የፖለቲካ “ሃይል” ብዙሃን “ነፃነት” ልዋጭ ነው!

በመሰረቱ “ነፃነት” (Liberty) ማለት ‘ያለ ምንም ውጫዊ ሃይል አስገዳጅነት በራስ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው’። መሪዎቹ በራሳቸው ፍላጎት እና ምርጫ መሰረት ስርዓቱን ለመጠበቅ ወይምለመለወጥ ያስችላል ያሉትን ውሳኔ ይሰጣሉ። ይህ የመሪዎቹን ነፃነት ለማስጠበቅ የተሰጠን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድርግ በስርዓት ጠባቂነት ወይም በለውጥ አራማጅነት ለመንቀሳቀስ የሚወስኑ ግን ከነፃነት ሳይሆን የጥገኝነት፣ ተገዢነት ወይም የባርነት ናፋቂዎች ናቸው።

የስርዓት የመጠበቅ ወይም የመለወጡን ተግባራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ የአመራርነት እርከን ላይ የሚገኙ ሰዎች የትግሉን እንቅስቃሴ በራሳቸው እሳቤና ግንዛቤ መሰረት ትክክልና አግባብ እንደሆነ ባመኑበት መንገድ እንዲካሄድ የመወሰን ስልጣን አላቸው። ነገር ግን፣ ሰዎች ምክንያታዊ ፍጡር እንደመሆናቸው ፍላጎታቸውና ምርጫዎቻቸው ከራሳቸው እሳቤና ግንዛቤ አንፃር የተቃኙ ናቸው። ሰው በማያውቀውንና በእሳቤው ውስጥ ኖሮ ስለማያውቀውን ነገር ፍላጎት ሊያድርበትና ምርጫው ሊያደርገው አይችልም። ስለዚህ፣ የስርዓቱ ሆነ የለውጥ መሪዎች የሚወስኑት በእነሱ እሳቤና ግንዛቤ መስረት ትክክል ነው ብለው ያመኑትን ነገር ነው። በዚህም፣ የራሳቸውን ፍላጎትና ምርጫ በብዙሃኑ አባላትና ደጋፊዎች ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋሉ። የፖለቲካ ሃይል በዚህ መልኩ የራሳቸውን ፍላጎትና ምርጫ በብዙሃን ዘንድ እንዲተገበር ማድረግ መቻል። የፖለቲካ መሪዎች ይህ ሃይል እንዲኖራቸው ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል በመሪዎቹ ፍቃድና ውሳኔ መሰረት ሲንቀሳቀስ ነው። መሪዎቹ አንድን ነገር በራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ መሰረት በብዙሃኑ እንዲተገበር ማድረግ የሚያስችል ሃይልን (Power፦ አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የሚያስችል አቅም) ሲያጎናፅፋቸው፣ በሌላ በኩል፣ ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍልን በራስ ፍላጎትና ምርጫ የመንቀሳቀስ ነፃነትን ይገፋል። የፖለቲካ ሃይል በብዙሃኑ ህዝብ ባርነት የተገኘ የመሪዎች ነፃነት ነው።

በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች እንቅስቃሴውን በአካልና መንፈስ ተግባራዊ የሚያደርገው ብዙሃኑ ህዝብ ካለበት ነባራዊ እውነታ ፍፁም የተለየ ሲሆን መሪዎቹ በእንቅስቃሴው በቀጥታ ተሳታፊ አይደሉም። ሊዮ ቶልስቶይ፣ “ሰብዓዊ የሆነ ፍጡር እንዴት ሀገርን በመውረር የብዙ ሰው ሕይወት የሚቀጥፍ  ጦርነትን ያውጃል?” ለሚለው መሰረታዊ የሞራል ጥያቄ ምላሽ ያገኘው በዚህች ክፍተት ውስጥ አሾልቆ በመመልከት ነበር።

እውነትም…እንደሚሞት እያወቀ ማን ወደ ጦርነት ይገባል? ወደ ጦርነት ለመግባት የሚወስነው መሪ ጦርነቱን በተግባር የሚዋጋው ሰውዬ ስላልሆነ  ነው። ኢሳያስ አፍወርቂ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን በተጀመረ የመጀመሪያዋ ቅፅበት እሱ ራሱ ፊት ቀድሞ እየተኮሰ የሚዋጋ ቢሆን ኖሮ 70,000 ህዝብ ያስፈጀውን ወረራ ይፈፅም ነብር?

ethiothinkthank.com

Advertisements