ሰርግ፦በመኪና ወይስ በቀንድ ጡርባ ነው?

በአንድ ወቅት “አሜሪካ ውስጥ እያንዳንዱ ቤተሰብ በአማካይ 1.7 #መኪና ሲኖረው በጃፓን ደግሞ ወደ 2.0 የሚጠጋ መኪና አለው” የሚል ዘገባ አንብቤ ነበር። የኢትዮጲያ ቤተሰብ ከዚህ ደረጃ ለመድረስ በሀገሪቱ ውስጥ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ መኪኖች ሊኖሩ ይገባል። (አሁን ኢትዮጲያ ውስጥ ያለው የመኪና ብዛት ቢካፈል እያንዳንዱ ቤተሰብ በአማካይ 0.06 አከባቢ መኪና ይኖረዋል) እንደ አሜሪካና ጃፓን ካሉ ሀገራት ጋር ተቀራራቢ የሆነ ቁጥር የሚገኘው ግን ሀገሪቷ ያሏትን መኪኖች ሳይሆን #የቀንድና_የጋማ_ከብቶች ለአጠቃላይ የቤተሰብ ብዛት ሲካፈል ነው።

በአሜሪካና ጃፓን አብዛኛው ሰው መኪና ስላለውና ሰርግ ሲሄድም በዚያ ስለሆነ፣ የሰርጉ ሥነ-ስርዓት በመኪና ሰልፍና ጡርባ የታጀበ ቢሆን አያስገርምም። የእኛ ሀገር ሰርገኛ ግን ፈረስ እና በቅሎ ተቀምጦ ከቀንድ የተሰራ ጡርባውን እየነፋ “ሆሆሆ” ከማለት ይልቅ ሁለትና ሦስት የቆረቆሱ መኪኖችን ለምኖና ተከራይቶ “ጲ…ጲ…ጲ” እያደረገ ሰርግ ሲል አይገርምም?

አሁን እንደው፤ ማን ይሙት የእኛ ሀገር ሰርግ የሚያምረው በፈረስ ሲታጀብ ነው ወይስ በመኪና? ሰርጉ’ስ የሚደምቀው በመኪና ጥሩባ ነው ወይስ ከቀንድ በተሰራ ጥሩባ ነው? ምንም ይሁን ምን፤ የሚደምቀው ባለን ነገር ላይ ሲሆን ነው፣ የሚያምርብን ሌሎችን ስንመስል ሳይሆን ራሳችንን ስንሆን ነው። ዘወትር ማለዳ በእድር ጥሩባ ከእንቅልፉ የሚቀሰቀስ ሰው ከደቡብ አፍሪካ የመጣ #ቩቩዜላ ብርቅ ሆኖበት ይዞ ስታዲዮም ይገባል። በስንቱ ነገር የሆነውን ትተን ያልሆነውን እያስመሰልን እንኖራለን?

በመጨረሻ፣ “የአባቴና የአያቴ ሰርግ በመኪና የታጀበ ነበር” የሚል ኢትዮጲያዊ አለ?
ለዚህ ጥያቄ መልሱ “አዎ” የሆነ ሁሉ በእርግጥ እሱ የጣሊያን ባንዳ ወይም ክልስ መሆን አለበት!!!

ethiothinkthank.com