ ድረስ እንደ ትክክለኛ ተግባር ወይም “መብት” ሊወሰድ ይችላል።

አንድ ግለሰብ በተረዳውና በፈቃዱ መሰረትና የሌሎች ሰዎች ነፃነትን በማይፃረር መልኩ የሚያደርገው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ አግባብነት እንዳለው ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ መልኩ የሚደረግ ተግባር ትክክለኛ እና የድርጊቱ ፈፃሚ መብት እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታሰብ፣ ከሥነ-መግባር መርህ አንፃር አግባብነት ይኖረዋል።

ከድርጊት ፈፃሚው አንፃር መብት የሆነ እና የሌሎች ሰዎች ነፃነት አንዳይጣስ የተቀመጠን የሥነ-መግባር መርህ የማይፃረር ማንኛውም ዓይነት ተግባር በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። የአንድ ተግባር አግባብነት በዚህ መልኩ የሚወሰን ከሆነና የሕብረተሰቡ የሞራል እሴቶች’ም ከዚህ አንፃር የተቃኙ ከሆነ፤ የሰው ተፈጥሯዊ መብት በተረዳውና በፈቃዱ መሰረት የመንቀሳቀስ ነፃነት ሲሆን፣ በእንቅስቃሴው ውስጥ የሌሎች ሰዎች ነፃነት እንዳይጣስ ማድረግ ደግሞ ግዴታው ይሆናል። በዚህ መሰረት፣ መብትና ግዴታ ሲባል ነፃነት እና ስለ ነፃነት እንደማለት ይሆናል።

ነገር ግን፣ ነፃነት፣ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ መብትና ግዴታ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነት ጋር የተቆራኘ ነው። “ሰብዓዊ መብት” የሚለውን አገላለፅ በተደጋጋሚ ሲባል የምንሰማውና የተለመደ አገላለፅ ቢሆንም፣ ፅንሰ-ሃሳቡን በጥልቀት ስንመረምር፣ በነፃነት የሚረጋገጠው “የሰው መብት” ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነት በእራሱ “ሰብዓዊነት ወይም ሰው-መሆን” እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

በመጀምሪያ፣ “ሰው” የሚለው ቃል “ሰብ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን “ሰብዓዊ” የሚለው ቃል ደግሞ “የሰው-የሆነ ነገርን” ያመለክታል። በመሆኑም፣ “ሰብዓዊ መብቶች” የሚለው “የሰው መብቶች” ከሚለው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያሳያል። “ሰብዓዊ-መብት” ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት እንደሆነና በውስጡ፤ ነፃነት፣ ፍትህ እና እኩልነት እንዳሉ ሲጠቀሱ መስማት የተለመደ ነው። ሆኖም ግን፣ በዩሃንስ እጅጉ የተዘጋጀው “human rights” የሚለው የሚሉው “የእያንዳንዱ ሰው ‘ነፃ’ የመሆን መብት” የሚል ትርጓሜ አለው። ይህ ለሰው-ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው መብት ‘ነፃነት’ ስለመሆኑ ይጠቁማል።

በመቀጠል፣ “ሰብዓዊ መብቶች” የሚለውን ስናይ ‘ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ የሚገኙ መብቶች’ ማለት ነው። “ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ” ሲል፣ መብቱ ‘ሰው-ከመሆን’ ጋር የተቆራጀ ስለመሆኑ ያሳያል። ምክንያቱም፣ የ“ሰብዓዊ-መብት” ባለቤት ለመሆን “ሰው-መሆንና ሰው-መሆን ብቻ በቂ ሲሆን፣ “ሰብዓዊነት” (humanity) ደግሞ “ሰው-መሆን፣ የሰብዓዊነት/የሰውነት መለያ ባሕሪያት ወይም ብቃቶች’ የሚል ትርጓሜ አለው።

ነገር ግን፣ “ሰብዓዊነት” በሚለው ስር የተገለፀው የሰው-ልጅ መለያ ባሕሪ ወይም ልዩ ተፈጥሯዊ ብቃት፣ እና ከነፃነት ጋር ያለው ተያያዥነት ምንድንነው? ከላይ በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው፣ ሰው በስሜት ህዋሳቱ አማካኝነት የተገነዘበውን እውነታ በምክንያታዊ አስተሳሰብ ያገናዝባል። በዚህም፣ በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት በማስተዋል፣ በማነፃፀርና በማመሳከር ነባራዊ እውነታን ከሌሎች እንስሳት በተሻለ መረዳት ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ነባራዊ እውነታን ለመረዳትና በተረዳው መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ይወስናል። ስለዚህ፣ “ፈቃድ” እና “መረዳት” የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ናቸው። በራስ ለመፍቀድ መረዳት፣ በራስ ለመረዳት ደግሞ መፍቀድ አስፈላጊ ስለሆነ ፈቃድ እና መረዳትን በጥምረት ካልሆነ በስተቀር በተናጠል ማየት አይቻልም። የእነዚህ ሁለት ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጥምር ውጤት ደግሞ “ነፃነት” ነው። በመሆኑም፣ “ነፃነት” የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው።

በአጠቃላይ፣ ነፃነት የሕይወት ትርጉም እና ፋይዳ ነው። የሰው-ልጅ ለሕይወት ያለው ስሜት አንፃራዊ ነፃነቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የሚገለፅ እንደመሆኑ፣ ነፃነትን መገንዘብ የማይችል ሰው ሕይወትን መገንዘብ አይችልም። ሀብት እና ድህነት፤ መፈለግ እና አለመፈለግ፤ ሃይል እና ተገዢነት፤ ጤና እና በሽታ፤ አዋቂነት እና አላዋቂነት፤ ጥጋብ እና ረሃብ፤ ጥሩ እና መጥፎ፣…ወዘተ፣ ሁሉም አንፃራዊ የነፃነት ማነስና መጨመር ውጤቶች ናቸው።

https://ethiothinkthank.wordpress.com

Advertisements