ነፃነት (Liberty)፥ ክፍል-6

ነፃነትን ከቦታ ገደብና ልቀት አንፃር የማየት እሳቤ የሰው እንቅስቃሴ እንደሌሎች እንስሳት በአካላዊ አፈጣጠሩ የተገደበ አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ነው። ነገር ግን፣ የሰው-ልጅ ነፃነት በዚህ መልኩ የሚገለፅ ቢሆን ኖሮ ሕይወት ፍፁም የተለየ ገፅታና ትርጉም በኖራት ነበር።

እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም እንስሳ የሰው-ልጅ’ም በቦታ ላይ አካላዊ እንቅስቃሴ (physical motion) ያደርጋል። ነገር ግን፣ ሰው በስሜትና ደመ-ነፍስ ከሚያደርጋቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ሃሳባዊ እቅስቃሴ ያደርጋል። ሰው በምክንያታዊ አስተሳሰብ ከቦታና ግዜ ገደብ ውጪ መንቀሳቀስ ይችላል። ከቦታ (space) ገደብ በአካል ያልተገነዘባቸውን ነገሮች በአዕምሮው መገንዘብ ይችላል።

በተመሳሳይ፣ በአካል ከሚገነዘባቸው ክስተቶች በተጨማሪ፣ ከግዜ (time) ገደብ ውጪ ተከስተው የነበሩና ወደፊት ስለሚከሰቱ ክስተቶች በአዕምሮው መገንዘብ ይችላል። በዚህ መልኩ ከቦታና ግዜ ገደብ ውጪ ሃሳባዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን በሃሳቡ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላል።

ሰው በራሱ ፍቃድ ማሰብ፣ በሃሳቡ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ መወሰን ይችላል። ስለዚህ፣ የሰውን እንቅስቃሴ “አካላዊ” ብቻ እንደሆነ አድርጎ መውስድና በዚህ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴን ከቦታ ገደብና ልቀት አንፃር ብቻ ማየት ስህተት ነው። ይህ የተሳሳተ የነፃነት ፅንሰ-ሃሳብ በስሜትና በደመ-ነፍስ ለሚመሩ እንስሳት እንጂ በራሱ ፋቃድ ለሚንቀሳቀስ ምክንያታዊ ፍጡር የሚሆን አይደለም (Thomas Hobbes, Levithan)።

በእንቅስቃሴያቸው ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ግለሰቦች መካከል፣ የአንዱ ነፃነት በሌላኛው ግለሰብ ግዴታውን መወጣት የሚወሰን እንደመሆኑ፣ ግዴታን የሚያስገድድ ስልጣን በሌለበት ሁሉን-አቀፍ የነፃነት መርህ ውድቅ ይሆናል። የሰዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሁሉን-አቀፍ የነፃነት መርህ የማይመራ ከሆነ፤ የመብትና ግዴታ፣ የትክክልና ስህተት፣ የጥሩና መጥፎ፣ የፍትሃዊነትና ኢ-ፍትሃዊነት እሳቤዎች መሰረት ይናዳል።

ግዴታ የሌለበት ነፃነት ‘ያለገደብ መንቀሳቀስ መቻል ወይም እንቅስቃሴን የሚገድብ ውጫዊ ኃይል ያለመኖርን የሚያሳይ ነው’። “ነፃነት” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ በዋናነት በቦታ ገደብና ልቀት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ከሰው-ልጅ የፍላጎትና የምርጫ ነፃነት ይልቅ የሌሎች እንስሳትን እና ጉዑዝ ነገሮችን አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያንፀባርቅ ነው። በዚህ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት የሰው ልጅን ነባራዊ ሁኔታ ለመግለፅ መሞከር ፍፁም ስህተት ነው።
*******
ይቀጥላል…
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com

Advertisements