ትግራይ: እማማ ብሬ’ን ወይስ ዘርዓይ’ን??

ትግራይ…መቀሌ…ዓዲ-ሃቂ ሰፈር…ትግራዋይቷ እማማ ብሬ ግቢ ሦስት ጓደኞቼ ቤት ተከራይተው ይኖራሉ። ከጎንደር፣ አምቦ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡና የማስተርስ ድግሪ ትምህርታቸውን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ-ሃቂ ካምፓስ የሚከታተሉ ናቸው። እነዚህን ሰዎች በአንድ ላይ ያገናኛቸው ከምንም በፊት ሰውነት (ሰብዓዊነት) ነው። በመቀጠል የአከራይና ተከራይ የጥቅም ግንኙነት። ለአሁን ዘመን ፖለቲካ እንዲያመች ደግሞ ከየትኛው ብሔር እንደመጡ ልንገራችሁ፤ ወላይታ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እና ተጋሩ (ትግሬ) ናቸው።  በቅድሚያ ግን ስለ እማማ ብሬ ትንሽ ልበላችሁ።

እማማ ብሬን በጣም እወዳቸዋለሁ። እድሜያቸውን ከ60 አመት በላይ ይመስለኛል። በእሳችው አቆጣጠር ግን፣ እምናም፣ ዘንድሮም፣ በየአመቱ 53 ናቸው። አቤ…ት ደግሞ ውፍረታቸው! በጣም ወ…ፍራም ናቸው! በወጣትነታቸው ዘመን መቀሌ ከተማ ውስጥ የታወቀ ሆቴል ነበራቸው። “ዋህ…ያኔ’ኮ በቀን 30ና 40 አሩስቶ ብቻዬን እሰራ ነበር“ ይሉኛል። ዛሬ እንዲህ በሦስት እግር እንዲንቀሳቀሱ ያደረጋቸው (ሦስተኛው እግር ከዘራ ነው)፣ በተለይ ታክሲ ውስጥ የሁለት ሰው ሂሳብ እንዲከፍሉ ያደረጋቸው ይህ ቅጥ-ያጣ ውፍረታቸው ከበግና ዶሮ አሩስቶ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። (…የታክሲው ነገር’ኮ በእውነት የሆነ ነው! እማማ ብሬ ጋቢና ከተሳፈሩ ከሹፌሩ በቀር ለሌላ ተሳፋሪ የሚሆን አንዲት ጋት ቦታ የለም። እሳቸው ጋቢና ከገቡ፣ እንኳን ሌላ ተሳፍሪ መጨመር ማርሽ መቀየር በራሱ መከራ ነው! የማርሹ እጄታ ከዳር-ዳር ከተዘረጋው የእማማ ብሬ ባት ስር በስንት መከራ ተፈልፍሎ ነው የሚገኘው። አንድ ቀን የታክሲ ረዳቱ “…ዓዲ-ሃቂ…ዓዲ-ሃቂ…ሁለት ሰው!” እያለ ነበር። ታዲያ እማማ ብሬ ባንዴ ጋቢናውን ሲሞሉት አይቶ “ዋይ…ናይ ክልተ ሰብ ትከፍልኺዲያ?“ ብሎ የሁለት ሰው ሂሳብ አስከፈላቸው)

እኔ የእማማ ብሬ ግቢ ተከራይ አልነበርኩም። “ጓደኞቼ’ጋ ስሄድ ነው የወኳቸው። እርግጥ “ተው አንተ ረባሽ እብድ እኔ’ጋ ግባ?” እያሉ እሳቸው ግቢ እንድከራይ ለምነውኛል። የእሳቸው ግቢ የሚዘጋው ሦስት ሰዓት ላይ ነው። ለእኔ ደግሞ ምሽቱ ልክ በዚያን ሰዓት የሚጀምረው። ታዲያ ሁሌ ጓደኞቼ’ጋ ስሄድ “ኧሃሃሃሃ….ይሄ ረባሽ እብድ መጣ! አን..ተ! ና…ስቲ! ሰሞኑንማ አስቸግረሃል!” ይሉኛል።    ለምን? ሃሃሃሃ…. ምሳ ሰዓት ላይ “ወጥ! ወጥ ያለው? ዜድ!…ነጋሳ!…ተሼ! በናታችሁ ወጥ ካላችሁ፣ ደረቅ እንጀራ ገዝቼያለሁ?” እያኩ ግቢውን ብጥብጥ ስለማደርግ፣ (በደሞዝ የምግብ ኮንትራት አይያዝም፣ ጨጓራውን የሚፈልግ ወጥ የምትሰራ ሰራተኛ አይቀጥርም። በተለይ ማስተርስ ላይ ሁሉም የአስተማሪ-ተማሪ ሁላ ደረቅ እንጀራ በፌስታል ገዝቶ፣ ወጥ በራሱ ሰርቶ ነው የሚማረው! እኔ ደግሞ ወጥ መስራት ኡህህ ሲያስጠላኝ!)

እማማ ብሬ “አንተ እብድ!…ና…ስቲ?” ሲሉኝ፣ “ሃ…ይ ማሚ…ከመይኪ! ፒስ ነው? ምንነው?“ እያልኩ እሄዳለሁ። እዚያ ግቢ በሄድኩ ቁጥር የሚልኩኝ ነገር አይጠፋም። “አንተ እብድ እስኪ ገብሬ ሱቅ ደርሰህ’ና? ሎሚ ግዛልኝ? …ና ካርድ ግዛልኝ!?…“ ሲልኩኝ፣ ሲቆጡኝ፣ ሲያወሩኝ ደ…ስ ይለኛል። “ስማ! አንተ ረባሽ…አልታዘዝም ማለትህ ነው? ና…ስኪ ፍሬወይኒ’ጋ ደውልልኝ።…. አንተ ስልኳ ጠራች! ና..ስኪ ማን ነው የደወለው?ፍሬወይኒ ነች?“ እማማ ብሬ ፊደል አልቆጠሩም። የሞባይል ቁጥር ለይተው አይደውሉም፣ የደወለውንም ሰው ለይተው አያውቁም።

አዎ እማማ ብሬ አልተማሩም! በወጣትነታቸውን የዶሮና የበግ አሩስቶ እየሰሩ፣ አሁን ደግሞ በወጣትነታቸው ዘመን ባፈሩት ሀብት ባለ አንድ ፎቅ ቤት ሰርተው እሱን እያከራዩ ነው የኖሩት።
አዎ እማማ ብሬ፤ እንደ #ዘራይ_ሀይለማሪያም፣ እንደ #ጀዋር_መሀመድ፣ እንደ #ሴቭ_ሸዋ፣ ዘመናዊ ትምህርት የመማር እድል አልነበራቸውም። እርግጥ ነው እማማ ብሬ አልተማሩም፣ እንደነዚህ ሰዎች በዘረኝነት ልክፍት አላበዱም።

አዎ እማማ ብሬ የፈረንጅ ፊደል፣ የቅንጦት ቃል አልተማሩም። በዘረኝነት ጠበል አልተጠመቁም! እማማ ብሬ አልተማሩም፣ በድንቁርናቸው አይኮሩም! ስላልተማሩ ሁሌም የሆነ ነገር እንደቀራቸው ያስባሉ፣ በሰው ላይ በእርግጠኝነት ለመፈረጅ አይቸኩልም። እሳቸው እኔም ሆንኩ ሦስቱ ጓደኞቼ በቅድሚያ ሰዎች ነን።

እማማ ብሬ አልተማሩም፣ እንደነዚህ ግልገል ጭራቆች ከሰውነት በፊት ዘርና ሃይማኖትን አያስቀድሙም። እንደ እንስሳ የሰውን ማንነት በመንጋው ምንነት አይፈርጁም። እማማ ብሬ ዘመናዊ ትምህርት አልተማሩም፣ አልዘመኑም! አልሰለጠኑም! አልሰየጠኑም! እንደ ዘራይ፣ ጀዋርና ሴፍ ሸዋ የሰለጠኑ መስሏቸው አልሰየጠኑም። እንደነሱ “ሰው እርስ-በእርሱ እንዲጫረስ ትጉ” የሚል አጋንንት በእሳቸው ላይ አልሰፈረም።

ለእኔ “ትግራይ” ሲባል በቅድሚያ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው እማማ ብሬ እንጂ ዘርዓይ አይደለም። ምንም ቢሆን አንድ ማህብረሰብ በጤነኛ እንጂ በእብድ ሰው አይመሰልም!!!
*****************************
(ለዚህ ፁሁፍ መነሻ የሆነው በ”Tsegaye R Ararssa” እና “Zeray Halemariam መካከል ተደረገ የተባለው የመልዕክት ልውውጥ ነው። ውይይቱ በእውን የተደረገ ይሁን-አይሁን የፅሁፉ ሃሳብ በይፋ ተንፀባርቋል። ስለዚህ፣ “ዘርዓይ ሀይለማሪያም” የሚለው “Zeray Halemariam” የሚባለውን ግለሰብ ወይም የእሱን ስም ጠቅሶ ይህን የዘረኝነት ልፋጭ ያዝረከረከው ግለሰብን ብቻ የሚወክል ነው። ጃዋር መሀመድ እና ሴፍ  ሸዋ ይህን የዘርነት ልፋጭ በይፋ ስለማዝረክረካቸው ግልፅ ነው።)
*****************************
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements