የዜሮ_እና_መቶ ወግ

#መቶ፡ “ው…ይ ዜሮ ደሞ ሙዝ…ዝ ስትል አይጣል! የለህም…ባዶ ነህ… ምንም ነህ! ለምን ድርቅ ትላለህ?”

#ዜሮ፡ “አይ መቶ! እሺ እኔ ከሌለውና ‘ምንም’ ከሆንኩ፣ አንተ ራስህ የለህም’ኮ። እንዴት ነው የምታስበው? እኔን በጥላቻና ፍርሃት ለማጥፋት ስትጥር ራስህን ታጠፋለህ’ዴ?! ያንተ ህልውና’ኮ በእኔ መኖር ላይ የተመሰረተ ነው። አንተ ግን ዝ…ም ብለህ ትጮኻለህ! የሆንክ ባዶ ነገር…”

#መቶ፡ “‘እ…ኔን ነው?…እንዴት ባክሽ? …ኧረ እስኪ እንዴት ነው የእኔ ህልውና ባንቺ መኖር የሚወሰነው?… ዶጮ ራስ!”

#ዜሮ: “‘እኔ ዶጮ ራስ’? አንተ አለህ አይደል ‘ዶማ ራስ!?’ …በቃ “መቶ” ስትባል ‘ምሉዕ’ የሆንክ ይመስልሃል? ያለኔ’ኮ “100” መሆንህ ቀርቶ “1” ነህ!”

#መቶ: “እንዲያም ሆኖ’ኮ ግን ቁጥር የሚጀምረው ከኔ ነው። በገሃድ ያለ ነገር “1” ብሎ እንጂ “0” ተብሎ አይቆጠርም። አየሽ እንዴት ያላቺ መኖር እንደምችል? ሃሃሃ…ደቃቃ ነገር ነሽ…ላጥፋሽ እንዴ?… ‘እፍፍፍ’!”

#ዜሮ፡ “ኤጭ…እሳቤህ ሁሉ ቁንፅል ነው። የእውነትን ጠምዝዘህ ባንተ ፍላጐት አቅጣጫ እንዲሄድ የምታደርግ ይመስልሃል። የሆንክ ጉልበታም ነገር ነህ! እውነት በእውቀት እንጂ በጉልበት አይገዛም!

#መቶ: “ኧረ ይሄን ሁኹትና ብጥብጥ የሚያስነሳ ንግግርሽን ተይ!…”

#ዜሮ: “እኔ ከሌለው አንተ “1” ብቻ ትሆናለህ። ይሄን ትክዳለህ?”

#መቶ:- “ይሁና…’1’ቁጥር ሆኜ’ኮ እኖራለሁ። አንቺ ግን ከሌለሽ የለሽም…በቃ አለቀ… ሃሃሃ”

#ዜሮ: “እሺ ይሁንልህ፣ እኔ የለሁም።  አንተ ብቻህን ከሆንክ’ኮ ቁጥርና መቁጠር አይኖሩም። አንተ ብቻህን ነሃ!  እንዳንተ አይነት ጡንቻ ራስ “እኔ በራሴ ‘ሙሉ’ ነኝ” ብሎ የሚለፍፍ ሁሉ “ሙሉ” የሚለው ነገር በራሱ “ምንም” ማለት እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል።

#መቶ: “እሺ…አንቺ እንዳልሽው መቶ ቀርቶ አንድ ልሁን። አንድም ሆኜ ግን በገሃድ ያለ ነገር ሁሉ “አንድ” እንጂ “ዜሮ” አይባልም። አየሽ… እኔ የመኖር መለያ፣ አንቺ ደግሞ ያለመኖር መለያ ነሽ። እኸ! ልዩነቱ ገባሽ?” 

#ዜሮ፡ “አለመኖር ከሌለ መኖር ፋይዳ የለውም! የሚቆጠር ሳይኖር መቁጠር አይቻልም፣ አንድ ብቻውን ቁጥር አይሆን’ማ! ቁጥር የሚኖረው አማራጭ ሲኖር ነው። አማራጭ በሌለበት ምርጫ የለም። “እኔ ብቻ” በማለት አለመኖርህን መሰከርክ እንጂ መኖርህን አላረጋገጥክም። ደደብ ነገር ነህ’ዴ?! “አለሁ” ስትል የለህም’ኮ!!!”

መቶ፡ “ኧ…?”

ዜሮ፡ “‘100’ ያለ ‘0’ አንድ ‘1’ ነው። 1 ምርጫና አማራጭ የለውም። ምርጫና አማራጭ ካለ 100% ድጋፍ ወይም ተቃውሞ አይኖረውም። አማራጭ ባለበት “100% ድጋፍ አገኘሁ” ማለት ምርጫው ነፃ እንዳልነበር ከመመስከር ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። 
******
ሰኔ 15, 2007 ዓ.ም

ethiothinkthank.com