የስርዓት ጠባቂዎችና የለውጥ ናፋቂዎች

ምንም እንኳን እነዚህ ሁለት ሃይሎች በመሪዎቻቸው የሚወከሉ ቢሆንም በተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው በዋናነት ተሳታፊ የሚሆኑት መሪዎቹ አይደሉም። በተለይ በአፍሪካ መንግስት ማለት የሀገሪቷን የፖሊስ፥ የጦርና ደህንነት ሃይሎች፣ የፋይናንስ እና የመረጃ አውታሮችን የተቆጣጠሩ የተወሰኑ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው። ስለዚህ፣ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የስረዓቱ ጠባቂዎች ሆነው የሚሳተፉት የገዢ መደቡ     አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም ቅጥረኛ ፖሊሶችና ወታደሮች ሲሆኑ የለውጥ ናፋቂዎች ሆነው የሚቀርቡት ደግሞ የስርዓቱ ተቃዋሚዎች ፖርቲ/ቡድን አባላትና ደጋፊዎች ናቸው።

በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በተግባር ተሳታፊ የሚሆኑትና ነባራዊ እውነታን የሚጋፈጡት የስረዓቱ ጠባቂዎች እና የለውጥ አራማጆች የሆኑ ብዙሃን ናቸው። በመሪነት መዋቅሩ ወደ ላይ ከፍ እያሉ በሄዱ ቁጥር ከነባራዊ እውነታው እየተነጠሉ ይመጣሉ።

በመሪነት ያሉ የፖለቲካ ሰዎች ከገሃዱ አለም የተነጠሉ ሲሆን በአመራር መዋቅሩ ጫፍ ላይ ያሉ ግለሰቦች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ውሳኔውን ተግባራዊ ከሚያደርገው አካል ፍላጎትና ምርጫ ጋር ፍፁም የተለየ ነው። በፖለቲካዊው እንቅስቃሴ በእውን ተሳታፊ ያልሆነ አካል ሌሎቼ እንዲሳተፉ ይወስናል። በዚህም፣ የተወሰነ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የዘረጉትንና ጥቅማቸውን የሚያስከብር ስርዓት ህልውናን በብዙሃን እንቅስቃሴ እና መስዋእትነት እንዲጠበቅ ያደርጋሉ።

አላማው ስርዓቱን ለመጠበቅ ሆነ ለመለወጥ፣ ውሳኔ የሚሰጠው በእነዚህ ከነባራዊ እውነታ በተነጠሉ መሪዎች እስከሆነ ድረስ፣ ውሳኔዎቹ የእነሱን ፍላጎትና ምርጫ (ነፃነት) ከማስጠበቅ ውጪ፣ የስርዓቱ ጠባቂ ወይም የለውጥ ናፋቂ በመሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴው የሚሳተፈው ህዝብ ግን ከአገልጋይነት ያለፈ ሚና የለውም።

ethiothinkthank.com