ሳሰለጥኑ ለሰየጠኑ ኢትዮጲያዊያን … ከቆሪጦች

በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ በቅኝ-አገዛዝ በሃይል የተጫነን፣ በምዕራባዊያን ነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተን የትምህርት ስረዓት፣ እኛ ኢትዮዺያዊን በራሳችንን ፍቃድ በህዝባችን ላይ የጫንን፣ ቅኝ_አገዛዝን በሃይል ተከላክለን፣ የአስተሳሰብ ባርነትን ከፍለን ኢምፖርት ያደረግን በአለም የመጀመሪያዎቹ ህዝቦች ነን። ይሄው የአንድ ክፍለ ዘመን ትውልድ የሀገሩን ነባራዊ እውነታ በሽውራራ እይታ እያየ በድህነት አረንቋ ተዘፍቆ አለ። የእኛ ዘመናዊ ትምህርት  “መሰልጠን” ሳይሆን “መሰይጠን” እንደሆነ የተረዱ በጣም ጥቂት ፈርጦች፣ ሰለጠንኩ ብሎ ለሰየጠነ ህዝብ የሆነውን ለማስረዳት እድሜያቸውን ከብዕርና ወረቀት ጋር ተጣብቀው አሳልፈዋል። በአምላክ ዘንድ በመጥፎነት የተፈረጀ ሁሉ በሰይጣን ዘንድ መልካም ነውና ለሰይጣን እንዴትስ ብለው ቢነግሩት ሰይጣንነቱን ይረዳል? ይህ ባይሆንማ ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሌላ ነጋሪ አይሻንም ነበር። ለማንኛውም ነፍስ የገዛ ሴይጣን ካለ “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” ከሚለው የሎሬቱ ግጥም የተቀነጨቡ ጥቂት ስንኞችን እኛ ቆሪጦች፣ የሴይጣን ወንድሞች እንሆ በረከት ብለናችሗል።
“…
አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፥ እጄን በትዝታሽ ያዢኝ
በሕልም ጣቶችሽ ሳቢኝ
መቼም…በውን አልሆንሽም፥ እንዲያው በሰመመን ዳሺኝ
የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም
የኔ ክንድ እኮ ተልም አይተልምም
የኔ ጣት አረም አይነቅልም
በፊደል መፈደል በቀር፥ ጉልጓል እኮ አይጎለጉልም፥
ለስልሻለሁ፥ ሰልጥኛለሁ፥ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም

አቴቴ ዱብራ ቦረና …
አጥንቴ ከአጥንትሽ ማዕድን፥ ቢመነጭም ተቀምሞ
ከ”ሀና” ከ”አሐዱ” በፊት፥ ከቃል በፊት አስቀድሞ
ዛሬ በዓይንሽ በዓይኔ መሀል፥ አጉል ስልጣኔ ቆሞ
ሰየጠንኩና አልሆንሽ አልኩ፥ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ

ፀጋዬ ገ/መድህን (፲፱፻፰፪ – ባሌ-ጎባ)፣ እሳት ወይ አበባ ገፅ 91-93

ethiothinkthank.com