የጦርነቱን’ስ በአደዋ፣ አስተሳሰቡ ግን ከአዲስ አበባ

በመሰረቱ የቅኝ-አገዛዝ ስርዓት በሁለት ደረጃዎች ይከፈላል። የመጀመሪያው አካላዊ (Physical) ሲሆን፣ በዚህም ቅኝ-ገዢው ሃይል የአንድን ሕብረተሰብ ወይም ሀገር ሉዓላዊነት በሃይል በመግፈፍ የራሱን አስተዳደራዊ ስርዓት ሲዘረጋ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አስተሳሰባዊ (Conceptual) ሲሆን በሃይል ቁጥጥር ስር የወደቀው ማህብረሰብ የነበሩትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶችና ስርዓቶችን በማጣጣል፣ በማገድና ኋላ-ቀርነታቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ ሥራዎችን በመስራት በቅኝ-ገዢው ሃይል እሴቶችና ስርዓቶች እንዲተኩ ማድረግ ነው። የሃይል አገዛዝ የአስተሳሰብ ባርነት ከሌለ በራሱ ሊቆም አይችልም።

በአፍሪካና በሌሎች የኢሲያ ሀገራት የነበረው የቅኝ-አገዛዝ ስርዓት፤ በቅድሚያ በሃይል የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በመጣስ በሃይል ሕዝቡን መቆጣጠር፣ በመቀጠል ሕዝቡን በአስተሳሰብ ባርነት ስር እንዲወድቅ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነበር። የአስተሳሰብ ባርነት የሚመጣው በዋናነት የትምህርት ስርዓት በመቀየር ለዘመናት የተከማቸን ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና ተለያዩ የስነ-ዕውቀት እሴቶችን በኋላ-ቀርነት በመፈረጅና ከሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲጠፉ በማድረግ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው፣ በተሳሳተ እሳቤ እና ከሀገሪቱ ነባራዊ እውነታው ጋር ምንም ዓይነት ተያያዥነት በሌለው ሁኔታ ውስጥ የተቀረፀን የትምህርት ስርዓት በቁጥጥር ስር ባዋሉት ህዝብ ላይ በመጫን ነው። በዚህ መልኩ በትውልድ ላይ የተዛባ ስነ-ዕውቀት መፍጠር ከተቻለ አስተሳሰባዊ ባርነት ይነግሳል። የአስተሳሰባዊ ባርነት በነፃነት ብስባሽ ላይ የሚበቅል አራሙቻ ነው።

በቅኝ-አገዛዝ ስር ወድቀው የነበሩ ሀገራት በሙሉ፣ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በቅድሚያ በሃይል ቁጥጥር፣ ቀጥሎ ደግሞ በአስተሳሰብ ባርነት ስር እንዲወድቁ በማድረግ የሀገራት ልዓላዊነትና የሕዝቦች ነፃነት ለዘመናት ተገፏል። ወደ ኢትዮጲያ ስንመጣ ግን ጉዳዩ የተለየ ነው። በቅኝ-አገዛዝ ስር ሊጥላት የመጣውን ወራሪ ሃይል አደዋ ላይ አሸንፋለች። በአስተሳሰብ ባርነት ግን የኢትዮጲያ ሉዓላዊ መንግስት አስተዳደር በአለም ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ትውልድ አደንዛዥ የሆነ የባርነት ስርዓት ዘርግቷል። ኢትዮጲያ የአስተሳሰብ ባርነትን ከአውሮፓዊያን ቅኝ-አገዛዝ ሃይሎች እንደ ሸቀጥ ገዝታ አምጥታ በህዝቧ ላይ የጫነች ብቸኛዋ ሀገር ናት።

ጣሊያን በቆየባቸው አምስት አመታት እንኳን፤ ቡና አፍይዋን “ባሬስታ”፣ የቡና ጀበናን በማሽን ቀይሮ ሄዷል። ቡና የሚጠጣ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብ በሚበላበት ሀገርን የቡና አፈላል ስርዓት እንዳልነበር አድርጎት ቢሄድም ቅሉ፣ የተማረው የሰው ሃይል ይህን ሃቅ ከ70 አመታት በኋላም አልተገነዘበውም። ለምሳሌ፣ እያንዳንዳችን ቤት ቡና የሚፈላው በጀበና እንደሆነ ግልፅ ነው። “በሁላችንም ቤት ያለው የቡና አፈላል ስርዓት በሆቴሎቻችንና መናፈሻዎቻችን እጅግ ውድ በሆነ የጣሊያን ማሽን ለምንና እንዴት ተቀየረ?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው አጋትሟችኋል። እ..ሺ ይሄ ይቅር!

ከጥቂት አመታት በኋላ “የጀበና ቡና” የሆቴሎችን የማሽን ቡና ከገበያ እሰዎጥቶታል። መልካም፣ ይሄ የወደ ቀልባችን የመመለሳችን አንዱ ምልክት ነው። ነገር ግን፣ አንድ በገበያ ጥናትና ምርምር ሞያ  የተመረቀ ባላሞያ በጀበና-ቡና አዋጭነት ላይ አንድ ጥናታዊ ሥራ ለመስራት ቢፈልግ፣ ጥናቱን እንዴት የሚያከናውን ይመስላችኋል? እዎ…እኔ ልንገራችሁ፣….ከጥናቱ ከመጠይቅ በስተቀር ሌላው ፁሁፍ በሙሉ የሚፃፈው በእንግሊዝኛ ነው። ለምን? ለእንግሊዞች የሚያካፍለው ዕውቀት ኖሮ ወይስ ሥራውን ወደ እንግሊዝ ሊልከው? ያም ሆነ ይህ፣ እንግሊዞች በሸፋፋ እንግሊዘኛ የተፃፈ ጥናታዊ ፅሁፍ አያሻቸውም። ምክንያቱም እንግሊዞች በአንድ አመት ብቻ በታወቁ የጥናታዊ መድረኮች ላይ የሚቀርቡ ከ90 000 በላይ ጥናታዊ ፁሁፎች አሏት። ኢትዮጲያስ? ካላችሁ፤ በአንድ አመት በአማካይ 300 የሚሆኑ ጥናታዊ ፁፎች ያቀርባሉ። ለመሆኑ? እኛ በደሃ ገበሬ ወዝና ግብር የተማርን ኢትዮጲያኖች፣ ያወቅነው ዕውቀት ኢትዮጲያ ካለባት፣ ከህዝቧና ሀገሪቷ ነባራዊ ችግር ጋር ተያያዥነት አለው?

አሁን…ይሄ የዕውቀት ሸርሙጣ የሆነ ትውልድ አደዋ ላይ መስዋዕት ከሆኑት አባቶች ጋር ይተዋወቃል። እንደዚያ ፈረንጅን ይንቅና ይጠየፍ የነበረ ትውልድ እንዴት አብራኹ እንዲህ የፈረንጅ አሽቃባጭ ሊሆን ቻለ??? አዕምሮውን አስቶ፣ ዕውቀቱ እውነታን እንዳያይ ጋርዶት፣ እውነት ተገላብጦበት፣ ነፃነትን ባርነት አድርጎ ማየት ካልጀመረ በቀር፣ እንዴት የአሉላ ልጅ ከግራዛይኒ ሀገር ጣሊያን ለመሄድ ሲል በባህርና በረሃ ይሞታል? ዕውቀቱ ማንነቱን እንዳያውቅ አድርጎ ካላደነዘዘው በቀር፣ እንዴት ጀግና ልጅ እንዲህ የፈረንጅ አሽቃባጭ ይሆናል?

የአደዋን ድል መዘከር፤ “የማያፀድቅ ፀሎት፣ ይዳርጋል ለቅስፈት!” እንደሆነ ለነገርከኝ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ወዳጄ….“ነፍስ ይማር” ብዬሃለው።

ethiothinkthank.com

Advertisements