ለነፃነት ዋጋ በሚሰጥበት ሀገር ለጀግኖች ተገቢው ክብር ይሰጣል!

ባለፈው ወር ከአብዲሳ አጋ ልጅ ጋር በተያያዘ አንዲት ፅሁፍ እዚህ ፌስቡክ ላይ አውጥቼ ነበር። ያን ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች ለአብዲሳ አጋ ቤተሰብ በራሳቸው ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት አንዳላቸው በመግለፅ፣ የቤተሰቡን አድራሻ እና አንዳንድ መረጃዎች ጠይቀውኝ ነበር። በዋናነት ማህሌት በላቸው ያሳየችው ተነሳሽነት እና ያደረገችው ጥረት በጣም የሚመሰገን ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል በቅድሚያ ስለ ቤተሰቡ እና የኑሮ ሁኔታ የተሟላ መረጃ ሊኖር ይገባል። በዚህ መሰረት፣ ዛሬ የአብዲሳ አጋ ልጅ ከሆነው ከኤልያስ አብዲሳ ጋር የግማሽ ሰዓት (29.22 ደቂቃ) ያህል ቆይታ በማድረግ ውይይታችንን በሞባይሌ መቅረፀ-ድምፅ ቀድቼዋለሁ። ስለ አብዲሳ አጋ ቤተሰብ ያለውን ነባራዊ እውነታ ለማወቅና በተቋም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ድጋፍ ለማድረግ ለምትሹ ግለሰቦች የድምፅ መረጃውንና ሌሎች ማስረጃዎችን በኢሜል አድረሻችሁ መላክ ይቻላል።

በምናባዊ እሳቤ ካልሆነ በስተቀር በእውን ለማሰብ ከሚከብደው የጀግንነት ታሪኩ ውስጥ የተወሰነች ነገር ለማለት ያህል….አብዲሳ አጋ በፋሽስቶች ተማርኮ ወደ ሮም ከተወሰደና ከእስር ቤት አምልጦ ከወጣ በኋላ እዚያው በኢጣሊያን ሀገር የሸፈተ፣ የራሱን አማፂ ቡድን አቋቁሞ በሁለተኛው አለም ጦርነት በፋሽስቶች እና ናዚዎች መቃብር ላይ የነፃነት ችቦ የአበራ…በተለይ ፋሽስት ጣሊያን ሲወድቅ የኢትዮጲያን ሰንደቅ-አላማ እያውለብለበ ከፊት ቀድሞ ሮም ከተማ የገባ፣ ቀጥሎ የጀርመን ናዚ ሲወድቅም ደግሞ በተመሳሳይ የሀገሩን ሰንደቅ-አላማ እያውለበለበ በርሊን የገባ ከሀገሩ አልፎ በአለም የነፃነት ትግል ውስጥ አኩሪ ታሪክ የፈፀመ፣ የነፃነት ፈር-ቀዳጅ ኢትዮጲያዊ ነው። 

ከዚህ ጀግና ልጅ፣ ከኤልያስ አብዲሳ አጋ ጋር በነበረኝ ቆይታ ስለ ቤተሰብ እና የኑሮ ሁኔታ የተገነዘብኳቸውን አንዳንድ ነጥቦችን ለመጥቀስ ያህል… አብዲሳ አጋ ከአውሮፓ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ትዳር መስርቶ ይኖር የነበረ ቢሆንም በግምት ከዛሬ 50 ዓመት በፊት (1950ቹ መጨረሻ አከባቢ) የመጀመሪያ ሚስታቸው በሞት ተለይተዋቸዋል። በመቀጠል፣ እስከ አሁን በሕይወት የሚገኙትን ወ/ሮ ቀለሟን በማግባት የ48 ዓመቱ ኤልያስ አብዲሳን ወልዷል። አብዲሳ አጋ በሞት እስከተለየበት 1970 ዓ.ም ድረስ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ወሎ-ሰፈር ከወ/ሮ ቀለሟ እና ከእና ኤልያስ ጋር የኖረ ሲሆን፣ በተለይ ኤልያስ በጥንታዊት ኢትዮጲያ የጀግኖች አርበኞች ማህበር፣ “የአርበኛው ተተኪ ልጅ“ በሚል ሙሉ እውቅና የተሰጠው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አባቱ በተለያዩ የጦርነት አውድማዎች የተሸለማቸው ሜዳሊያዎች፣ ኒሻኖች፣ የተለያዩ የክብርና ወታደራዊ ማዕረጎች፣ እንዲሁም የግል ሕይወት ታሪክ (ድያሪ) ጥራዝ ጭምር በኤልያስ እጅ ይገኛሉ። 

ከኤልያስ ጋር ባደረኩት ቆይታ፣ የአብዲሳ አጋ’ን ጀግንነትና ክብርን እንዲያስጠብቅ “የአርበኛው ተተኪ ልጅ“ የሚለውን የክብር ስያሜ ልዩ መታወቂያን በማየቴ በጣም አስደንቆኛል።  የሆነ ልዩ የሆነ ክብር ስሜት ይፈጥራል። ነገር ግን፣ አብዲሳ አጋ እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ አብረዋቸው የኖሩት የወ/ሮ ቀለሟ ሆነ የኤልያስ ሕይወት በጣም አሳዘኝ ነው። በተለይ፣ አብዲሳ አጋ አዲስ አበባ፣ ወሎ ሰፈር 1300 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ግቢ ውስጥ መኖሪያ ቤት ሰርቶ ለቤተሰቡ አውርሶ ኖሯል። ባለቤቱም ቀድሞ ያገኙት በነበረው 163 ብር የጡረታ ገንዘብ ፈፅሞ መኖር ስለማያስችላቸው፣ የመኖሪያ ቤቱን የተወሰኑ ክፍሎች እያከራዩ ጥሩ የሚባል ኑሮ ይኖሩ ነበር። ነገር ግን፣ የስድስት መቶ ሺህ ብር ካሳና የ1300 ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ 200 ካሬ ሜትር ቦታ በምትኩ በመስጠት አብዲሳ አጋ ለቤተሰቡ ሰርቶ ያወረሰው መኖሪያ ቤት መንግስት አፍርሶታል። በዚያ ላይ፣ ለቤቱ የተከፈለው የካሳ ገንዘብ ከቀድሞ ሚስታቸው ከተወለዱት ልጆች ጋር የተካፈሉ መሆኑ ሲታሰብ፣ ወ/ሮ ቀለሟ ከባለቤታቸው ጋር በጋራ የሰሩትን የመኖሪያ ቤት መስራት ቀርቶ፣ አንዲት ማረፊያ ጎጆ የተሰራው እንኳን በሌሎች ሰዎች ድጋፍ ነው። በዚህ በተረፈ፣ በአሁን ወቅት ወ/ሮ ቀለሟ የሚተዳደሩበት የአብዲሳ አጋ ባለቤትነታቸው በሚያገኙት የጡረታ ገንዘብ ሲሆን፣ ይህም በወር 500 ብር ነው። ደሃ ሀገር ለአለምና ለጀግናዋ የምትከፍለውን የጡረታ ገንዘብ መጠንን አያችሁልን?

መንግስት አብዲሳ አጋ በጡረታ ዘመኑ ሰርቶ ለቤተሰቡ ያወረሰውን ንብረት አፍርሶ በምትኩ ፍፁም ተመጣጣኝ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ከፍሎ ሚስትና ልጆቹን አፈናቅሏቸዋል። ይህ ለኢትዮጲያ ነፃነት የወጣትነት ዘመኑን ሙሉ-በሙሉ አሳልፎ ለሰጠ ብሔራዊ ጀግና፣ ለአብዲሳ አጋ ፍፁም የማይገባ ድርጊት ነው። የነፃነት ትርጉምና ፋይዳ የገባን ኢትዮጲያኖች፣ ለሀገራችን ነፃነት ዋጋ የምንሰጥ ዜጎች ለአብዲሳ አጋ ቤተሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለጀግኖቻችን ክብር እንስጥ!!!

ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com