“ቅይጥ ብሔር” የኢህአዴግ ቅምጥ ናት

ብሔርን/ቋንቋን ማዕከል ባደረገው የኢህአዴግ ፖለቲካዊ መዋቅርና የአስተዳደር ስርዓት የተማረሩ “ቅይጦች” #የነፃአውጪግንባር እናቋቁምና ‘ጥጋቸውንን እንያዝ’ ዓይነት ሃሳብ ተነስቶ አየሁና በነገሩ ላይ አሰብኩበት። ከዚያም በገሩ ዙሪያ የሚከተሉትን 10 ነጥቦች በማንሳት ሃሳቡ በራሱ የኢህአዴግ የብሔር የብሔር ፖለቲካ ፍርፋሪ እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ።


1ኛ፦ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፅንሰ-ሃሳብ በመሰረቱ ፖለቲካዊና መነሻውም የኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ ነው።

2ኛ፦ ይህ የልዓላዊነት ጥያቄ መድረሻው (ምላሹ) እንደ መነሻው ሁሉ መዋቅራዊ (Structural) ሲሆን ፖለቲካዊ አስተዳደር ስርዓትን በመቀየር የሚረጋገጥ ነው።

3ኛ፦ ይህ የሉዓላዊነት ጥያቄ “እኛ የኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፦…” ብሎ በሚጀምረውና ህዳር 29/1987 ዓ.ም በፀደቀው ሕገ-መንግስት ምላሽ አግኝቷል። 

4ኛ፦ ከዚያ በኋላ ባለው ግዜ፣ ሌሎች ለምሳሌ፦ እንደ ኦነግና ኦብነግ ያሉ ድርጅቶች የራስን-በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ማንሳታቸውን ይቀጥላሉ (ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስላሉ…)። ነገር ግን፣ ራሱ በዘረጋው የፖለቲካ አስተዳደራዊ ስርዓት ውስጥ #ለኢህአዴግ የቀረው ሕግን የማስከበር ሥራ እንጂ ራሱ የመለሰውን ጥያቄ መልሶ መጠየቅ አይደለም።

5ኛ፦ ነገር ግን፣ ኢህአዴግ “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች (የቡድን) መብት…” በሚል ከ20 ዓመት በፊት ራሱ የመለሰውን ጥያቄ መልሶ እየጠየቀ ያለበት ዋና ምክንያት የመብቱ ያለመከበር ጉዳይ ሳይሆን ወደ ቀጣዩ ደረጃ፣ መልካም አስተዳደርና ልማትን ወደ ማረጋገጡ ደረጃ ለመሸጋገርና በቂ/አመርቂ የሆነ ምላሽ መስጠት ስለተሳነው ነው።

6ኛ፦ የመልካም አስተዳደርና ልማት የመጨረሻ ግብ በኢኮኖሚና ፖለቲካ ዘርፎች ዘላቂ የሆኑ ለውጦችን በማምጣት የሀገሪቱ ዜጐች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻል ነው።

7ኛ፦ የሀገሪቱ ዜጐች የተሻለ ሕይወት መኖር የሚችሉት በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ነፃነትን ሲቀናጁና፣ በዚህም የዳበረ ማህብረሰባዊ ስርዓት መፍጠር ሲችል ነው። በዚህ ረገድ መንግስት ከዜጐች ለሚነሳው ዘርፈ-ብዙ እና ተለዋዋጭ ፍላጐት አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ሲሳነው፣ ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መንገዶችን ይጠቀማል።

8ኛ፦ ኢህአዴግ ህልውናውን ለማረጋገጥ እየተጠቀማባቸው ካሉት ዋና ዋና መንገዶች አንዱ የከዚህ ቀድም ስኬቶቹን መልሶ-መላልሶ ለህዝቡ በማቅረብ ዋጋ እንዲሰጣቸው ማድረግ፣ የስኬቶቹ ዘላቂነትም ከፓርቲው ህልውና ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ለማሳየት መጣር ነው።  በተለይ የዜጐች የሕይወት ደህንነት፣ የተለያዩ የማህብረሰብ ክፍሎች (የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) ፖለቲካዊ መብት፣ ብሎም የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ከእሱ ውጪ ዋስትና እንደሌላቸው አድርጐ በማቅረብ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተፈላጊነት ማረጋገጥ ነው።

9ኛ፦ በዚህ መሰረት መንግስት ሀገሩቷን ወደፊት ማራመድ ሲሳነው ወደ-ኋላ መራመድ ይጀምራል። ከላይ 5ኛ ላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ የህዝቡን ያልተመለሰ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ  በመዋቅር እና ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉና መንግስት ራሱ ምላሽ የሰጠባቸውን መብቶች (ለውጦች) ዋስትና እንደሌላቸው አድርጐ ማቅረብን እንደ አማራጭ ይወስደዋል።

10ኛ፦ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ወደ-ኋላ እያየ ያለውን ኢህአዴግ ለመታገል “ቅምጥ” በሚል በኢህአዴግ ቅርፅና ይዘት መደራጀት በራሱ ከእሱ ጋራ ወደ-ኋላ አብሮ መራመድ ነው። ከዚያ ይልቅ፣ በዋናነት የዜጐችን በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብት ለማረጋገጥ በሚያስችለው መንገድ ቀጣዩን የወደፊት እርምጃ መራመድ አማራጭ የለውም። ስለዚህ፣ ቀጣዩን የወደፊት እርምጃ ለመራመድ የግለሰብ መብትን እና ነፃነት ማዕከል ባደረገ መልኩ መደራጀትና ትግሉን መቀላቀል አስፈላጊ ነው።


በአጠቃላይ፣ መንገድ ጠፍቶበት ወደ-ኋላ የዞሮን ከፊት ቀድመው መንገድ ይመሩታል፣ አቅጣጫ ያስይዙታል እንጂ አብሮ ወደ-ኋላ ከተዞረ’ማ ነገሩ ሁሉ “የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት…” ዓይነት ነው የሚሆነው። የኢህአዴግን ዜማ እያዜሙ ከእሱ የተሻለ ነገር መስራት አይቻልም። ስለዚህ “ቅይጥ” የምትለዋ ነገር እንደ አማራጭ የፖለቲካ አቅጣጫ መልካም ብትሆንም፣ ውስጧ ሲመረመር ግን እንደ #ቤተ_ምናምኖች ያው የኢህአዴግ ቅምጥ ናት።