‘የወጨጌዎች’ ልሙጥ ሥልጣኔ

ሥልጣኔ እንዳይወድቅ፣ የሀገር ብልፅግና እንዲረጋገጥ በሁሉም ማህበራዊ ዘርፎች እድገት እና መሻሻል መቋረጥ የለበትም። የእድገትና መሻሻል መንፈስ በማሕብረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ልዩነት ሊኖር ይገባል።

የእድገት እና መሻሻል መንፈስ ሊፈጠር የሚችለው በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊ ጉዳዮች፤ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ በአኗኗር ዘይቤ እና የሞራል እሴቶች ያላቸውን ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል ሲችሉ ነው። ምክኒያቱም፣ እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል በእራሱ የሕይወት ፍልስፍና እና አቅጣጫ በሚሄድበት ወቅት ለእራሱና ለሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አዲስ ልምድና ተሞክሮ በማምጣት እሴት ይጨምራል። 

ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም፣ በአጠቃላይ ከሀገር ብልፅግና እና እድገት አንፃር ሲታይ፣ ልዩነት ምንግዜም ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ለምሣሌ፣ አንድ የሕብረተሰብ ክፍል የሚከተለው የሕይወት መንገድ ብልፅግናን ከማምጣት አንፃር ሲታይ ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። ነገር ግን፣ የሄዱበት አቅጣጫ ጠቃሚ ከሆነ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲከተሉት ትምህርት ይሆናል፤ ጎጂ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የተቀሩት መንገዱን እንዳይከተሉ ትምህርት ይሆናል። ስለዚህ፣ ልዩነት ባለበት ሁሌም አዲስ ነገር አለ፤ አዲስ ተሞክሮ እና ተጨማሪ ዕውቀት ባለበት መሻሻል እና ለውጥ አለ። በሕብረተሰቡ ውስጥ የዚህ ዓይነት ልዩነት ከሌለ ግን የእድገት እና የመሻሻል መንፈስ ውድቀት ምልክት ነው።

ሥልጣኔ የሚያድገው በልዩነት፣ የሚወድቀው በተመሣሣነት ነው። ሁሉም ሃይማኖቶች በተከታዮቻቸው ዘንድ ተመሣሣይነትን እንጂ ልዩነትን አይሰብኩም። ስለዚህ፣ የትኛውም ሃይማኖት ወይም የሃይማኖት ክፍል ለእድገት እና ብልፅግና የሚያደርስ የሥልጣኔ አቅም ሊኖረው አይችልም። 

የግለሰብ-ነፃነት፣ የእድገት አና መሻሻል መንፈስ፣ የካፒታሊዝም-መንፈስ ሊኖር የሚችለው በሃይማኖታዊ እና መለኮታዊ ትዕዛዛት ሳይሆን በመንፈሱ ተሸካሚው ላይ ነው። ከአምላክ በትዕዛዝ የሚወርድ ሳይሆን የአስተሳሰብ እና የግል ስብዕና ነፀብራቅ ነው። እግዚያብሄር እንዲያስብ አድርጎ የፈጠረውን አካል እንዳያስብ በማድረግ ሳይሆን አዕምሮን ተጠቅሞ በማሰብ እና የሕይወትን መንገድ እና አካሄድ በእራስ በመወሰን ሂደት የሚመጣ ነው።  

የአለም ሥልጣኔዎች እድገት እና ወድቀትን ስናጠና፣ ሥልጣኔ በሃይማኖት ውድቀት፣ ሃይማኖት በሥልጣኔ ውድቀት ላይ እንደሚነግሱ ነው። የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ምሁራን ሆይ፤…በሃይማኖት እጅ እና አዕምሮው በታሰረ ሕብረተሰብ ውስጥ፣ ስለምን የእድገት እና የመሻሻል መንፈስን ትፈልጋላችሁ?

ethiothinkthank.com

Advertisements