የባንዳ እና ሽፍታ ፖለቲካ

በእኛ በኢትዮጲያዊያን መካከል የሚደረጉ ውይይቶች እና ክርክሮች፣ በግል ሆነ በቡድን የሚሰጡ አስተያዬቶች እና የአቋም መግለጫዎች፣…በአጠቃላይ በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ  እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰነዘሩ ሃሳቦች በሁለት ተቃራኒ ፅንፎች ላይ የረገጡና በጭፍን እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። አብዛኛውን ግዜ ስለ አንድ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉደይ የሚደረጉ ውይይቶች “…..“ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ሰላም!….አምባገነን…ፀረ-ዴሞክራሲ!…..ዘረኛ፣ ነፍጠኛ፣… አሸባሪ፣ አክራሪ፣… ጠባብነት፣ ትምክህተኛነት፣ አማራ…ኦሮሞ…ተግሬ፣ የመለስ… መንግስቱ… የሚኒሊክ ርዝራዦች” በሚሉ የባንዳ ወይም ሽፍታ ጠባብ የፖለቲካ አመለካከት፣ ግርድፍ ፍረጃ፣ ውንጀላና ስድቦች የሚስተናገዱበት ነው።

አንደኛው ወገን የሚፈፅመውን ተግባር ወይም የሚደግፈውን አቋምና አመለካከት ሌላኛው ወገን ለምን እና እንዴት ሊፈፅመው ወይም ሊደግፈው እንደቻለ በመጠየቅ፣ በነገሩ ላይ ምክንያታዊ የሆነ ግንዛቤ ለመጨበጥ ጥረት አያደርግም። በአንድ ወገን የተፈፀምን ተግባር “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ በአግባቡ ለመፈረጅ፣ በቅድሚያ ተግባሩ በምን አይነት ሁኔታ (Space)፣ መቼ (Time)፣ እና ለምን (Cause) እንደተፈፀመ መገንዘብ ያስፈልጋል። አቋም’ም ቢሆን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ፣ መቼ እና ለምን ተቀባይነትና ድጋፍ እንዳገኘ ካልተገነዘብን አንዱ የሌላኛውን አቋም ሊረዳ አይችልም። ለምሳሌ፣ ምን ያህሉ የኢህአዴግ ደጋፊዎች የተቃዋሚዎችን ማንፌስቶ፣ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ፕሮግራሞችን በጥሞና ይከታተላል? የትኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ነው፣ ስለሚቃወመው ኢህአዴግ እና ሀገሪቱን ስለሚመራበት የልማታዊ መንግስት (Developmental State) ፍልስፍና የጠራ ግንዛቤ ያለው?

አንድ ሰው ከጭፍንነት የፀዳ አቋምና በምክንያታዊ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ አመለካከት ሊኖረው የሚችለው፣ በምንደግፈው’ም ሆነ በምንቃወመው አካል (ፓርቲ፣ ቡድን ወይም ግለሰብ) የተፈፀመን ተግባር፤ ለምን፣ መቼ እና እንዴት እንደተፈፀመ መረዳት ሲችል ብቻ ነው። ነገሩን ቀለል ባለ መልኩ ለመገንዘብ እንዲቻለን፣ መስቀል አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በሃይል እንዲበትን ቆመጥና ክላሽ ተሰጥቶት የተላከን አንድ አድማ-በታኝ ፖሊስን እንውሰድ። ይህ የፖሊስ አባል ሰላማዊ ሰልፈኞችን ያለ ርህራሄ በያዘው ቆመጥ ሲደበድብና በጥይት ሲገድላቸው ብናይ፣ ድርጊቱ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው፣ ፖሊሱ’ም ርህራሄ ያልፈጠረበት ጨካኝ አውሬ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተለመደ ነው። ነገር ግን፣ ፖሊሱ ይሄን የጭካኔ ተግባር ለምን፣ መቼና እንዴት እንዳደረገው የበለጠ በተረዳን ቁጥር በጉዳዩ ላይ የነበረን አቋም እየለዘበ ይሄዳል። ሦስቱን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመጠየቅ ምሉዕ የሆነ ግንዛቤ ስናዳብር ግን የፖሊሱ ተግባር አማራጭ ያልነበረውና በነገሮች አስገዳጅነት የተፈፀመ እንደሆነ እንረዳለን። በዚህም፣ ተግባሩን ለመደገፍም ሆነ ለማውገዝ ይሳነናል።

ለምሳሌ፣ ፖሊሱ “ያንን የመሰለ ጨካኝ ድርጊት ለምን ፈፀመ?“ ብለን እንጠይቅ። ከሰልፈኞቹ የተለየ ጨካኝ የሆነ ልብና ሰብዕና ስለነበረው ነው? ነገሩ በማክሲም ጎርኪ መፅሀፍ ውስጥ፣ አንድ ጡረታ የወጣ ራሺያዊ ጀኔራል እና በጉዳት ከጦሩ በተሰናበት ወታድር  መካከል ከሚደረግ ቃለ-ምልልስ ውስጥ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ትዝ አሉኝ።
ጄኔራል፡ “ስማ አንተ!…ወታደር ምንድነው?”
ወታደር፡ “የበላይ አለቃው እንዲያደርግ ያዘዘው የሚያደርግ ነው!“
ጄኔራል፡ “ኧ…አለቃው ዓሳ እንዲሆን ቢያዘውስ?”
ወታደር፡ “ወታደር የታዘዘውን ማድረግ መቻል አለበት።”

በእንዲህ ያለ የሥራ ስነ-ምግባር የታነፀ እና በጥብቅ የዕዝ-ሰንሰለት የሚመራ ወታድር/ፖሊስ፣ የመኖር ህልውናው ከወር-ወር በማታደርሰው ደሞወዝ ላይ እንደተመሰረተ እያወቀ፣ የታዘዘውን ከመፈፀም ባለፈ ድርጊቱ በሚከናዎንበት ቦታና ሰዓት “አ…ይ! ይህ ሰልፍ ሰላማዊ ስለሆነ ትዕዛዙን አልቀበልም!…” ለማለት የሚያስችል ነፃነት ሊኖረው ይችላል? በተለይ እንደ እኛ ሀገር “ሰላማዊ ሰልፎች” ሰልፈኞቹ የያዘውን ቆመጥና ክላሽ ቀምተው ራሱን ደብድበው እንደሚገሉት የሚያውቅ ፖሊስ በ“ሳይቀድሙኝ-ልቅደም” የታዘዘውን ከመፈፀም ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖረው ይችላል? “ሰላማዊ ሰልፍ” እንደተባለው መብትን ለማስከበር ሳይሆን የሌሎችን መብት ለመጣስ የተደረገ ወይም በሚጥስ መልኩ የተደረገ ከሆነ፣ በቦታውና በሰዓቱ በፖሊሱ የፈፀመውን ተግባር ከመፈፀም ውጪ ሌላ አማራጭ ነበር? በዚህ መልኩ አንድ ተግባር የተፈፀመበትን ነባራዊ እውነታ ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር በዝርዝር እየተረዳን በሄድን ቁጥር ድርጊት ፈፃሚው አካል በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ እንረዳለን።

በሕግ’ም ሆነ በሞራል ስነ-ምግባር፣ የአንድ ተግባር ትክክለኝነት እና ስህተትነት የሚወሰነው ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ድርጊቱን ለመፈፀም በነበረው አንፃራዊ ነፃነት እና አስገዳጅነት ነው። በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚፈፀም ተግባር በሕግ’ም ሆነ በሞራል ስነ-ምግባር አግባብነት ይኖረዋል። ለምሳሌ፣ ሰው መግደል በሕግ የተከለከለ ተግባር (ወንጀል) ቢሆንም ሊገድል የመጣን ሰው በአልሞት-ባይ-ተጋዳይ መግደል ግን በሕግ ፊት ተቀባይነት ይኖረዋል።

የመጀመሪያው ግድያ በፈፃሚው አካል ፍላጎት እና ምርጫ (በነፃነት) እንደ ተከናዎነ ስለሚታሰብ ተግባሩ በወንጀልነት ይፈረጃል። በአልሞት-ባይ-ተጋዳይነት የተፈፀመ ግድያ ግን፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈፀመ ተግባር ስለሆነ እንደ መብት ይወሰዳል። በዚህ መሰረት፣ አንድ ተግባር፤ መብትን የማስከበር ይሁን ግዴታ ያለመወጣት፣የሚለየው በሚፈፀምበት ቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር በነበረው አንፃራዊ የነፃነት እና የአስገዳጅነት ሚዛን መሰረት ነው። 
ወደኋላ ተመልሰን የአድማ-በታኙን ተግባር ከውጪ፣ ከሌላ ሰው እይታ አንፃር ሳይሆን፣ እራሳችንን ሙሉ-በሙሉ በእሱ ቦታ ተክተን ብንመለከት፣ ድርጊቱን ሲፈፅም የነበረውን ሁለመና የውጫዊ ገፅታና ውስጣዊ ባህሪና ስሜት፣ አስተሳሰብና አመለካከት ቢኖረን፣ እሱ ያደረገውን ከማድረግ ውጪ ሌላ ለመወሰን አማራጭ አይኖረንም ነበር። ሊዮ ቶልስቶይ “War and Peace“ በተሰኘው መፅሃፉ፣ ምንም እንኳን እኛ ሰዎች እልፍ በሆኑ ጉዳዩች ላይ የተለያየን እንደሆንን ብናስብም፣ በተመሳሳይ ነባራዊ እውነታ ውስጥ ስንገኝ ግን አንድ አይነት ተግባር ስንፈፅም እንደምንገኝ ይነግረናል።

እንደ ማጠቃለያ፣ “ይሄን ማድረግ አልነበረባቸውም፣ እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ?“ በማለት ሌሎችን የምትፈርጅ ሁሉ፣ የፈረጅካቸው ሰዎች ድርጊቱን በፈፀሙበት ቦታ፣ ግዜና ምክንያት እራስህን ብታስቀምጥ፣ እነሱ ያደረጉትን ደግመህ ከማድረግ ውጪ አማራጭና ምርጫ እንደሌለህ ትረዳለህ። ያኔ፣ በነፃነት እንዳደረጉት ያሰብከው ነገር በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዳደረጉት ትገነዘባለህ። ስለዘህ፣ “ይሄን ያደረገ፣…እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው“ ብሎ ሌሎችን ከመፈረጅ እራስን በድርጊት ፈፃሚዎቹ ቦታ በማስቀመጥ ጉዳዩን ለማጤን መሞከር ይገባል። በዚህም እንተ ያወቅከውን እውነት ሌሎቹም እንዲያውቁ በማድረግ፣ በአንተ እሳቤ ትክክል ነው በሆነው መንገድ ድርጊቱን እንዲፈፅሙ ማድረግ ነው። በአንተ እሳቤ ትክክል የሆነው መንገድ፣ እውነተኛና አግባብነት ያለው አካሄድ ከሆነ ሌሎቹን ሰዎች ማሳወቅና ድርጊቱን በአንተ መንገድ እንዲፈፅሙ ማድረግ አይሳንህም። አንተ “ትክክልና አግባብ ነው“ ያልከው ነገር በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ካጣ ግን፣ ትክክለኝነቱና አግባብነቱ ለአንተ ብቻ ይሆናል። ሕይወትና እውነት ደግሞ ባለው ነባራዊ እውነታ እንጂ በአንተ እሳቤ ብቻ አይመሩም።

ethiothinkthank.com

Advertisements