ነፃነት (Liberty)፥ ክፍል-5

ከላይ በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው፣ ሰው በስሜት ህዋሳቱ አማካኝነት የተገነዘበውን እውነታ በምክንያታዊ አስተሳሰብ ያገናዝባል። በዚህም፣ በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት በማስተዋል፣ በማነፃፀርና በማመሳከር ነባራዊ እውነታን ከሌሎች እንስሳት በተሻለ መረዳት ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ነባራዊ እውነታን ለመረዳትና በተረዳው መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ይወስናል። ስለዚህ፣ “ፈቃድ” እና “መረዳት” የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ናቸው። በራስ ለመፍቀድ መረዳት፣ በራስ ለመረዳት ደግሞ መፍቀድ አስፈላጊ ስለሆነ ፈቃድ እና መረዳትን በጥምረት ካልሆነ በስተቀር በተናጠል ማየት አይቻልም። የእነዚህ ሁለት ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጥምር ውጤት ደግሞ “ነፃነት” ነው። በመሆኑም፣ “ነፃነት” የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ስለዚህ ነፃነት ሰውን “ሰው” ያሰኘ፣ የሰብዓዊነት መለያ ባህሪ ከሆነ፣ “ነፃነት በራሱ ምንድነው?” ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው።

በመሰረቱ፣ ነፃነት “ያለምንም ገደብ መንቀሳቀስ መቻል” በሚል ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ለምሳሌ፣ በእንግሊዘኛ “freedom” የሚለው ቃል “ነፃነት፣ ነፃ-መሆን፣ ነፃ-መውጣት፣ የመንቀሳቀሻ-ቦታ ልቀት፣ ስፋት፣ ርዝመት፤ ነፃ የመንቀሳቀሻ-ቦታ፣ ሙሉ-የመንቀሳቀሻ ቦታ፤ ለመንቀሳቀስ ምቹ የሆነ ቦታ፤ ነፃ ቦታ፣ ነፃ ይዞታ፤ ነፃ-ሰው፣ ነፃ-የወጣ ሰው፤ ራስ-ገዝ፣ ራስ-አመራር፣ ነፃ-ማውጣት፣…ወዘተ እንደማለት ነው። ስለዚህ “ነፃነት” የሚለው ቃል፤ ነፃ-መሆንን፣ የመንቀሳቀሻ-ቦታ መኖርን፣ የመሄጃ-ቦታ መኖርን፣ በራስ-መንገድ መሄድን፣ በራስ-ፈቃድ መመራትን፤ እንደወደዱት፣ እንደፈለጉትና እንደመረጡት ማድረግን፤ በራስ-መቆምን፣ በእራስ-እግር መቆምን፣ ለእራስ-መሆንን…ወዘተ፣ የመሳሰሉት ተግባራት እና ሁኔታዎች ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ የቃሉ ፅንሰ-ሃሳብ ጠቅለል ተደርጎ ሲቀመጥ፤ “ያለገደብ መንቀሳቀስ መቻል ወይም እንቅስቃሴን የሚገድብ ውጫዊ ኃይል ያለመኖር (አለመኖር) ነው” የሚል እሳቤ እንዳለው መረዳት ይቻላል።

በመሰረቱ፣ “ያለምንም ገደብ መንቀሳቀስ መቻል” የነፃነት የመጨረሻ ደረጃ ነው። አንድ ሰው በዚህ ደረጃ ምሉዕ የሆነ ነፃነት ሊኖረው የሚችለው አንድና አንድ ብቻ ሆኖና ምንም ዓይነት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሳያደርግ የሚኖር ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከሰው-ልጅ ተፈጥሮ እና ባህሪ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ምክንያቱም የሰው-ልጅ በተፈጥሮም ሆነ በባህሪ በዚህ ዓይነት የተናጠል ህይወት መኖር አይችልም። በተፈጥሮ የሰው ዘር ቀጣይነት በሁለቱ ፆታዎች ጥምረት ላይ የተመሰረተ ነው። በባህሪም ቢሆን ሰው ማህበራዊ እንስሳ እንደመሆኑ አብዛኛውን የህይወት መስተጋብር በጋራ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ የነፃነት ፅንሰ-ሃሳብ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር አብሮ የማይሄድበት ምክንያትን በግልፅ ለመረዳት ፅንሰ-ሃሳቡ የተመሰረተበትን እሳቤ መገንዘብ ያስፈልጋል።
*******
ይቀጥላል…
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements