ጌታ ፍ.ቅ.ር ሆይ…?!

“እግዚያብሄር ሰውን ‘በአምሳሉ’ ፈጠረ…”
“ኧ…¿? እግዚያብሄር በሁሉም ቦታ ለዘላለም ይኖራል፣ የተፈጥሮን ሕግ አርቅቋል፣ “ሰው” የሚባል ሟች ፍጡርን ፈጥሯል። አይደል?”     
“አዎ… ለእግዚያብሄር ምን ይሳነዋል”
“ሰው በሁሉም ቦታ ለዘላለም መኖር ይችላል’ን?፣ የተፈጥሮን ሕግ መቀየር ይችላል’ን?፣ ሞትን ማስቀረት ይችላልን?…”
“አይችልም፣ ሰው ደካማ ፍጡር ነው”
“ታ…ዲ…ያ ይሄን ደካማ ፍጡር ነው ‘በእግዚያብሄር አምሳል ተፈጠረ’ የምትለው?”
“እንደሱ አይደለም…’አምሳሉ’ ሲል’ኮ”
“የሰው-ልጅ ምኑ ነው በእግዚያብሄር አምሳል የተፈጠረው?…የሰው ምኑ እግዚያብሄርን ይመስላል? ክፋቱ?፣ ምቀኝነቱ?፣ ዘረኝነቱ?፣ አላዋቂነቱ?፣ ሟችነቱ?፣…እስኪ ምኑ…? ኤ…ዲ…ያ ይልቅ ባክህ የጥላሁንን ሙዚቃ፣ ‘አምሳሉ’ ልጋብዝህ።

የሕይወት ጥልቅ ምስጥሩና
የደስታ ትርጉም ሁሉ:
ውብት’ም ስሜትም
‘ፍ…ቅ…ር’ ብቻ’ኮ ነው ይላሉ።
ታ…ዲ…ያ ፍቅር’ስ ቢሆን
ያንቺ’ኮ ነው ‘አምሳሉ’።
የፍቅር ውሉ፡
ስሜቱ ሁሉ፡
ነሽ አምሳሉ።”
“እግዚያብሄር ፍቅር ነው።”
“የፍቅር ውሉ…ስሜቱ ሁሉ: …ኧ?”
“እግዚያብሄር ፍቅር ነ…ው!”
“ምን አልክ…?”
“ስምተሃል!”
“ነሽ አምሳሉ! ‘ነ…ሽ’!? ከመቼ ጀምሮ ነው እግዚያብሄርን ‘በችክ’ አምሳል መግለፅ የጀመርከው ባክህ?”
“ኧረ ይቅር ይበልህ። በስመ አ…ብ! እኔ እንደዛ አልወጣኝም!!!”
“የእግዚያብሄር አምሳል ሰው ውስጥ ቢኖር እንኳን በሴት ላይ ነው። እንጂ በወ…ን…ድ ላ…ይ ቁራጭ ታክል የጌታ አምሳል አይኖርም።”
“ለምን ሴት ብቻ? እንደውም ሄዋን’ኮ…”
“ተውተውተው…እንዳጨርሰው! እግዚያብሄር ማዘን ካለበት ወንድን በመፍጠሩ መሆን አለበት። እንደ…ው…ም  ‘…በምድር ላይ የተሰራውን ጥፋት ባዬ ግዜ እግዚያብሄር ሰውን በመፍጠሩ ክፉኛ አዘነ’ የሚል በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ መሰለኝ?!”
“ሳይኖር አይቀርም…”
“እግዚያብሄር መጀመሪያ የፈጠረው ሰው ማን ነው?…አዳም አይደል?”
“እህ…?”
“አዳም ደግሞ ወንድ ነው። ስለዚህ እግዚያብሄር ማዘን ካለበት ሚስተር አዳምን በመፍጠሩ መሆን አለበት እንጂ ‘ሄዋን ከመድረሷ ቅጠል በጥሳ ጉድ ሰራችው የሚለዉ አድቬንቸር’ አይገባኝም!”
“ምነው አንተ ሴቶችን ቅዱስ ፍጥረት አስመሰልካቸው? ወንድም ሆነ ሴት ሁለቱም እግዚያብሄር በአምሳሉ የፈጠራቸው ናቸው።”
“ፋብሪካው አንድ ይሁን’ጂ ‘Operating System’ቸው ይለያያል።”
“የምንና ምን?”
“የወንድና ሴት”
“ሃሃሃ…የማታመጣው የለ! እንዴት ባክህ?!”
“አየህ…ሴት በማህፀኗ አስባ በፍቅሯ ትገዛሃለች። ወንድ ደግሞ በስሜቱ እያሰበ፡ በጉልበቱ ሊገዛህ ይሞክራል”
“‘ሴት በማህፀኗ ታስባለች’ ማለት…? አልገባኝም።”
“‘በማህፀኗ’ ስል ወላድ ናት ለማለት ነው። ሁሉንም ነገሮች ከልጇ አንፃር ነው የምታያቸው። ለምሳሌ ልጇ ቢያጠፋ መክራ፣ ገስፃና ቀጥታ ምግባሩ እንዲስተካከል ታደርጋለች። የልጇ ሕይወት እንዲሰምር ያለመታከት ትጥራለች። ምንም ቢሆን በልጇ ላይ ተስፋ አትቆርጥም። በሌሎች ላይም ቢሆን እንደ ወንድ ክፋትና ውድቀትን አቅዳ አትንቀሳቀስም። ወንድ ለሌሎች ውድቀት ቦታና ግዜ ለይቶ፣ በጀት መድቦ ነው የሚንቀሳቀሰው።…
ኤጭ… ወንድ ሁሉ በቆለ* አይደል’ዴ የሚያስበው?!  “እናውቅሻለን… እናውቅሻለን” አለ መስከረም…
ተወኝ ባክህ፣ ጥልዬን ላጣጥምበት…
የፍቅር ውሉ፡
ስሜቱ ሁሉ፡
ነሽ አምሳሉ።…
ኧ…! ይሄ ነገር እንዴት ነው?”
“ምኑ?”
“እሷ የፍቅር አምሳል ከሆነችና እግዚያብሄር ደግሞ፣ አንተ ራስህ እንዳልከው፣ “ፍቅር” ከሆነ፣ ‘እሷ የእግዚያብሄር አምሳል ነች’ ማለት አይደለም?”
“የመድሃኒያለም ያለህ!!! ማ…???”
“እ…ሷ!”
“ሃ…ሃ…ሃ ማ…???”
“ሙድ እየያዝክ ነው? ብሞት አልነግርህም! ጉረኛ! ይልቅ በሰው ፍቅር መገልፈጥ ተውና፣ ቅድም ወሬውን ስንጀምር፣ ‘ከሰው-ልጅ ምኑ ነው በእግዚያብሄር አምሳል የተፈጠረ…?’ ብዬህ አልነበር?”
“አዎ…”
“ፍቅር”
“ምኑ?”
“በእግዚያብሄር አምሳል የተሰጠው ፍቅር ብቻ ነው። ከሁሉም የሰው ልጅ ባሕሪ የእግዚያብሄር የሆነው ፍ…ቅ…ር ብቻ ነው። አየህ ‘ፍቅር የእግዚያብሄር አምሳል ነው።”
…ቆይ…ቆይ ግን…እግዚያብሄር በራሱ የፍቅር አምሳል ቢሆንስ? እንደ…ው…ም…ቆይ፣ እግዚያብሄርን ማን አይቶት ያውቃል? ማንማ! ታዲያ በእውን ያየንውን ‘ፍቅር’ በገሃድ ባላየንው ‘እግዚያብሄር’ ከመመሰል ይልቅ፣ ‘እግዚያብሄርን’ በምናውቀው ፍቅር መምሰሉ አያሳምንም?”
“አንተ ግን እ…ል…ም ያለ ፍቅር ይዞሃል! ማን ናት እሷ?”
“ጌታ ፍ.ቅ.ር ሆይ! ፀሎቴን ስማ… ሃ…ሃ…ሃ”

ethiothinkthank.com

Advertisements