‘ክፉ ሰው’ ካለ ‘ሰው’ መሆን አልሻም!

“ሰው አውቆና ፈቅዶ በሌሎች ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አይፈፅምም!” የሚል የሕይወት መርህ አለኝ። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በነፃነት (በነፃ ፍላጐትና ምርጫ) በሌሎች ሰዎች ላይ “ክፉ” ነገር አያደርግም።

አንድ ሰው ከሕግም ሆነ ከሞራላዊ እሳቤ  አንፃር ጥፋተኛ ሊሆን የሚችለው በጥፋተኝነት ያስፈረጀውን ተግባር በነፃነት የፈፀመው ከሆነ ብቻ ነው። በነፃነት የተፈፀመ ተግባር ድርጊት-ፈፃሚው አውቆና ፈቅዶ ያደረገው ሲሆን ነው። ለመፍቀድ ማወቅ፣ ለማወቅ ደግሞ መፍቀድ አለበት። ሰው በራሱ ፍቃድ (by his own Free Will) ላደረገው ተግባር ተጠያቂ ይሆናል።

ከዚህ በተረፈ፣ ሰው በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለፈፀመው ተግባር ግን ተጠያቂ አይሆንም። ለምሳሌ፣ እንበልና አንዲት ሴት ከአንድ ሱቅ ዳቦ ሰረቀች፣ የሚያስፈልገውን ክፍያ ሳትፈፅም ዳቦውን ደብቃ ወሰደች። ስርቆት በሕግም ሆነ በሞራል ደረጃ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። የሴትዮዋን ተግባር አግባብነት “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” ብሎ ለመፈረጅ፣ ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ያለን ግንዛቤ ወሳኝ ነው። ሴትዮዋ በዚያ ቦታና ግዜ የምትከፍለው ገንዘብ የሌላትና የ3ወር ልጇ ባዶ ጡቷን በድዱ ነክሶ እያለቀሰ ቢያስቸግራት፣ የልጇና የራሷ ሕይወት ቢያስጨንቃት፣ ህልውና (ህላዌ) ከምንም ይቀድማልና (Necessity has no law) ዳቦውን መስረቅ በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የተደረገ ነው። ይህን ነባራዊ እውነታ ሙሉ-ለሙሉ ካልተገነዘብን ሴትዮዋ ስርቆቱን በራሷ ነፃ ፍላጐትና ምርጫ እንዳደረገችው፣ በዚህም በሌብነት መጠየቅ እንዳለባት ልንወስድ እንችላለን።

የአንድን ሰው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ሙሉ በሙሉ መገንዘብ ከቻልን ግን ተግባሩ በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንደተፈፀመ እንረዳለን። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተደረገ ነገር በግዴታ እንጂ በፍላጐትና ምርጫ እንደተደረገ ተደርጐ ሊወሰድና ተጠያቂ ሊደረግ አይገባም።

አንድ ሰው አሁን እኔ ይሄን ፅሁፍ የምፅፍበትን ምክንያት፣ ቦታና ግዜ ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት የእኔን አመለካከት፣ እሳቤና አስተሳሰብ፣ በውስጤ እየተሰማኝ ያለውን ስሜት መረዳትና ዛሬ ያስተዋልኩት እውነታ ማስተዋል፣ እንዲሁም እኔ ያለሁበትን ቦታና ግዜ ማወቅ አለበት። ይህን ሙሉ ለሙሉ መረዳት የሚችለው በአካልና መንፈስ እኔን መሆን ከቻለ ብቻ ነው። እኔን መሆን ከቻለ ደግሞ አሁን የማደርገው ያደርግ ነበር።

ይህ እንደሌሎች የተፈጥሮ ሕጎች የማይነቃነቅ ቋሚ የሆነ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። አንድን ሰው ‘ከዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪ ውጪ ነው’ የምትሉኝ ከሆነ “በእርግጥ እሱ ሲጀመር  *ሰው* ነው’ን?” ስል እሞግታችኋለሁ። “አውቆና ፈቅዶ በሌሎች ሰዎች ላይ ክፋትን የሚያስብና የሚሰራ ሰው አለ” ብላችሁ ካሳመናችሁኝ ግን “ሰው” የሚለውን የክብር ስያሜ ከእኔነቴ ይገፈፍ እላለሁ። ያኔ ከሕይወት ይልቅ ሞትን እመርጣለሁ!!!
ክፉ ሰው ካለ ሰው መሆን አልሻም።
*******
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com