እድገትና ውድቀት በልዩነት! ክፍል-3

እኔ እና እንተ የምንከተለው የሕይወት መንገድ ሆነ ሕይወታችንን የምንመራባቸው የሞራል እሴቶች ተመሣሣይ ቢሆኑ የምናጣው ነገር ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ተመሣሣይ የሕይወት መንገድ እና መርህ ሲኖረን በአስተሳሰብ እና አመለካከት አንድ አይነት አቋም ይኖረናል፣ ልዩነት ይጠፋል። አንተ ባልከው ነገር ሁሉ የምስማማ ከሆነ አንተ ከእኔ ምንም ልትማር አትችልም። እኔና አንተ የተለያየ አቋም የምናራምድ ከሆነ፣ በመሰረቱ ከሁለት አንዳችን ወይም ደግሞ ሁለታችንም የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘናል ማለት ነው። ልዩነታችን የአንዳችንን አዋቂነት እና የሌላችንን አላዋቂነት፣ ወይም ደግሞ የሁለታችንንም አላዋቂነት የምንመለከትብት መስታዎት ነው። አቋማችን ተመሣሣይ ከሆነ ስለትክክለኝነቱ ምንም ማረጋገጫ አይኖረንም። ተቃራኒ ሃሣብ በሌለበት ‘የእኔ ሃሣብ ትክክል ነው’ ብሎ ማሰብ ልክ በጭለማ ክፍል የተሰቀለን መስታዎት እየተመለከቱ ቁማናን እንደማድነቅ ይቆጠራል።

ስለዚህ፣ ሰው በተፈጥሮው ነፃ ነው፤ ፋይዳ ያለው ሕይወት ነፃነት ያስፈልገዋል። ነፃነት ሲኖር በሕይወት ምርጫችን ይንፀባረቃል፤ በልዩነት የገለፃል። የሕይወት መንገድ ምርጫችን በግል እሳቤ እና አመለካከት የሚወሰን እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ የሕየወት መንገዶች ይኖራሉ፤ በማህብራዊ ግንኙነታችን ልዩነቶች ይንፀባረቃሉ። ግለሠቦች የግል አመለካከት እና እምነት በሚያራምዱበት ወቅት፣ የተለያዩ ቡድኖች፣ ብሎም የማሕብረሰብ ክፍሎች የፈጠራሉ። እነዚህ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ እና እንቅስቃሴያቸውን ከሚመሩበት የሞራል እሴቶች አንፃር ልዩነት ሲኖር አዲስ ነገር አለ፤ አዲስ ተሞክሮ እና ተጨማሪ ዕውቀት ባለበት መሻሻል እና ለውጥ አለ። በዚህ ምክኒያት በሕብረተሰቡ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ የእድገት እና መሻሻል መንፈስ ይሰፍናል።

 

ethiothinkthank.com