ባይደግፍ_የማይቃወም ህዝብ፥

በህዝብ መስዕዋት ወደ ስልጣን የመጣ ድርጅት ለምን ህዝቡ የለውጥ ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም” ብላችሁ አትበሳጩ። አይዟችሁ ምንም አይደል፣ የተለመደ ነው። ምንም የተለየ ነገር አልተፈጠረም። በመሰረቱ፣ ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ቢሆን የፖለቲካ ስልጣን በእጁ እስካለ ድረስ ይመዘብረዋል። ይሄው ነው የሆነው።

የማይለወጥ ነገር ቢኖ ለውጥ ራሱ ነው። የዚህ ሀገር ፖለቲካ’ም ቢሆን መለወጡ የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ፣ እስካሁን እና ወደፊት ለምትሰጡት ጭፍን የፖለቲካ ድጋፍ፥ “የቀድሞው ሥርዓት ርዝራዥ፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ…” የሚሉት ማንጓጠጫዎች ግን አይቀሩም። መቼም እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ እና ረሃብ ራሳቸውን የሚደግሙበት ሀገር የለምና እስኪ ወደ ኋላ ዞር ብለን እንመልከት።

የፊውዳሉ አገዛዝ ለሁሉም የኢትዮጲያ ህዝቦች ጨቋኝ ነበር። የኤርትራ፣ ትግራይ፣ ጐጃምና ኦሮሞ ወጣቶች የፊውዳሉን አገዛዝ በሃይል በሚታገሉበት ወቅት የሸዋ እና ጐንደር አማራ ዳር ቆሞ ሲያይ የነበረው፣ ገዢው መደብ የአማራው ህዝብ ላቃ ላይ እንደ አልቂት ተጣብቆ ስለነበረው።

ከተጋሩዎች ጋር ተግባብቶ የጋራ የፖለቲካ አቋም እንዳይዝ፤ “ዋ…መንበረ መንግስቱ ወደ ትግራይ ሄዶ እንደ ቀድሞህ “በትግሬ” አገዛዝ ስር ትወድቃለህ…” ብለው ያስፈራሩታል። በተመሣሣይ ከኦሮሞ ጋር እንዳያብር “ዋ…ዘመነ-መሣፍትን በራስህ ላይ መልሰህ ታመጣና እንደቀድሞህ ትበታተናለህ…” ብለው ያስፈራሩታል።

ገዢው መደብ የአማራን ህዝብ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶ፣ ባይደግፍ-እንዳይቃወም አድርጐ፣ ላንቃው ላይ ተጣብቆ ያንን የበሰበሰ ሥርዓት እድሜ አራዘመ።

ህዝቡ ሌላውን ብሔር በፍርሃት እና ጥርጣሬ እንዲመለከት፣ የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን እራስን-በራስ የማስተዳደር መብቱን ዋስትና በማሳጣት የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍ ማግኘት፣ ወይም ህዝቡ ባይደግፍ-እንዳይቃወም የማድረግ ዘዴ አዲስ አይደለም። ከጥንታዊት ግብፅ እስከ ጥንታዊት ቻይና የነበረ፣ ከሮማው ማቻቬሌ እስከ ኢትዮጲያዊው መለስ ዜናዊ የተተገበረ የፖለቲካ አመራር (Political Leadership ) ዘዴ/ስልት ነው።
#EPRDF, #TPLF, #OPDO, #ANDM, #SEPDM, #Ethiopia,

ethiothinkthank.com

Advertisements