የኢትዮጲያ የእድገት አቅጣጫ እየወሰደን ያለው ወደ “ቤጂንግ” ወይስ ወደ “ሲዖል”?

“…’ዴሞክራሲ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ነው’ የሚል በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ የለም።” ይህ የቀድሞው ጠ.ሚ መለስ ዜናዊ ያለ ምንም ማስመሰል በግልፅነት የተናገሩት ነው እውነት ነው። ሀሣቡን በይፋ፣ በመድረክ ላይ አንስተው የተናገሩት አዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ነበር። ውይይቱን ይዘግብ የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ የጠ.ሚ መለስን ሃሣብ “Bold idea…” በመለት ነበር የገለፀው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ከምዕራባዊን ጋዜጠኞች እሳቤ እና ግንዛቤ ውጪ የሆነን ነገር ሲናገሩ የሰማኋቸው ሌላ አፍሪካዊ መሪ ፕረዘዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሲሆኑ፣ በአንድ የምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ላይ “We turn to the East where the Sun rises and give our back to the west where the Sun sets!!” ሲሉ የተናገሩት ነው። ምንም አንኳን የመሪዎቹ ሃሣብ ለምዕራባዊያን ልሂቆች ከሸመደዱት እውነታ ውጪ ቢሆንም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ነባራዊው ገፅታ መሆኑ ግልፅ ነው። ዴሞክራሲ ለኢኮኖሚ እድገት ሳይሆን የኢኮኖሚ እድገት ለዴሞክራሲያዊ ሥረዓት ግንባታ አስፈላጊ መሆኑና ይህን ፊታችንን ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ስናዞር የምናየው ነው።

ምዕራባዊያን እ.አ.አ ከ1960ቹ ጀምሮ “ዴሞክራሲ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ነው” ሲሏቸው የአፍሪካ መሪዎች ከኢኮኖሚ እድገት ዴሞክራሲን አስቀደሙ። የማጣት ስርቅርቅታ እያሰማ ላለ አፍሪካዊ የአውሮፓዊያን ተረት መንገር ትርጉም እንደሌለው የተረዱት ከሃያና ሰላሳ አመታት በኋላ ነው። ቀጣዮቹን ሃያና ሰላሳ ዓመታት ደግሞ ኢኮኖሚያችን እንዴት ማደግ እንዳለበት ሲነግሩንና እኛም ስንሰማቸው ኖርን። በዚህ ግዜ ውስጥ ከአብዛኞቹ ሀገራት ጋር ተመሳሳይ የሆነ የእድገት ደረጃ ላይ የነበሩት የሩቅ ምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ሀገራት፣ አፍሪካዊያንን ጥለው መሄዳቸው ሳይሆን እንዴት ማደግ እንዳለብ ከሚነግሩን የምዕራባዊያ ሀገራትና ተቋማት የተሻለ የእድገት ደረጃ ላይ ደረሱ። በተለይ ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ ያደጉት እንደ ጃፓን እና ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን፣ እንዲሁም ከ1980ቹ በኋላ ደግሞ እንደ ቻይና እና ቬትናም ያሉ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት

አሁን አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የሚከተሉት የልማት አቅጣጫ አሁንም ከብዥታ የፀዳ አይደለም። በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት፣ በምዕራቡ አለም እይታ የተቃኘን አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግተው በሩቅ ምስራቅ ኢሲያ የታየውን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የሚጥሩ ናቸው። ልክ፣ ‘በግራ አይናችሁ-ግራ ትከሻችሁን፣ በቀኝ አይናችሁ-የቀኝ ትከሻችሁን ለማየት ስትሞክሩ የሚታያችሁ አይነት ብ..ዥ ያለ እይታን ይመስላል። ከላይ የጠቀስኳቸው ሦስት የሩቅ-ምስራቅ ሀገራት ይከተሉት የነበረው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ መዋቅር አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከገቡበት ውዥንብር የሚያወጣ ነው። የ”ልማታዊ መንግስት” አቅጣጫ፣ የዴሞክራሳዊ ሥረዓት ግንባታ እና የኢኮኖሚ እድገት ስብጥር ስለሆነ በአንድ ግዜ ወደ ሁለት አቅጣጫ ማየት ሳያስፈልግ ማደግ የሚቻልበት ብቸኛ አማራጭ ነው። ሆኖም ግን፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ይሄን የእድገት አቅጣጫ በይፋ ተቀብላ ያለች ሀገር ኢትዮጲያ ብቻ ናት ማለት ይቻላል።

በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው የፕረዘዳንት ሙጋቤ ንግግር ከዚምባብዌ ይልቅ ኢትዮጲያን ይገልፃል፤ ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደ ምስራቅ አዙራለችና። ወደ ሩቅ-ምስራቅ ፊታችንን ስናዞር ሁለት የተለያየ አይነት ገፅታ ያለው እድገት ይታያል። ለማነፃፀሪያ እንዲሆን የደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን እድገት በአንድ ወገን፤ የቻይና እና ቬትናም እድገትን በሌላ በማድረግ፣ ኢትዮጲያ እያየች ያለችው ወደ’ማን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ምክኒያቱም፣ በሁለቱም ወገኖች እድገት ያለ ቢሆንም ገፅታው ግን በጣም የተለያየ ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የደቡብ ኮሪያ እና የታይዋን እድገት የዴሞክራሳዊ ሥረዓት ግንባታ እና የኢኮኖሚ እድገት ስብጥር ነው። የቻይና እና የቬትናም ኢኮኖሚ እድገት ግን የዴሞክራሲዊ መብቶችን ልዋጭ ነው። እዚህ’ጋ የቻይና ኮሚኒስት ፓርት እንደ መመሪያ የሚከተለው፣  ነገር መትቀስ ይቻላል። በዴሞክራሲያዊ መብቶች እጦት ሳቢያ ሊፈጠር ከሚችለው ነውጥና አመፅ ለማስቀረት ኢኮኖሚው በየአመቱ በስምንት ፐርሰንት ማደግ እንዳለበት ይገልፃል።
በደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን የታየው ግን የኢኮኖሚው እድገት የሚጠይቀውን እና ካለው ማህበራዊ ለውጥ ጋር አብሮ በሚሄድ መልኩ ዴሞክራሲያዊ ሥረዓትን በመዘርጋት ነው።  በተለይ በደቡብ ኮሪያ እና በቻይና ኢኮኖሚ እድገት መካከል ያለው ልዩነት ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ተያይዞ መንግስት በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ ዘርፎች  ውስጥ የሚኖረውን ቁጥጥር ከመቀነስ ጋር በተያያዘ ነው። በደቡብ ኮሪያ የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የመንግስትን ቁጥጥር በፍጥነት ከመቀነስ ጋር የተቀናጀ ነው። በቻይና ያለው የመንግስት ቁጥጥር ግን እየቀነሰ አይደለም ለማለት ባይቻልም ኢኮኖሚው እድገ ባለበት ፍጥነት እየቀነሰ ነው ለማለት አይቻልም።

ኢትዮጲያ እየተከተለች ያለችው የእድገት አቅጣጫ የሚወስደው ወደ ቤጂግ ወይስ ሲኦል ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሀገሪቱ የልማት አቅጣጫ ዋና ቀያሽ የሆኑት የቀድሞው ጠ.ሚ መለስ ዜናዊ ስለ የዴሞክራሲ እና ኢኮኖሚ እድገትን አስመልክቶ የተናገሯቸውን ሃሳቦች ለዚህ ፅሁፍ በሚመች መልኩ አጠር አድርገን እንይ። “…’ዴሞክራሲ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ነው’ የሚል በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ የለም። ስለዚህ፣ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ዴሞክራሲያዊ ሥረዓትን ማስፈን የግድ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ዴሞክራሲ የሚያስፈልገው ለኢኮኖሚ እድገት ተብሎ ሳይሆን በእራሱ ጠቃሚ የሆነ ዕሴት ስላለው ነው።” ከእሳቸው በስተቀር ይህን እውነት ደፍሮ ሲናገር የሰማሁት ባለስልጣን ባይኖርም እንደ አቅጣጫ ግን ኢህአዴግ ሀገሪቱን እየመራበት ነው ብዬ አምናለሁ። 

የቀድሞው ጠ.ሚ በተናገሩት ሀሳብ ጋር በተያያዘ የተሰሩ ጥናታዊ ሥራዎችን ለመዳሰስ ሞክሪያለሁ ነበር። ነገር ግን፣ ሁሉም የሚያረጋግጡት ነገር ቢኖር “ዴሞክራሲ ለኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ነው” የሚለውን ሳይሆን የተገላቢጦሽ ነው። “የኢኮኖሚ እድገት የዴሞክራሲያዊ ሥረዓትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው” የሚል ነበር። የጠ.ሚኒስትሩ መለስ ሃሣብ ግን ከዚህ ያለፈ ያልፋል። እሳቸው በተደጋጋሚ  እንደተናገሩት፤ “እንደ ኢትዮጲያ ላሉ ሀገራት ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲን የምንፈልገው ለእርዳታ ፍርፋሪ ብለን አይደለም፤ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ነው። ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር እና ማስከበር፤ የሕግ የበላይነትን እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ከተሳነን፣ እንደ አንድ ሀገር ያለን ህልውናችን ያከትማል። እንበታተናለን!!!”

ስለዚህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኔስትር፣ “ዴሞክራሲ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ አይደለም”  ሲሉ ለዴሞክራሳዊ ሥረዓት ዝቅተኛ ግምት ሰጥተው ነው ብሎ ማሰብ ፍፅም ስህተት ነው። ምክኒያቱም፣ እንደ እሳቸው አባባል፣ ከኢኮኖሚው እድገት ጎን-ለጎን ዴሞክራሳዊ ሥረዓት እገነባን መሄድ ከተሳነን በኢኮኖሚ የምናሳድገው ሀገር አይኖረንም እንደማለት ነው። በልማታዊ መንግስት አካሄድ ዴሞክራሲያዊ ሥረዓት መገንባት ከኢኮኖሚው እድገት ጋር በተቀናጀ መልኩ የመንግስት በፖለቲካው እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ቁጥጥር መቀነስ ነው። ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጲያ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ከዚህ አንፃር ካየንው አካሄዳችን ለፅድቅ እንጂ ለኩነኔ የሚዳርግ አይደለም። ስለዚህ ልማታዊ መንግስታችን ኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ተኩረት በማድረግ ሀገራችን ወደ “ሲኦል” እንዳትሄድ እየጣረ ያለ ይመስለኛል።
Beijing, here I come!!!

ለነገሩ ከአንዳንድ ቀውሶች በቀር ማን “ሲኦል” መሄድ ይመኛል ብላችሁ ነው?….እኔ’ጃ!!!

ethiothinkthank.com

Advertisements