ያለማስተዋል ለፍርድ ያመቻል!!!

አሁን ሀገሪቷ ኢህአዴግ በዘረጋው መንግስታዊ ስረዓት እየተዳደረች ነው። በኢህአዴግ’ች እና ተቃዋሚዎች መካከል ያለው ግንኙነት የስረዓቱ ጠባቂዎች እና የለውጥ ናፋቂዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚወሰን ይሆናል። በተለይ መንግስት በህዝቡ ሕይወት ውስጥ ያለውን ቁጥጥር  ለመገንዘብ፣ ወታደር/ፖሊስ የመንግስታዊ ስረዓቱ ነፃብራቅ እንደመሆናቸው ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጤን ያስፈልጋል።

ለምሳሌ፣ መስቀል አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በሃይል እንዲበትን ቆመጥና ክላሽ ተሰጥቶት የተላከን አንድ አድማ-በታኝ ፖሊስን እንውሰድ። ይህ የፖሊስ አባል ሰላማዊ ሰልፈኞችን ያለ ርህራሄ በያዘው ቆመጥ ሲደበድብና በጥይት ሲገድላቸው ብናይ፣ ድርጊቱ ፍፁም ተቀባይነት የሌለውና ፖሊሱ’ም ርህራሄ ያልፈጠረበት ጨካኝ አውሬ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተለመደ ነው።

ነገር ግን፣ ፖሊሱ ይሄን የጭካኔ ተግባርን የፈፀመበትን ነባራዊ እውነታ የበለጠ እየተረዳን በመጣን ቁጥር በነገሩ ላይ ያለን አመለካከት ቀስ-በቀስ እየለዘበ ይሄዳል። ሦስቱን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመጠየቅ በጉዳዩ ላይ ምሉዕ የሆነ ግንዛቤ ስናዳብር ግን የፖሊሱ ተግባር ጭራሽ አማራጭ ያልነበረውና በነገሮች አስገዳጅነት የተፈፀመ እንደሆነ እንረዳለን። ይህን ግዜ የፖሊሱን ተግባሩ ለመደገፍም ሆነ ለማውገዝ ይሳነናል።

ለምሳሌ፣ ፖሊሱ “ያንን የመሰለ ጨካኝ ድርጊት ለምን ፈፀመ?“ ብለን እንጠይቅ። ከሰልፈኞቹ የተለየ ጨካኝ የሆነ ሰብዕና ስለነበረው ነው? ፖሊሱ የነበረበትን ነባራዊ እውነታ ለመገንዘብ፤ ከማክሲም ጎርኪ መፅሀፍ ውስጥየሚከተለውን ቃለ-ምልልስ እንውሰድ፦
ጄኔራል፡ “ስማ!…ወታደር ምንድነው?” ወታደር፡ “አለቃው እንዲያደርግ ያዘዘው የሚያደርግ ነው!“
ጄኔራል፡ “ኧ…አለቃው ‘ዓሳ ሁን!’ ቢለውስ?”
ወታደር፡ “ማንኛውም ወታደር የታዘዘውን ማድረግ መቻል አለበት!”

በእንዲህ ያለ የሥራ ስነ-ምግባር የታነፀ እና በጥብቅ የዕዝ-ሰንሰለት የሚመራ ወታድር እና ፖሊስ፣ የመኖር ህልውናው ከወር-ወር በማታደርሰው ደሞወዝ ላይ እንደተመሰረተ እያወቀ፣ የታዘዘውን ከመፈፀም ባለፈ ድርጊቱ በሚከናዎንበት ቦታና ሰዓት “አ…ይ! ይህ ሰልፍ ሰላማዊ ስለሆነ ትዕዛዙን አልቀበልም!…” ለማለት የሚያስችል ነፃነት ሊኖረው ይችላል? በተለይ  እንደ’ኛ ባለ ሀገር “ሰ…ላ…ማ…ዊ ሰልፈኞች” ፖሊሱ የያዘውን ቆመጥና ክላሽ ቀምተው ከመግደል ወደሗላ እንደማይሉ የሚያውቅ በ“ሳይቀድሙኝ-ልቅደም” ከመግደል  ውጪ ሌላ አማራጭ አለው? “ሰላማዊ ሰልፍ” እንደተባለው መብትን ለማስከበር ሳይሆን የሌሎችን መብት ለመጣስ የተደረገ ወይም በሚጥስ መልኩ የሚደረግ ከሆነ፣ በቦታና ሰዓቱ የፖሊሱን ተግባር ከመድገም ውጪ ሌላ አማራጭ አለ?

በዚህ መልኩ አንድ ተግባር የተፈፀመበትን ነባራዊ እውነታ ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር በዝርዝር እየተረዳን በሄድን ቁጥር ድርጊት ፈፃሚው አካል በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ እንረዳለን።

በሕግ’ም ሆነ በሞራል ስነ-ምግባር፣ የአንድ ተግባር ትክክለኝነት እና ስህተትነት የሚወሰነው ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ድርጊቱን ለመፈፀም በነበረው አንፃራዊ ነፃነት እና አስገዳጅነት ነው። በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚፈፀም ተግባር በሕግ’ም ሆነ በሞራል ስነ-ምግባር አግባብነት አለው።

ለምሳሌ፣ ሰው መግደል በሕግ የተከለከለ ተግባር (ወንጀል) ቢሆንም ሊገድል የመጣን ሰው ‘በአልሞት-ባይ-ተጋዳይነት’ መግደል ግን ተቀባይነት አለው። የመጀመሪያው ግድያ በፈፃሚው አካል ፍላጎት እና ምርጫ (በነፃነት) እንደ ተከናዎነ ስለሚታሰብ ተግባሩ በወንጀልነት ይፈረጃል። በአልሞት-ባይ-ተጋዳይነት የተፈፀመ ግድያ ግን፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈፀመ ተግባር ስለሆነ አግባብነት ያለው ተግባር እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ መሰረት፣ አንድ ተግባር፤ መብትን የማስከበር ይሁን ግዴታ ያለመወጣት፣ የሚለየው በሚፈፀምበት ቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር በነበረው አንፃራዊ ነፃነት ወይም አስገዳጅነት የሚመዘን ነው።
 
ወደኋላ ተመልሰን የአድማ-በታኙን ተግባር ከውጪ፣ ከሌላ ሰው እይታ አንፃር ሳይሆን፣ ፖሊሱ በነበረበት ነባራዊ እውነታ ውስጥ እራሳችንን ሙሉ-በሙሉ አስገብተን ብናይ፣  በሃሳብና እሳቤ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን ሲፈፅም የነበረውን ውጫዊ ገፅታ፣ ውስጣዊ ስሜት፣ ግለሰባዊ ባህሪ፣ ልምድ፣ አስተሳሰብና አመለካከት፣… በአጠቃላይ ሁለመናችን ተመሳሳይ በሆነ መንስዔ፣ ቦታና ግዜ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ከፖሊሱ የተለየ ተግባር እንፈፅም ነበር? በተመሳሳይ ነባራዊ እውነታ ውስጥ ፖሊሱ ያደረገውን ከመድገም ውጪ ሌላ አማራጭ ለመፈለግና ለመምረጥ እድል ይኖረን ነበር?

እንደ ሊዮ ቶልስቶይ አገላለፅ እኛ ሰዎች እልፍ በሆኑ ጉዳዩች ላይ የተለያየ ፍላጎትና ምርጫ እንዳለን አድርገን እናስባለን።  ይሁን እንጂ፣ በተመሳሳይ ነባራዊ እውነታ ውስጥ ስንሆን ግን አንድ አይነት ተግባር እንፈፅማለን።…ሰይጣን በለው፣ ዘረኛ፣ ነፍጠኛ፣… አሸባሪ፣ አክራሪ፣… ጠባብነት፣ ትምክህተኛነት፣ አማራ…ኦሮሞ…ተግሬ፣ መለስ…መንግስቱ…ሚኒሊክ” እያለ የጥላቻ ፖለቲካ ሲያቀነቅን የሚውል ሰው፣ እጅግ አድርጎ የሚጠላው ሰው በነበረበት ቦታ፣ ግዜና ሁኔታ ውስጥ እራሱ ኖሮ ቢሆን ኖሮ አሁን የጠላውን ተግባር ከመፈፀም ውጪ አማራጭ አይኖረውም ነበር። እናንተ “ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ሰላም!”  እና  “አባገነን…ፀረ-ዴሞክራሲ!” የምትባባሉ… በጭፍን ጥላቻና አመለካከት የስድብ ናዳ ስትንዱ የምትውሉ ሁሉ፣ አንዳችሁ የሌላኛችሁ መስታዎት ናችሁ!!!

ethiothinkthank.com

Advertisements