እድገትና ውድቀት በልዩነት! ክፍል-2

በሕብረተሰብ ደረጃ ልዩነት እንዲኖር ከተፈለገ ‘ግለሰብ’ በፖለቲካዊ ሥረዓቱ ውስጥ ‘ነፃነት’ ሊኖረው ይገባል። ሰው በተፈጥሮ ፖለቲካዊ እንስሳ ከመሆኑም በላይ፣ የሕይወቱን መንገድ እና የሚመራበትን የሞራል እሴት በእራሱ መወሰን የሚያስችለው ‘የምክኒያታዊ አስተሳሰብ እና የሞራል ስብዕና ባለቤት ነው። በመሰረቱ ግለሰብ የሚያደርጋቸው ማህበራዊ ግንኙነቶች ለመቆጣጠር ከወጡ ሕጎች እና መርሆች በላይ ተፈጥሮ በቸረችው ምክንያታዊ ግንዛቤ እና  የሞራል ስብዕና  ማህበራዊ ግንኙነቱን መምራት ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው፣ ሁላችንም በግላችን ጥሩ፣ መልካም ነው ብለን ያመንበትን ተግባር፤ የሌሎችን መብት በማይነካና ሌሎች በግላቸው ጥሩ ያሉትን ነገር ለማሣካት የሚያደርጉትን ጥረት በማያደናቅፍ መልኩ፣ በራሣችን መንገድ መንቀሳቀስ ስንችል ነው።

ሁሉም ሰው ያሰበውን በራሱ መንገድ ለማሣካት በሚያደርገው ፍትጊያ ሊከሰት የሚችለው ጉዳት፣ እና ሌላ ጠባቂ አካል ማስቀመጥ ከሚያስከትለው ጥፋት አንፃር ሲታይ የመጀመሪያው እጅግ በጣም ውስን ነው። ለምሳሌ፣ አንተ ከእኔ አካሄድ ጥሩውን ወስደህ፣ ከሰራሁት ስህተት ትማራለህ፤ እኔም በተመሣሣይ ከስኬትህ እና ውድቀትህ እማራለሁ። አንተ ሆንክ እኔ፣ አንዳችን የምንከተለው የሕይወት መንገድ ትክክለኝነቱን ለሌላችን ለማረጋገጥ በምናደርገው የማያቋርጥ ጥረት ሁሌም አዲስ ነገር እንፈጥራለን። ስለዚህ፣ ሁለታችንም በግላችን መልካምና ትክክል ነው ብለን በመረጥነው መንገድ ስንጓዝ ለውጥ ይመጣል። እስከ አሁንም በአለም ላይ የመጣው ለውጥ በዚህ መንገድ የተጓዙ፤ በግላቸው መልካም ያሉትን አሳክተው፣ ጥቅሙን ለማህብረሰቡ እንዲዳረስ ባደረጉ ግለሰቦች ነው።

ethiothinkthank.com

Advertisements