ግብርና – ሃይማኖት = የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት

83% የሚሆነው የኢትዮጲያ ሕዝብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ዘርፉ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ አመታዊ የምርት መጠን (GDP) ከ44 – 54% ያለው ይሸፍናል። በመሆኑም፣ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት በግብርናው ዘርፍ እድገት ላይ የተንጠለጠለ ነው።

ይሁን እንጂ፣ “እድገት“ ማለት የምርታማነት መጨመር እንደመሆኑ፣ ከዚህ አንፃር ሲታይ በኢትዮጲያ የዘርፉ ምርታማነት ከአለም የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ለምሳሌ፣ የኢትዮጲያ ግብርና አመታዊ የምርት መጠኑ 587 ዶላር በሄክታር ሲሆን፣  የኬኒያ 1190፣ የሞሮኮ 1150 ዶላር በሄክታር መሆኑ የዘርፉን ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ያሳያል።

ሀገራችን በ2025 (እ.አ.አ) መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ፣ ከግብርና ምርት 65%ቱን በሚሸፍነው የሰብል ምርት ላይ ምርታማነትን በ95% ማሳደግ የግድ ነው። የሕዝብ ቁጥር እድገቱ በዚህ ከቀጠለና ምርታማነት በተጠቀሰው መጠን ካላደገ፤ በ2025 የዘርፉ ምርታማነት በ20% ይቀንሳል፣ 50 ሚሊዮን የሚሆን የሀገሪቱ ዜጎች የምግብ ዋስትና ችግር ያጋጥማቸዋል።

ከአጠቃላይ የሀገሪቱ አመታዊ ወጪ ውስጥ ከ15 – 17% የሚሆነው ለግብርናና ገጠር ልማት የተመደበ (ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከአለም 3ኛ ወይም 4ኛ) እና ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተዛባ የንግድ ሚዛን (trade deficit) ያላት ደሃ ሀገር፣ በዘርፉ ተጨማሪ ግባዕቶችንና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን በማቅረብ ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያስችል አቅም ሊኖራት አይችልም። ስለዚህ፣ የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለማረጋገጥ ያለው ብቸኛ አማራጭ የአርሰ–አደሩን ጉልበት አሟጦ መጠቀም ነው።

ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ አርሶ-አደር ምርታማነት ከአንድ ቻይናዊ አርሶ-አደር ጋር ሲነፃፀር በ60% ያነሰ ነው። ፈጣሪ “ጥረህ ግረህ ኑር“ ብሎ፣ ከሆድ ጋር እኩል እጅና እግር በሰጣቸው ሰዎች መካከል ይህን ያህል የሰፋ ልዩነት መኖሩ ሊያስገርም ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ነገሩን በጥልቀት ከታየ ልዩነቱ በመስራት-ያለመስራት ሳይሆን ከስራ ግዜ ልዩነት የመነጨ እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው። ቻይናዊ ገበሬ በወር ውስጥ 30 ቀናት ስራውን ሲሰራ የኢትዮጲያ አቻው ግን በአማካይ 15 ቀናት ብቻ ይሰራል። ክርስቲያን አርብቶ-አደር አጋጠሞት የማያውቅ ሰው አብዛኛው የኢትዮጲያ አርሶ-አደር ገበሬ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ እንደሆነ ይረዳል።

በተለይ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በፈረዖኖች ዘመን ሲተገበር የነበረውን፤ ቀናትን በቅዱሳን ስም በመሰየምና የማክበር፣ የጥንት ግብፃዊያንን, የአምልኮ ስረዓትን በኢትዮጲያ ገበሬ ላይ በመጨን፣ እጅና እግሩን በባርነት ሰንሰለት በማሰር ለዘመናት ከድህነት አረንቋ እንዳይወጣ በማድረግ፣ የአስተሳሰብ ባርነት ጠባቃ፣ የድህነት አቀንቃኝ ሆና እያገለገለች ነው። የኢትዮጲያ ልማት በግብርናው ዘርፍ እድገት፣ የዘርፉ እድገት ደግሞ የአርሶ-አደሩን ምርታማነት በመጨመር፣ ለዚህ ደግሞ የግብፅን የባርነት ሰንሰለት በባህል አብዮት መበጣጠስ ያስፈልጋል።
******
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements