“ነፃነት ወይም ሞት!”

በአስተሳሰብ ባርነት ስር ያለ ማህበረሰብ የሕይወት ትርጉም እና ፋይዳ አይገባውም። ይህ እንዲሆን፣ በቅድሚያ የነፃነት ትርጉምና ፋይዳ ሊገባው ይገባል። የነፃነት ትርጉም የሌሎችን ነፃነት በማይፃረር መልኩ በራስ ግንዛቤ፣ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መቻል ነው። ሰብዓዊነት (Humanity) ማለት የሰው-ልጅ መለያ የሆኑ ልዩ ባህርያት ሲሆን “ሰው” በተፈጥሮ ያለው አንድና ልዩ ባሕሪ በምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚመራ ፍጡር መሆኑ ነው። ምክንያታዊ ፍጡር መሆን፣ በራስ ግንዛቤ፣ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው። ስለዚህ፣ በራሱ ግንዛቤ፣ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችል ፍጡር “ሰው” በሚለው የክብር ስያሜ ሊጠራ አይገባውም። በአጠቃላይ፣ ነፃነት ለሰው-ልጅ ያለው ፋይዳ “ሰው መሆን መቻል” ነው። ምሉዕ የሆነ ነፃነትን ለመጎናፀፍ የማይተጋ ግለሰብ፣ “ሰው” ከሚለው ስያሜው በስተቀር በምክንያታዊ ፍጡርነት ለመፈረጅ የሚያስችል ባሕሪ የለውም። ባርነትን ለምዶ፣ ልማዱ አድርጎ የሚኖር ማህበረሰብ የጉዑዝ ነገሮች ወይም በስሜት የሚነዱ እንስሳት ስብስብ እንጂ “ሰው” በሚለው የክብር ስያሜ ለመጠራት የሰውነት ልዩና መሰረታዊ የሆነውን ባሕሪ አያሟሉም። በሁለት እግሩ መሄድ የቻለ እንስሳ ሁሉ “ሰው” ከተባለ’ማ ዶሮ’ም ሰው ናት። ወይም በአስተሳሰብ ሰው የሆኑና በአካላዊ አፈጣጠር ሰው የሚመስሉ በሚል ለሁለት ይከፈሉልን እንጂ “ሰው” የሆነንና የሚመስልን ባንድነት “ሰው” ብሎ መፈረጅ አግባብ አይደለም።
“ማንን ነው?”
“አንተ/ቺን ነው!”
እያልኩት ያለው “ወይ ‘ሙት’ ወይም ‘ነፃነት’ በልና ሰው-ሁን!!! There is NO in between…!!!

ethiothinkthank.com

Advertisements