እድገትና ውድቀት በልዩነት!

የሀገር ብልፅግና እንዲረጋገጥ በሁሉም ማህበራዊ ዘርፎች እድገት እና መሻሻል መቋረጥ የለበትም። ስለዚህ፣ የእድገትና መሻሻል መንፈስ በማሕብረሰቡ ዘንድ መስረፅ አለበት። ይህ ሊሆን የሚችለው በማህበራዊ ሕይወታቸው ልዩነት ሲኖር ነው። የእድገት እና መሻሻል መንፈስ ሊፈጠር የሚችለው በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊ ጉዳዮች፤ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ በአኗኗር ዘይቤ እና የሞራል እሴቶች ያላቸውን ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል ሲችሉ ነው። እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል በእራሱ የሕይወት ፍልስፍና እና አቅጣጫ በሚሄድበት ወቅት ለራሱና ለሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አዲስ ልምድ እና ተሞክሮ ያካፍላል፣ ኑሮ እና አኗኗር እንዲሻሻል ያደርጋል።

ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም፣ በአጠቃላይ ከሀገር ብልፅግና እና እድገት አንፃር ሲታይ፣ ልዩነት ምንግዜም ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ለምሣሌ፣ አንድ የሕብረተሰብ ክፍል የሚከተለው የሕይወት መንገድ ብልፅግናን ከማምጣት አንፃር ሲታይ ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። ነገር ግን፣ የተከተሉት የሕይወት መንገድ ጠቃሚ ከሆነ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲከተሉት፣ጎጂ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የተቀሩት መንገዱን እንዳይከተሉት ትምህርት ይሆናል። ስለዚህ፣ ልዩነት ባለበት ሁሌም አዲስ ነገር አለ፤ አዲስ ተሞክሮ እና ተጨማሪ ዕውቀት ባለበት መሻሻል እና ለውጥ አለ። በሕብረተሰቡ ውስጥ የዚህ ዓይነት ልዩነት ከሌለ ግን የእድገት እና የመሻሻል መንፈስ ይከስማል።

ልዩነት ሊገለፅ የሚችለው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ እና እንቅስቃሴያቸውን ከሚመሩበት የሞራል እሴቶች አንፃር ነው። ይህም ግለሰብ፣ ቡድን፣ ወይም ሕብረተሰብ አንዱ ከሌላው ጋር በሚያደርገው ግንኙነት የሚገለፅ ነው። ሆኖም ግን፣ ‘ቡድን’ የግለሰቦች ስብስብ፣ ሕብረተሰብ’ም እንዲሁ የቡድኖች ወይም የግለሰቦች ስብስብ እንደመሆናቸው መጠን፤ ሕብረተሰብ እራሱን የቻለ ህልውና እና አቋም ሊኖረው አይችልም። ከዚያ ይልቅ፣ ልዩነትን ማራመድ የሚችለውና የእራሱ አቋም መያዝ የሚችለው ‘ግለሰብ’ ነው። ‘ግለሰብ’ አንዱ ከሌላው ጋር ወይም ከሕብረተሰቡ ጋር የሚኖረው ግንኙነት የሚመራበት ማህበራዊ ሥረዓት ‘የፖለቲካ ሥረዓት’ ሲሆን ሥርዓቱ የሚመራበትን መርህ የሚያስቀምጥና የሚቆጣጠር ደግሞ መሪ የፖለቲካዊ ሃይል – መንግስት ነው።

ethiothinkthank.com

Advertisements