እድገትና ውድቀት በልዩነት! ክፍል-4

“የሥልጣኔ አቅም” ማለት በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለ የእድገት እና መሻሻል መንፈስ ነው። ይህ መንፈስ መሰረቱ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለው “ልዩነት” ነው፤ ልዩነት’ም በተራ ግለሰብ ደረጃ ያለ “ነፃነት” ነው። በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለው “ልዩነት” ሲጠፋ፤ ማህብረሰቡ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ረገድ ያለን “ልዩነት” ማስተናገድ ሲሳነው፣ በሌላ አነጋገር “ልዩነት”ን በ“ተመሣሣይነት” ሲቀይየር፤ የሥልጣኔ እቅም ይሞታል። ሕብረተሰቡ በልዩነት ሊያገኝ የሚችላቸው ጥቅሞች ይቀራሉ፤ የእድገት  እና መሻሻል መንፈስ ይጠፋል። በዚህ መሰረት፣ የተሻለ ነፃነት ያለበት ሕብረተሰብ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎቹ ሰፊ ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ማለት ነው። በመሆኑም፣ በእነዚህ ግንኙነቶች ውስጥ የሚኖረው ሰፊ ልዩነት፣ በአንፃራዊነት የላቀ ነፃነት ይንፀባረቅበታል፣ የላቀ የእድገት እና የመሻሻል መንፈስ ይሰፍንበታል፣ እድገት እና የብልፅግና ምንጭ ይሆናል።

“የግለሰብ ነፃነት” በአንፃራዊነት ሲታይ ዝቅተኛ በሆነበት ሕብረተሰብ፣ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎቹ ልዩነቶች በስፋት አያስተናግድም። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ግለሰቦች እዳዲስ ሃሣቦች፣ ሥራዎች፣ እና የአሰራር መንገዶች ተጠቅመው እንዲሰሩ የሚያስችል ነፃነት ስለማይኖር፤ ሁሉም ነገር ወጥና ተመሣሣይ በሆነ መልኩ ስለሚከናዎን፤ ሥራዎች፣ አሰራሮች፣ እና ግልኙነቶች በነፃነት አይከናዎኑም። በዚህም፣ የእድገት እና የመሻሻል መንፈስ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክኒያት እድገት እና የብልፅግና ምንጭ መሆን ይሳነዋል። ሁሉም ነገር ተመሣሣይ በሆነ መልኩ ሲከናዎን፣ ሥራዎች እና አሰራሮች ታደጋጋሚ እና ድግግሞሽ ይሆናሉ። ይህ ሲሆን የሥራና የአሰራር መርሆች መሰረታዊ አላማቸውን ይስታሉ። ስራውን የሚሰራው ሰው አዕምሮውን ተጠቅሞ እንዲሰራ፣ አዲስ እና የተሻለ አሰራር እንዲሰፍን ስለማይፈቅዱ ሥራው በእራሱ ትርጉም-አልባ ያደረገዋል።

ethiothinkthank.com