የግለሰብ እና ቡድን መብትን አስመልክቶ ከImmanuel Kant ጋር የተደረገ ምንባዊ ውይይት፡ (ካለፈው የቀጠለ…)

እኔ፡ “Mr. Kant… ሰላማዊ ፀጋዬ እና ተሾመ ከበደ የተባሉ ጓደኞቼ እንዳንተ ያሉ የምዕራቡ አለም ፈላስፎች ስለ ሰው-ልጅ “መብትና ነፃነት“ ያላችሁ አመለካከት ጠባብ እና ውስን እንደሆነ ይገልፃሉ። እኔ’ም ትላንት በተወሰነ ደረጃ ነገሩን ለመነካካት ሞክሬ ነበር። ነገር ግን አንተም ትኩረት የሰጠኸው አይመስለኝም።“

Kant፡ “ስዩም…ለማለት የፈለከው ነገር ሳይገባኝ ቀርቶ ወይም ትኩረት ለመንፈግ ፈልጌ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ያነሳኸው ሃሳብ ጭራሽ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ስላልሆነ ነው። ትላንት “እኛ’ጋ ‘የቡድን መብት’ የሚባል ነገር አለ”  ስትል፣ “እዚያ ሰዎች ይኖራሉ ወይ?“ የሚል ጥያቄ ጠይቄህ ነበር?

እኔ፡ “ አዎ!…ምን ለማለት ፈልገህ ነበር?“

Kant፡ “አየህ የነ ሰላማዊት እና ተሾመ፣ እና ሌሎችም፣ “በእኛ ማህብረሰብ ውስጥ ….“ በሚል የሚያነሱት ሃሳብ በአፍሪካ ወይም በኢትዮጲያ ያለው ማህብረሰብ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ፍጡር ስብስብ ሳይሆን “የከበት መንጋ“ ወይም ነፃነት የማይገባውና የማይገባው ግዑዝ ነገር እንደሆነ የሚያንፀባርቅ ነው።“

እኔ፡ “ኧ………….!!!! እኔ ጠፋሁ……እንዴት….እንዴት ብትደፍረኝ ነው አንተ! ምን….ስታዬኝ ጭላዳ ዝንጀሮ መሰልኩህ? ወይስ እንደ ተቀመጥክበት ወንበር ግዑዝ ሆንኩብህ?…..ስማ’ጂ Kant! ነገረኛ!“

Kant፡ “አትቆጣ’ጂ! ሲጀመር እኔ ያልኩት እነ ሰላማዊትና ተሾመ ባነሱት ሃሳብ እንደዚያ አይነት ሃሳብ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ለመጠቆም እንጂ የአንተንም ሆነ የእነሱን ሰብዓዊነት ለማጣጣል አይደለም።”

እኔ፡ “እኮ እንዴት?…አንዴት ነው የመብትና ነፃነት እሳቤን ከሰብዓዊነት ጋር ያገናኘኸው? “የአንተ የመብትና ነፃነት ፅንሰ-ሃሳብ በግለሰባዊነት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ግንጥል እሳቤ ነው“ ስላሉህ? የሰው-ልጅን ነፃነትና መብት ከማህበራዊ መስተጋብር፣ እሴት፣ አስተሳሰብ ውጪ እንደሆነ አድርገህ ማየትህ ስህተት እንደሆነ ስለነገሩህ ነው “የከብት መንጋ…ግዑዝ“ ብለህ የተሳደብከው?“

Kant፡ “እንደሱ አይደለም። ይሄውልህ ስዩም…“ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ቡድን፣….ብቻ የፈለከውን በለው፣ ከግለሰብ በስተቀር አንዳቸውም የራሳቸው የሆነ ስብዕና የላቸውም። ግለሰብ ብቻ ነው የራሱ የሆነ ስብዕና ምክንያታዊ ግንዛቤ ያለው። የቡዱኑ ወይም ብሔሩ ህልውና በአባላቱ ምክንያታዊ ግንዛቤና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው። “የቡድን መብት“ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የቡዱኑ አባላት ተመሳሳይ የሆነ ምክንያታዊ ግንዛቤ፣ ፍላጎትና ምርጫን እንዳላቸው የሚያደርግ እሳቤ ነው። ይህ ደግሞ የአባላቱን ነፃነት የሚጨፈልቅ ሲሆን ቡዱኑ ከአባላቱ ውጪ በራሱ ህልውና ሊኖረው ስለማይችል፣ በቡድን መብት ስም የአባላቱ ነፃነት ይገፈፋል። በዚህም፣ ባለመብቱን ግለሰብ ነፃነቱን በመግፈፍ መጀመሪያውኑ መብት ለሌለው ቡድን ከሰጠን፣ ማህበሩ የከብቶች መንጋ እንጂ ምክንያታዊ አስተሳሰብና ነፃነት ተፈጥሯዊ ባህሪው የሆነ ፍጡር ማህበር ሊሆን አይችልም።“

እኔ፡ “እጅግ በጣም አመሰግናለሁ ጌታዬ!“

Kant፡ “እኔም አመሰግናለሁ!…እኔ አንድ ነገር ልጠይቅህ?“

እኔ፡ “በደስታ….!?“

Kant፡ “ቅድም ሲጋራ ልታጤስ ወደዚያ የሄድክ ግዜ እሱን ፁሑፍ በጨረፍታ አነበብኩት። እስካሁን ካነሳኋቸው ሃሳቦች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ከምነግርህ ሃሳብ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ፣ በመሐል እንደ አዲስ ሰው ሃሳቤን ስትቃዎም ሳይ በውስጤ እየሳኹ ነበር? ለምንድነው?“

እኔ፡ “አዎ…ልክ ነህ! ግን አንተ በምትለው ሃሳብ ሁሉ ብስማማ ኖሮ ውይይታችን በጣም በአጭሩ ይቀጭ ነበር።

ethiothinkthank.com

Advertisements