ነፃነት (Liberty)፥ ክፍል-2

በተፈጥሮ አስገዳጅነት በሚደረጉ ተግባራት ላይ ነፃ-ፍላጎት እና ምርጫ፤ የፍላጎት እና የምርጫ ነፃነት ሊኖር አይችልም። ነገር ግን፣ ሰው ነባራዊ እውነታን በመገንዘብ፣ የነገሮችን ምንነት እና የምልክቶችን ትርጉም በመረዳት፣ እንዲሁም በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት በመገንዘብ፤ ሃሳቦችን ይፈጥራል፣ ያዳብራል፣ ይለውጣል። በመሆኑም፣ በአዕምሮው ውስጥ ያሉ ሃሳቦችን ከመገንዘብ፣ ከነባራዊ እውነታ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማነፃፀር፣ በመካከላቸው ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት ከማስላት አንፃር፣ ሰው ቀጥተኛ-የሆነ ኃይል (active power) አለው። ስለዚህ፣ ሰው ሃሳባዊ እንቅስቃሴን ለማድረግና ላለማድረግ፣ በእንቅስቃሴው ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል መወሰን ይችላል።

ሰው ሃሳባዊ አንቅስቃሴውን ተግባራዊ የማድረግና የመለወጥ አቅምና ብቃት አለው። ምንም እንኳን በደመ-ነፍስና በስሜታዊ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለመጀመር ወይም ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል ባይኖረውም፣ በሃሳባዊ እንቅስቃሴው ላይ ግን ሙሉና ቀጥተኛ-የሆነ ኃይል አለው። በዚህ መሰረት፣ ሰው በአዕምሮው በማሰብና በመምረጥ ብቻ የተለያዩ ተግባራትን መጀመር ወይም መግታት፤ መቀጠል ወይም ማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ኃይል አለው።

በሃሳቡና በፍላጎቱ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ፣ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቀጠል ወይም ለማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ኃይል ስላለው፣ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ስለ አንድ ነገር ለማሰብ ወይም ላለማሰብ፣ በሃሳቡ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ መወሰን ይችላል። ስለዚህ፣ ሰው በእራሱ ፈቃድ  ሃሳባዊ እንቅስቃሴን የማድረግ፣ እንዲሁም በሃሳቡና አስተሳሰቡ መሰረት የተወሰነ የሰውነት ክፍሉን ማንቀሳቀስ ይችላል።

በዚህ መሰረት፣ “ፈቃድ “ (Will) ማለት፣ በሃሳብ ላይ ብቻ በመመስረት አንድን ነገር ለመፍጠር ወይም ለማድረግ መሞከር ይሆናል። አንድ ሰው፣ የተወሰነ ሃሳባዊ ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ወይም ባለማድረግ ፍቃዱን በተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገልፅ “መፍቀድ ወይም መምረጥ“ (willing or volition) ይባላል። “ፍቃደኛ“ (voluntary) የሚለው፣ በእራስ ሃሳብ ላይ ተመስርቶና ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል አስገዳጅነት መንቀሳቀስ ወይም ከእንቅስቃሴ መቆጠብ እንደማለት ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ የሆነ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ “ያለውዴታ“ ወይም “በግዴታ” (involuntary) የሚደረግ ተግባር ነው።
*******
ይቀጥላል…
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements