የጥቅማ-ጥቅም ሱሰኞች!!!

አንዱ ባልደረባችን 1500 ብር ወራዊ አበል ላለው የጀማሪ ባለስልጣን ቦታ ላይ ተሾመና “የደስ-ደስ” ቢራ ልጋብዛችሁ ብሎ ወሰደን። እንደ የውሻ ሲሪያ ጓደኛ የተባለ ሁሉ ሹመቱን እያሸተቱ ከየቦታው መጠራራት ጀመረ። ሁሉም በሞቀ ፈገግታ “ሹመት ያዳብር!… ሹመት ያዳብር! ድሮም’ኮ አንተ!…አይ አጅሬ!” እያሉ ሰውዬውን ‘ሼም’ እያስያዙ ቢራቸው መሰልቀጥ ቀጠሉ…። እኔም ታዲያ 3ኛውን ጨርሼ 4ኛው ላይ ስደርስ፣ እንደው ውስጤን ፈ…ታ ፈ…ታ፣ ደስ-ደስ፣ ሞ…ቅ ሞ…ቅ አለኝ። 5ኛው ላይ ስደርስ’ማ ወፍ የለም! ስ…ክ…ር አልኹ! ያው ባለፈው እንዳልኳችሁ፣ እኔ ስሰክር የማደርገውን አላውቅም አይደል? በ…ቃ ብድግ አልኳ!

“እያንዳንድሽ! ሆዳም አሽቃባጭ ሁላ፣ የጥቅም ሱሰኛ!… ” ወደ ተሿሚው ዞር አልኩና፥
“ስማ አንተ ደ’ሞ! ‘ታንክስ ፎር ዘ ቢር’። ግን አንተም እንደሌሎቹ ሆዳም ባለስልጣን እንዳትሆን ከፈለክ በአበልህ ‘እቁብ’ ግባ!” ብዬው እየተወላገድኹ ወደ ቤቴ ሄድኩ።

በማግስቱ  ጓደኛዬ “ትላንት ለምን እንደ’ዛ አልክ?” ብሎ ጠየቀኝ።

እኔም ታዲያ በስካር ግብዣውን ጥዬ መሄዴን ለመካስ ነገሩን ሰፋ አድርጌ አስረዳሁት።
“እ…እ ከሹመቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጥቅሞችን አንዴ ከለመድክ እና እንደ ቋሚ ገቢ አድርገህ መውሰድ ከጀመርክ አንተም የጥቅም ሱሰኛ ትሆናለህ። አንድን ሱሰኛ ሰው ከሱሱን እንዲተው መክረህ ታውቃለህ? የፈለከውን በል፣ ሱሱን ካላደረሰ፣ ጭራሽ አይሰማህም። ሱሱን አድርሶ እንኳን ቢሆን ለግዜው ‘እሺ…እሺ’ ይልሃል እንጂ ምክርህን ተቀብሎ ሊተገብር ምናምን? ጭራሽ!…” ድንገት አቋረጠኝና፥
“አበል’ኮ በስራህ ወይም በሃላፊነት ደረጃህ የሚገኝ ጥቅማ-ጥቅም እንጂ ‘ጉቦ’ኮ አይደለም። አንተ ‘ሱስ’ ምናምን እያልክ ስርቆት አስመሰልከው” አለኝ።

“አልገባህም ወዳጄ!… ሱስ የሲጋራ ብቻ አይደለም። እንደ የወንበር አበል፣ የነዳጅ፣ የስልክ፣ የአልጋ (800 ብር?)፣ የቤት፣ የቀን ውሎ-አበል (የሴትና የገንዘብ ጉቦን ሳይጨምር) ያሉ ጥቅሞ’ኮ ከጫትና ሲጋራ የባሱ ሱሶች ናቸው። አንዴ ከለመድካቸው ያለእነሱ መኖር ይሳንሃል (ይመስልሃል)። …
…እንበልና 1500ውን ብር ለልጅህ የት/ት ቤት ክፍያ አዋልከው። ከዚያ ከስልጣንህ የሚነቀንቅ ነገር በመጣ ቁጥር በቅድሚያ ወደ አዕምሮህ የሚመጣው የአቋምህ ትክክለኝነት ሳይሆን የልጅህ የት/ት ጉዳይ ነው።

…የራሱ አቋም የሌለው ባለስልጣን ደግሞ የሰጡትን ተቀብሎ የሚፈጭ ወፍጮ እንደማለት ነው። ከበላዩ የመጣን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከመፍጨት በቀር ምን፣ ለምን፣ እንዴት፣ …ብሎ አይጠይቅም። ሱሰኛ ተግባሩ ለራሱም ሆነ ለሌሎች እንደማይበጅ ሳያውቅ ቀርቶ ይመስልሃል’ዴ? በአለም ላይ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሱሱን ማርካት ነው ስለሆነ ነው። በቃ ሱሰኛ ነዋ! አንተም የጥቅም ሱሰኛ ከሆንክ ከስልጣንህ በላይ ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር አይኖርም። በቃ እ…ል…ም ያለ ‘ካድሬ’ ሆነህ እርፍ! እን…ዴ! አብዛኛውን ካድሬ’ኮ ‘ከስልጣን ውረድ’ ስትለው የሚፈራው ምን ከመሰለ መኪና ወርድና ያለ ጫማ በባዶ እግርህ ሂድ እንደማለት ስለሚሆንበት ነው። …’የብልጦች ተላላኪ ከመሆን የቀድሞው ከብት እረኝነትህ ይሻልሃል እያልከው እኮ ነው’ አበደ’ዴ…አይሰማህም!!!…

“ትዕዛዝ ከምትጠጣ እቁብ ብትጠጣ ይሻልሃል። ከስልጣን ሊያወርዱህ፣ ህሊናህን በጥቅም እንድትሸጥ ሲጠይቁህ፣ በእቁብ ያጠራቀምከውን ይዘህ፣ ከስልጣን “ወረደ” ሳትባል ቀድመህ ትዘልና “በፍቃዴ ወረድኹ” ብለህ ከሞራል ኪሣራ ትድናለህ!!! ወዳጄ እቁብ…ጥሩ ነው። ከሱስ ያድናል።”

ethiothinkthank.com