ነፃነትን ሳያውቁ ለሚናፍቁ…፣ ነፃነት ምንድነው?

“ከምንም ዓይነት እገዳ ወይም ገደብ ነፃ መሆን” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነፃነት ግዴታ የሌለው “መብት” ነው። ሃሳቡን በግልፅ ለመረዳት የ“መብት”ን ፅንሰ-ሃሳብ በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል። የ“መብት” (right) ፅንሰ-ሃሳብ፣ “በውጫዊ እንቅስቃሴ ተግባራዊ የምናደርገው ነፃ-ፍላጎትና ምርጫ ከሁሉም ሰዎች ነፃነት ጋር አብሮ ሊሄድ በሚችል መልኩ መሆን አለበት” በሚል እሳቤ ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። ፅንሰ-ሃሰቡ ሦስት መሰረታዊ መርሆች አሉት።

አንደኛ፡- መብት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ በሚችሉ ግለሰቦች መካከል የሚኖርን ውጫዊ እና ተግባራዊ ግንኙነትን ብቻ የሚመለከት ነው።

ሁለተኛ፡- መብት፣ አንዱን ተግባር ከሌላ ግለሰብ ተስፋና ፍላጎት ጋር ያለውን ግንኙነት ‘ጥሩ ወይም መጥፎ’ በሚል መጠቆም ሳይሆን፣ የግለሰቡ ነፃ እንቅስቃሴ ከሌላው ግለሰብ ነፃነት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው።

ሦስተኛ፡- በመብት ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት፣ ግንኙነት ከተካሄደበት ነገር ወይም ክስተት ይልቅ በግንኙነቱ ወቅት የነበረውን የተሳታፊዎች “ፈቃድ“ የግንኙነቱ መጨረሻ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከእነዚህ ሦስት መሰረታዊ መርሆች በመነሳት ነፃነት እያንዳንዱ ግለሰብ በእራሱ ፈቃድ የሚያከናዉናቸው ተግባራት ሌሎች ሰዎች በፍቃዳቸው ከሚያከናዉኗቸው ተግባራት ጋር በእውን ሊስማሙ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በአንድነት ያጠቃለለ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል።  በዚህ መሰረት፣ በፍላጎት የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም የግል ምርጫ ተቀባይነት የሚኖረው “ነፃ” ሲሆንና ከሌሎች ሰዎች ነፃነት ጋር በሚስማማ መልኩ ሲደረግ ብቻ ነው።

ethiothinkthank.com