እድገትና ውድቀት በልዩነት! ክፍል-5

በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለ “ልዩነት” የሚጠፋው የአንደኛው ክፍል እምነት፣ መርህ እና መመሪያ በሌሎቹ ላይ ሲጫን እና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተመሣሣይ የሆነ አቋም፣ መርህ እና መመሪያ ሲኖራቸው ነው። ለምሣሌ፣ ጆን ስትዋርት ሚል እንዳስቀመጠው፣ የምዕራብ አውሮፓ የሥልጣኔ መሰረት የሆነው ነገር በክፍለ-ሀጉሩ ያለው ልዩነት፡- በባህል፣ ፖለቲካ፣ በአጠቃላይ በሁሉም ረገድ የሰፋ ልዩነት መኖሩን የአውሮፓ ብልፅግና ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ዋና ምክኒያት መሆኑን ይገልፃል።

እንደ ጆን ስትዋርት ሚል አገላለፅ፣ “በተለምዶ በተለያየ አቅጣጫ የሚሄዱ ሀገራት ወይም ሕዝቦች አንዱ ሌላውን ወደ እራሱ መንገድ የማምጣት ፍላጎት አላቸው….ለምሳሌ፣ ሁሉም የምስራቁ አለም ሥልጣኔዎች ለውድቀት የተዳረጉት በአንድ ወቀት ለከፍተኛ ስልጣኔ ያደረሷቸውን ማህበራዊ እሴቶች፡- እምነቶች፣ መርሆች እና መመሪያዎች በተቀሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንዲጫን በማድረግ ነው።“ በአውሮፓም የዚህ አይነት የማያቋርጥ ጥረት ይደረግ ነበር። ሆኖም ግን፣ የአውሮፓዊያኑን ሀገራት በሌሎች ቦታዎች ከታዩት ሥልጣኔዎች ለየት የሚያደርገው ነገር፣ ምንም እንኳን አንዱ ሌላውን ለመጨፍለቅ የማያቋርጥ ጥረት ቢያደርግም፣ በቋሚነት ሥኬታማ መሆን የቻል ሀገር ግን አልነበረም።

በረጅም የግዜ ሂደት ውስጥ ስናየው፣ ከምዕራብ አውሮፓ ሀገራት፣ ለምሣሌ፡- ፈረንሣይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ የጣሊያን ከተሞች እና ሌሎች አንዱ ሌላውን በመጨፍለቅ፣ በዚህም አንድ ዓይነት መንገድ እንዲጓዝ ለማድረግ የተደረጉት ጦርነቶች እና ፍትጊያዎች በአንዱ ወገን ዘላቂ የሆነ አሸናፊነት አልተጠናቀቁም። በመሆኑም፣ በተለይ አውሮፓዊያን የበላይነት መያዝ ከጀመሩበት ከ14ኛ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ከፍተኛው ደረጃ ላይ እስከደረሱበት የ18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በብልፅግና እያደጉ መቀጠል አስችሏቸዋል።

ethiothinkthank.com

Advertisements