ነፃነት (Liberty)፥ ክፍል-10

ሰው በተግባራዊ እንቅስቃሴው የሚኖረው መብትና ግዴታ ከራሱና ከሌሎች ሰዎች ነፃነት አንፃር የተቃኙ ናቸው። ነፃነት የሌሎችን ነፃነት ሳይገድቡ በራስ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መቻል ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት “ሌላውን ሰው ነፃነት ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፥ … መብት”  ነው። ስለዚህ፣ በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ ነፃነት መብትና ግዴታን በአንድነት አጠቃሎ የያዘ እንደሆነ እንገነዘባለን። በመሆኑም፣ የፈለጉትን የመስራት፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት፣ የሌላውን ሰው ነፃነት እንዳይነካ ከሚያደርግ “ግዴታ” ጋር የተጣመረ ነው።

በምንም ነገር ላይ ጥገኛ ያለመሆን መብት ምንም ነገርን ጥገኛ እንዳናደርግ ከሚያደርግ ግዴታ ጋር የተጣመረ ነው። በራሳችን ፍላጎትና ምራጫ ለመንቀሳቀስ ያለን መብት፣ የሌሎችን ሰዎች የፍላጎትና ምርጫ ነፃነት እንዳንፃረር ከሚያደረግ ግዴታ በጋራ የያዘ ስለሆነ ነፃነት ከመብት የበለጠ ሰፊና ሁሉን አቀፍ ነው። በዚህ መሰረት፣ የነፃነት ፅንሰ-ሃሳብ ከመብት አንፃር ሰፊና ምሉዕነት አለው።

እኛ የምንሻው ነፃነት ሌሎች ሰዎች ከሚሹት ነፃነት ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ሁሉም ሰው እኩል የሆነ መብት አለው። እኛ እንዲከበርልን የምንሻው ነፃነት ሌሎች እንዲከበርላቸው ከሚሹት ነፃነት ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ሁሉም ሰው እኩል የሆነ ግዴታ አለበት። የእኛ መብት ለሌሎች ግዴታ፣ የሌሎች መብት የእኛ ግዴታ ሲሆን፣ በሁለቱም ውስጥ አንድ ዓይነት ባህሪ አለ። ይህ በመብትና ግዴታ ውስጥ ያለ ባህሪ “ነፃነት” ነው።

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ ነፃነት ማለት የሌሎች ሰዎችን ፍላጎትና ምርጫ ሳይጋፉ በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል ነው። በዚህ መሰረት፣ የአንድ ሰው ግዴታ የመብቱ እኩሌታ እንደመሆኑ፣ መብታችን ከግዴታችን ጋር እኩል ነው። ነገር ግን፣ መብታችን ከግዴታችን ሲበልጥ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎትና የምርጫ ነፃነት የሚጋፋ ጨቋኝ ተግባር እንፈፅማለን። ከመብታችን የሚበልጥ ግዴታ ሲኖርብን ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትና ምርጫ ተገዢ እንሆናለን። የመብትና ግዴታ እኩሌታን ያልጠበቀ እንቅስቃሴ ለጨቋኝነት ወይም ተገዢነት ይዳርጋል። ለጭቆና ወይም ተገዢነት በሚዳርግ እንቅስቃሴ ውስጥ ነፃነት ሊኖር አይችልም። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት እንዲኖር የመብትና ግዴታን እኩሌታ በጠበቀ መልኩ መንቀሳቀስ የግድ ይሆናል። ይህ መሰረታዊ የመብት መርህ እሳቤ ሲሆን የማንኛውም ተግባር “ትክክለኝነት” ወይም “ስህተትነት” ከዚህ አንፃር የሚወሰን ይሆናል።
*******
ይቀጥላል…
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements