ነፃነት (Liberty)፥ ክፍል-1

ነፃነት የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ መብት ከመሆኑ ባለፈ ከተፈጥሯዊ ማንነት/ ባህሪው ጋር የተቆራኘ ነው። “ሰብዓዊ መብት” የሚለውን አገላለፅ በተደጋጋሚ ሲባል የምንሰማውና የተለመደ አገላለፅ ቢሆንም ፅንሰ-ሃሳቡን በጥልቀት ከመረመርን በነፃነት የሚረጋገጠው “የሰው መብት” ብቻ ሳይሆን ነፃነት በእራሱ “ሰብዓዊነት ወይም ሰው-መሆን” እንደሆነ እንረዳለን።

እንደ ሊዮ ቶልስቶይ አገላለፅ፣ ነፃነት የሕይወት ትርጉም እና ፋይዳ ነው። የሰው-ልጅ ለሕይወት ያለው ስሜት አንፃራዊ ነፃነቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የሚገለፅ እንደመሆኑ፣ ነፃነትን መገንዘብ የማይችል ሰው ሕይወትን መገንዘብ አይችልም። ሀብት እና ድህነት፤ መፈለግ እና አለመፈለግ፤ ሃይል እና ተገዢነት፤ ጤና እና በሽታ፤ አዋቂነት እና አላዋቂነት፤ ጥጋብ እና ረሃብ፤ ጥሩ እና መጥፎ፣…ወዘተ፣ ሁሉም አንፃራዊ የነፃነት ማነስና መጨመር ውጤቶች ናቸው (Leo Tolstoy, War & Peace)። ይህን ፅንሰ-ሃሳብ በግልፅ ለመረዳት ነፃነት ከአጠቃላይ የሰው ሕይወት ጋር ያለውን ቁርኝት በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል።

በቅድሚያ በአማርኛ “ሰው” የሚለው ቃል “ሰብ” ከሚለው የግዕዝ (ትግሪኛ) ቃል የመጣ ሲሆን “ሰብዓዊ” የሚለው ቃል ደግሞ “የሰው የሆነን ነገር ወይም ባህሪ” ያመለክታል። በመሆኑም፣ “ሰብዓዊ መብቶች” ሲባል “የሰው የሆኑ መብቶችን” ያሳያል። ነገር ግን “ሰብዓዊ-መብቶች” ሲባል ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ የሚገኙ መብቶች እንደሆኑና በውስጡ፤ ነፃነት፣ ፍትህ እና እኩልነት እንዳሉ ሲጠቀስ መስማት የተለመደ ነው።

በዩሃንስ እጅጉ የተዘጋጀው መዝገበ-ቃላት፣ “Human rights” የሚለውን ሕረግ፤ “የእያንዳንዱ ሰው ‘ነፃ’ የመሆን መብት” ይለዋል። በዚህ መሰረት፣ ለሰው-ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው መብት ‘ነፃነት’ ስለመሆኑ ይጠቁማል። በመቀጠል፣ “ሰብዓዊ መብቶች” ‘ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ የሚገኙ መብቶች’ ናቸው። “ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ” ሲል፣ መብቱ ‘ሰው-ከመሆን’ ጋር የተቆራጀ ስለመሆኑ ያሳያል። ምክንያቱም፣ የ“ሰብዓዊ-መብት” ባለቤት ለመሆን “ሰው-መሆንና ሰው-መሆን ብቻ በቂ ሲሆን፣ “ሰብዓዊነት” (humanity) ደግሞ “ሰው-መሆን፣ የሰብዓዊነት/የሰውነት መለያ ባሕሪያት ወይም ብቃቶች’ የሚል ትርጓሜ አለው። ስለዚህ ‘“ሰብዓዊነት” በሚለው ቃል የተገለፀው የሰው-ልጅ መለያ ባሕሪ ወይም ልዩ ተፈጥሯዊ ብቃት፣ እና ከነፃነት ጋር ያለው ተያያዥነት ምንድንነው?’ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
*******
ይቀጥላል…
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements