ቅምሻ…

…‘ሲወለድ የተረገመ ነው’ ሲሉኝ እሰማ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ጠል ያለ ሜዳ ላይ የራሴን ስም ከፍ አድርጌ ጠራኹ።
“መዝገቡ!… መዝገቡ!!…መዝገቡ!!!“
“መ…ዝ…ገ…ቡ!“ የሚገርም ስም ነው!
“መዝ…መዘዝ“ ሊሆን ይችላል። “መዘዘኛ!“ ለማለት። “…ገጣባ!፣ ቡ…ቡቃያ“ ሲጠቃለል “መዘዘኛ የሆነ፣ ገና ካሁኑ የተገጠበ ቡቃያ!“ አሁን ካልጠፋ ስም ይሄን ይሰጡኛል? ሌላ..ሌላ ስም ጠፋ’ዴ? ለምሳሌ፣ ለምን “እግዜር“ ብለው አይጠሩኝም። እሱ እንደ’ኔ ቁጭ ብሎ ከማየት ሌላ ምን ሰራ? ወይም ደግሞ ካደኩ በኋላ ለምን ‘የራስህን ስም አውጣ’ አይሉኝም ነበር?

ሳስበው ታዲያ ስሜ ትክክል መሰለኝ ። ትንሽዬ ያልገባኝ ‘መዘዘኝነቴ’ ነበር። ይህንንም ግን ቆይቶ ሳስበው ትክክል ነው። ‘መዘዘኛነቴን’ ልክ ሆኖ አገኘሁት። የእንጀራ እናቴ ሲዖል ስትወርድ እግዜር በኔ ነገር ክስ ያቀርብባታል። ታዲያ እሳት ውስጥ ቆማ “ያ መዘዘኛ ልጅ ነው ለዚህ የዳረገኝ! ያ…መዘዘኛ ልጅ ነው….“ ማለቷ አይቀርም። አመሏ ሆኖ ማላከክ ትወዳለች። መዘዘኛው መዝገቡ ነው ማለቷ አይቀርም። ስሜን ሁልግዜ ስትጠራው እየተነጫነጨች ነው።

እ..ህህህ። የኔን ስም ነገርኳችሁ አይደል? ደሞ ስለ አባቴ ስም ልንገራችሁ። የአባቴ ስም ለኔ ለራሴ ይከብደኝ ነበር። ስለሚያስቀኝ እንኳን ልጠራው አልፈልግም። እኔ ግን የሱ አይነት ስም ቢኖረኝ በእግሬ ነው፣ ያ…ውም በእግሬ ካርቱም ወይም ወደ ሌላ…ወደሚቀርበኝ አገር እሰደድ ነበር።

በየቀኑ ለሥራ እየወጣ-ሲገባ፣ ሳያንገራግር፣ እኔ በሆዱ ሊነጫነጭ ይችላል፣ አላውቅም፣ ግን በዝምታ ሲበላ ሳየው፣ ስሙ እንዴት እንዳላማረረው እየገረመኝና በሱ ምትክ እኔ እተክዛለሁ።

በተለይ አንዳንድ ቀን ለብቻዬ ሆኜ፣ ድምፄን ዝቅ አድርጌ ስሙን እየደጋገምኩ ስጠራው፣ መጀመሪያ እንደ ቀልድ ያስቀኝና እየቆየ…እየቆየ ደ’ሞ ጣዕም እንደሌለው የሳንጋቱራ ዶፍ ይሆንብኛል። የሆ…ነ እ… አንብቤ የጨረስኩት የጋዜጣ ቅዳጅ በድንገት ከእጄ አምልጦ መሬት ሲወድቅ የሚሰጠው ዓይነት ስሜት….አዎ፣ “ዱብ-አለ…’ዱባለ'” ነው ያባቴ ስም።

…እኔ ግን ሳስበው ሰሞኑን የምሞት…የምሞት ይመስለኛል። ምክንያቱም፣ አንደኛ በአባቴ ስም እቀልዳለሁ። በራሴ ስም እቀልዳለሁ። ምክንያቱም ጤነኛ ልጅ ስልክ እንጨት ስር ተጎልቶ አይውልም። ምክንያቱም ጤነኛ ልጅ ከሰው ኋላ-ኋላ እየተከተለ ጀርባ ላይ ያረፈ ዝንብ አያጤንም። ምክንያቱም ጤነኛ ልጅ ብቻውን አይስቅም። ምክንያቱ….ም ጤነኛ ልጅ በሣምንት ሰባት ቀን ምሳውን የተንገረገበ ወይም የተቆላ ሽንብራ አይበላም።

እን…ዴ! ሽብራ ብል ት…ዝ አለኝ። እኔን የመምታት ወስፋት ማን እንደሰጣት፣ ከየት እንዳገኘችው እኔ እስከዛሬ ድረስ አላውቅም። እኔም ደግሞ ፈርዶብኝ እሷ አጠገብ ስሆን የማጠፋው ነገር አላጣም።

እንጀራ እናቴ ስትቀጣኝ በሁለት የአመታት ስልቶች ነበር። ጠርታኝ ተጠንቅቄ የምትመታኝና ሳልጠነቀቅ የምትመታኝ። ጠርታኝ ስትመታኝ በጥፊ ነው። በቀኝ እጇ ግራ ጆሮዬ ላይ “ጯ…ዋ“ ታደርገኛለች ይዛ…። በሷ ጥፊ ሰበብ መሰለኝ፣ ይሄው ይሄኛው ግራ ጆሮዬ ከቀኝ ጆሮዬ፣ ማሪያምን፣ ቀርፈ…ፍ ያለ ነው። አስጠንቅቃ ስትመታኝ ግን በኩርኩም ነው። ወይኔ! ቅድም ሣምንቱን ሙሉ የተንገረገበ ሽንብራ እንደምታበላኝ ነግሬያችኋለው አይደል? ኩርኩሟ ደግሞ እንደ መድፍ ነው። ይዛ ‘ገጭ’ ስታደርገኝ፣ የበላሁት ሽንብራ ሆድ-እቃዬ ውስጥ እንደ ፅናፅል ‘ሿ…ሿ…ሿ” ይላል። ወይኔ ጉዴ!…
፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣
ግራጫ ቃጭሎች ከተሰኘው የአዳም ረታ መፅሐፍ የተወሰደ።
===========
የአዳም ረታን ብቃት ለመግለፅ የሚያስችሉ ቃላትን ስመርጥና ሳማርጥ ከርሜ “በቃላት የማይገለፅ…” ብዬ አለፍኩት!
፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦፦

ethiothinkthank.com