ነፃነት (Liberty)፥ ክፍል-11

በመሰረታዊ የመብት መርህ መሰረት፣ ማንኛውም ተግባር፣ በራሱ ወይም በሚከተለው መርህ፣ ከእያንዳንዱና ከሁሉም ተንቀሳቃሽ ፍላጎትና ምርጫ ነፃነት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል እስከሆነ ድረስ “ትክክለኛ” (right) ተግባር ነው። በዚህ መሰረት፣ “ትክክለኛ” ተግባር መብትና ግዴታ የተስተካከሉበት ተግባር ሲሆን፣ “ትክክለኝነት” ደግሞ ሁለቱን አስተካክሎ መንቀሳቀስ መቻል ነው። በዚህ መሰረታዊ መርህ መሰረት ከሌሎች ሰዎች ፍላጎትና ምርጫ ነፃነት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ተግባራዊ እንቅስቃሴን የሚያደናቅፍ ወይም የዚህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይኖር የሚያደርግ ማንኛውም ተግባር “ስህተት” (wrong) ነው። እንዲህ ያለ ተግባር በራሱ ወይም በመርህ ደረጃ የመብትና ግዴታን እኩሌታ የሳተ ነው። የሰው-ልጅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚመራበት መሰረታዊ መርህ አንፃር የተሳከረ፣ የተፋለሰ ወይም የተዛነፈ ተግባር ትክክለኛ ተግባር ሊሆን አይችልም። በመሆኑም፣ በሁሉን-አቀፍ የነፃነት መርህ ጋር አብሮ ሊሄድ የማይችል የተሳሳተ ተግባር የሚያደርግ ማንኛውም ሰው “ስህተተኛ” ነው። 

እያንዳንዱ ሰው የሌሎችን ነፃነት የሚገድብ ተግባር ያለመፈፀም ግዴታ (obligation) አለበት። በውጫዊ እንቅስቃሴያቸው በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ መፍጠር በሚችሉ ግለሰቦች መካከል፤ የአንዱ መብት ለሌላኛው ግዴታ፣ የአንዱ ግዴታ ለሌላኛው መብት ይሆናል። የአንዱ ግዴታውን በአግባቡ ያለመወጣት የሌላውን ነፃነት መገደብ ነው። በዚህ ምክንያት ነፃነት እንዳይገደብ ማድረግ መብትን ማስከበር ነው። ነፃነት የሌሎችን ፍላጎትና ምርጫ ሳይጋፉ መንቀሳቀስ መቻል እንደመሆኑ የመብትና ግዴታ እኩሌታ ነው። የሌሎችን የፍላጎትና ምርጫ ነፃነት የሚጋፋ ነፃነት ደግሞ በራሱ ስህተት ነው። በመሆኑም፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ሌላኛው ግለሰብ ግዴታውን እንዲወጣ የሚያስገድድ ስልጣን ሊኖረው ይገባል። ይህ አስገዳጅነት ያለው ስልጣን (መብት) በሌለበት በነፃነት የመንቀሳቀስ አይቻልም።

ነፃነት ፍላጎትና ምርጫ ጥምር ውጤት፣ የመብትና ግዴታ እኩሌታ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው በራሱ በፍላጎትና ምርጫ መሰረት የሌሎች ሰዎች ነፃነትን ሳይገድብ የመንቀሳቀስ መብት አለው። ተግባራዊ እንቅስቃሴውን በዚህ ስርኣት መሰረት የሚመራ ከሆነ የእያንዳንዱና የሁሉም ሰዎች ነፃነት ይከበራል። ይህ እንዲሆን ግን ሁሉም ሰዎች ስርኣቱን በተከተለ መልኩ መንቀሳቀስ አለባቸው። በመሆኑም፣ ሁሉም የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች ስርኣቱን አስመልክቶ ከጋራ መግባባት ላይ ሊደርሱ ይገባል። በዚህ መልኩ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት ስረኣት የሚደረጉ እና የማይደረጉ ተግባራት በዝርዝር የሚጠቀሱበት ይሆናል።

ነፃነት የማድረግ እና ያለማድረግ ነፃ ፍላጐትና ምርጫ ሲሆን “ሕግ” (law) ደግሞ የሚደረጉ እና የማይደረጉ ተግባራት የሚለዩበትና በአንድነት እንዲፀኑ የሚደረግበት ስረኣት ነው።  ስለዚህ፣ ሰው ነፃነትን የመብትና ግዴታ እኩሌታን በመጠበቅ የሚገኝ ሲሆን ሕግ ይህን ሚዛን ለመጠበቅ የሚዘረጋ ስረኣት ነው።

ሕግ በሌለበት ሰው በራሱ ፍላጎትና ምርጫ ለመንቀሳቀስ ቢችል እንኳን ግዴታውን ማስገደድ አይችልም። በመሆኑም፣ ሕግ ለሰው መብቱን ለመስጠትና ግዴታውን ለማስገደድ የተዘረጋ ስረኣት ነው።
በዚህ መልኩ በሕጋዊ ስርዓት ያልተገደበ ነፃነት ውስጥ ሁሉም ነገር ትክክል፥ ሁሉም ተግባር አግባብ ነው። የሰው-ልጅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከምክንያታዊነት ይልቅ በጉልበት፤ በነፃነት ሳይሆን በአስገዳጅነት የሚደረግ ስለሚሆን፣ የሰው-ልጅ ሕይወትን በሠላም ሳይሆን በጦርነት ይመራል።

ትክክለኝነት እና አግባብነት በኃይል እና ማጭበርበር ይተካሉ። ማንኛውም ሰው በራሱ መያዝ እስከቻለበት ግዜ ድረስ የፈለገውን ነገር ለራሱ መያዝ ይችላል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ፤ የእኔ እና የእናንተ የሚል የመብት ክፍፍል የለም፣ ሃብትና ንብረት ማፍራትና ማስተዳደር አይቻልም።

አንድን ግለሰብ ግዴታውን እንዲወጣ የማስገደድ ስልጣን በሌላ ግለሰብ እጅ ስር እስከሆነ ድረስ ግዴታውን እንደ መብት ከመጠየቅ በጉልበት የሚፈፀም ይሆናል። ጉልበተኛ ግዴታን ከማስገደድ ባለፈ የግለሰቡን መብቱን ጭምር በመቀማት ከነፃነት አስገዳጅነትን ይመርጣል። ምክንያቱም፣ መብትና ግዴታ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ ፍትህ የለም፣ ፍትህ በሌለበት ፍትሃዊ ያልሆነ ነገር ሊኖር አይችልም።
*******
ተፈፀመ…
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements